በየመን የተጣለው ዕገዳ ከተነሳ በኋላ የምግብ ድጋፍ የሃገሪቱ ወደብ ደረሰ

A Yemeni woman holds her malnourished child receiving treatment amid worsening malnutrition at a hospital in Sana"a, Yemen, 24 November 2017. Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ የመናዊያን ለረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት

በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ቡድን ለሶስት ሳምንት የጣለውን ዕገዳ ማንሳቱን ተከትሎ ምግብ የጫነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርከብ በየመን አማጺዎች ቁጥጥር ስር በሚገኘው ወደብ እንዲቆም ተፈቅዶለታል።

ዕገዳው በድርቅ ተጎድተው የነበሩ ሚሊዮኖችን ለባሰ ችግር አጋልጧል።

የህክምና ቁሳቁስ የጫኑ አውሮፕላኖች በየመን ዋና ከተማ ሰነዓ እንዲያርፉ ባለፈው ቅዳሜ የተፈቀደ ሲሆን የምግብ ድጋፍ እንዲገባ ሲደረግ ግን የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

እገዳው ተጥሎ የቆው ከሶስት ሳምንት በፊት በሳዑዲ አረቢያ ላይ የሚሳኤል ጥቃት ከደረሰ በኋላ ነበር።

በየመን የሚገኙ የታጣቂ ቡድኖች በሳዑዲ ዋና ከተማ ሪያድ የሚሳኤል ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ በምድር፣ በውሃም ሆነ በአየር የሚደረግ ጉዞ ላይ ዕገዳ ጥለው ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርከብ በሺህዎች የሚቆጠር ቶን ስንዴ ይዞ ሳሊፍ ወደብ ደርሷል።

የሃገሪቱ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ስቴፈን አንደርሰን ለቢቢሲ እንደገለጹት መርከቡ 1.8 ሚሊዮን ሰዎችን ለአንድ ወር መመገብ የሚያስችል ስንዴ ይዟል።

መርከቡ የመግቢያ ፈቃድ እስኪያገኝ ድረስ በወደቡ አካባቢ ለሁለት ሳምንታት ቆይቷል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳይ ቢሮ የሁዳይዳህ ወደብ ተዘግቶ እንደቀረ አስታውቆ ነበር

5500 ቶን የስንዴ ዱቄት የያዘ የንግድ መርከብ በምዕራብ ሳሊፍ በሁቲ አማጺያን ቁጥጥር ስር በሚገኘው ሁዳይዳህ ወደብ መድረሱ ይታወቃል።

"በሰሜን የመን ለሚገኙ ሰዎች ይህ አዎንታዊ ለውጥ ነው" ሲሉ አንደርሰን አስረድተዋል።

በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ቡድን የሁዳይዳህ ወደብን እና የሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዕርዳታ ሥራ ክፍት ይሆናሉ ብሎ ነበር።

ባለፈው አርብ ግን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳይ ቢሮ የሁዳይዳህ ወደብ ተዘግቶ እንደቀረ አስታውቆ ነበር።

በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ቡድን ዕገዳው አማጺዎች የጦር መሣሪያ እንዳያገኙ ለማድረግ የታቀደ ነው ይላል። ኢራን ለሁቲ አማጺያን የጦር መሣሪያ ድጋፍ ታደርጋለች በሚል ሳዑዲ አረቢያ ብትከስም ቴህራን ውድቅ አድርጋዋለች።

ቅዳሜ ሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያ 1.9 ሚሊዮን ክትባት ቢደርስም ዩኒሴፍ ግን መድኃኒቱ አነስተኛ መሆኑን አስታውቋል።

"በጣም አስፈላጊ እና አንገብጋቢ የሆነውን ነገር ከማድረስ ምንም እንዳይከለክለን በህጻናቱ ስም እጠይቃለሁ" ሲሉ በመካከለኛው ምስራቅ የዩኒሴፍ ዳይሬክተር ግሪት ካፕላየር ለሮይተርስ ተናግረዋል። "ትላንት የደረሰን በጣም ጥቂቱ ነው" ብለዋል።

በየመን የሚገኙ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ይፈልጋሉ። ከእነዚህ ውስጥ 11 ሚሊዮን የሚሆኑት ህጻናት ሲሆኑ 400 ሺዎቹ ደግሞ በከፍተኛ ያልተመጣጠነ የምግብ እጥረት ተጎድተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች