የዱቄት ወተት እና የእናት ጡት ወተት ምንና ምን ናቸው?

በጡጦ ተበጥብጦ የተዘጋጀ የዱቄት ወተት Image copyright Getty Images

መርዛማ ጋዝ እና የቀለጠ አለት ተቀላቅለው ከ ታምቦራ ተራራ በንፋስ ፍጥነት ሺዎችን እየገደሉ ይንደረደራሉ። ግዙፉ የታምቦራ ተራራ በ 1220 ሜትር አጥሯል።

ይህ የሆነው በ1815 ነበር። ቀስ በቀስ የአመድ እሳተገሞራ ወደ ሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ በማምራት ፀሀይን ጋረዳት።

በ1816 አውሮጳ ያለ ክረምት ያለፈ ዓመት ሆነ ፤ ሰብሎች ደረቁ። ረሃብ የጠናባቸው ሰዎች አይጦችን፣ድመቶችን እና ሳር ተመገቡ።

በጀርመኗ ዳርምስታድት ከተማ የዚህ ጉስቁልና ጥልቀት ለ 13 ዓመቱ የፈጠራ ሃሳብ ፈነጠቀለት። ጀስተስ ቮን ሊይቢግ አባቱን በስራ ቦታው ቀለም በመቀባት፣ በመወልወል እና በማቀራረብ ማገዝ ይወድ ነበር።

ጥልቅ ጥናት

ሊይቢግ ርሃብን የመከላከል ምኞትን ሰንቆ ምርጥ የኬሚስትሪ ባለሙያ ሆኖ አደገ። በማደበሪያ ላይ የተደረጉ የቀደሙ ምርምሮችን ሰርቷል። የስነምግብ ሳይንስ ምርምርም ፈርቀዳጅ ነው።

ይህ ብቻ አይደለም ሌላም ነገር ፈጥሯል፡ የዱቄት ወተትን።

ሊይቢግ በ1865 ያስተዋወቀው ለህፃናት ያዘጋጀው ሟሚ ምግብ ከላም ወተት፣ከስንዴና ከብቅል ዱቄት እንዲሁም ከ ፖታሺየም ካርቦኔት የተዘጋጀ ነበር።

ይህ የእናት ጡት ወተትን ተክቶ ለገበያ የቀረበ የመጀመሪያው የምርምር ውጤት ነበር።

ሊይቢግ እንዳስተዋለው ሁሉም ህፃን ጡት የሚያጠባው እናት የለውም።

ዘመናዊ ህክምና ሳይስፋፋ በፊት ከ100 ነፍሰጡር እናቶች መካከል አንዷ በወሊድ ምክንያት ትሞት ነበር። ዛሬ ይህ ቁጥር በድሃ አገራት በመጠኑ የተሻሻለ ነው።

አንዳንድ እናቶች ደግሞ ጡታቸው ወተት አያግቱምም፤ ቁጥሩ አከራካሪ ቢሆንም ከሃያ እናቶች መካከል አንዷ ይህ አይነት ነገር እንደሚገጥማት ይገመታል።

ታዲያ የዱቄት ወተት ከመፈብረኩ በፊት እነዚህ ህፃናት ምን ይውጣቸው ነበር?

አቅሙ ያላቸው ወላጆች ልጃቸውን የሚያጠባላቸው ነርስ ይቀጥሩ ነበር፤ ከሊይቢግ ፈጠራ በፊት ጥሩ ገቢ የሚገኝበት ስራ ነበር። አንዳንዶች ደግሞ ፍየል ወይም አህያን ይጠቀሙ ነበር።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ጀስተስ ቮን ሊይቢግ የፈጠራ ሃሳቡ የመጣለት አዳጊ እያለ የተመለከተው ረሃብ ነበር

ጥሩ ግጥምጥሞሽ

በርካቶች ለጨቅላዎቻቸው ዳቦ በውሃ አላቁጠው ይመግቡ ነበር፤ ይህ ደግሞ የመመገቢያ እቃው በቀላሉ በባክቴሪያ ስለሚበከል የጨቅላው ጤና አደጋ ላይ ይወድቃል።

በ1800ዎቹ የመጀመሪያ አመታት የእናታቸውን ጡት ወተት ማግኘት ካልቻሉ ሶስት ህፃናት መካከል ሁለቱ ብቻ ነበሩ በህይወት መኖር የሚችሉት።

የሊይቢግ የዱቄት ወተት በዚህ ወሳኝ ወቅት ነበር ገበያውን የተቀላቀለው።

የጀርም ቲየሪ በሚገባ ተዋውቆ ነበር፤ የጡጦ ጫፍም ተፈብርኮ ነበር። በዚህ ወቅት የዱቄት ወተትም ጡት ማጥባት ካልቻሉ እናቶች በላይ ፈጥኖ ተሰራጨ።

የሊይቢግ ለህፃናት የተዘጋጀ ሟሚ ምግብ ቀደም ሲል ጥሩ የኑሮ ዘይቤ ለሚመሩ ብቻ የነበረው አስቀርቶ ለሁሉም መድረስ ቻለ።

አሁን ደግሞ ዘመናዊ የስራ ቦታን መልክ ለመስያዝ የሚመረጥ ሆኗል። ከወለዱ በሗላ ወደ ስራ መመለስ ለሚፈልጉ በርካታ እናቶች የዱቄት ወተት የፈጣሪ በረከት ሆኖ ቀረበ።

የገቢ ክፍተት

በቅርቡ የቺካጎ ዩኒቨርስቲ ከማስተርስ ዲግሪ መርሃ ግብር ወጥተው በማማከር እና በፋይናንስ አለም ወደስራ የገቡ ከፍተኛ ሃላፊነት ያላቸው ወንዶችና ሴቶች ላይ ጥናት አድርጎ ነበር።

መጀመሪያ ላይ በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለው የገቢ መጠን ተመሳሳይ ይመስል ነበር።

ከጊዜ በሗላ ላይ ግን ከፍተኛ የሆነ የገቢ ልዩነት መታየት ጀመረ። ይህ ደግሞ የሆነው በወሊድ ጊዜ ነው። ሴቶች ሲወልዱ ልጆቻቸውን ለመንከባከብ ከስራ እረፍት ይወስዳሉ በምላሹ ቀጣሪዎች አነስተኛ ክፍያ ይከፍሏቸዋል።

በተገላቢጦሽ ከሴቶች የበለጠ ልጅ ያላቸው ደግሞ ወንዶች ናቸው። ነገር ግን የስራ ጊዜያቸውን አይቀይሩም።

ሴቶች ብቻ አምጠው መውለድ የመቻላቸውን ሀቅ ልንቀይረው አንችልም፤ነገር ግን የስራ ቦታ ባህሉን ልናስተካክለው እንችላለን።

አንዲት ወላድ እናት ከወሊድ በሗላ ወደ ስራዋ ስትመለስ አባቶች ልጃቸውን ለመንከባከብ የዱቄት ወተት ቀላል ያደርግላቸዋል።

በርግጥ የጡት ማለቢያ አማራጭ አለ። ነገር ግን ለአንዳንዶች ይህ ከዱቄት ወተት በላይ ጥረት የሚጠይቅ ነገር ነው።

በ2016 በህክምና የጥናት መፅሄቶች ላይ የዱቄት ወተት የጎንዮሽ ጉዳቶችን የሚያሳዩ በርካታ ጥናቶች ታትመዋል።

የዱቄት ወተት የሚጠጡ ህፃናት የእናታቸውን ጡት ከሚጠቡ ህፃናት በበለጠ ይታመማሉ፤ በዚህም የተነሳ ወላጆች የህክምና ወጪያቸው ይጨምራል፤ እንዲሁም ከስራ ገበታቸው ላይ በተደጋጋሚ ይቀራሉ።

ጡት በማጥባት ብቻ ግማሽ ያህል የህፃናት ተቅማጥን እና ሶስት እጅ የሚሆነውን ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዘ ኢንፌክሽንን መከላከል እንደሚቻል ይታመናል።

በዚህ ጥናት መሰረት የእናት ጡት ወተት በአመት 800 000 ያህል የህፃናት ሞትን መከላከል ያስችላል።

ታዲያ ሕይወት ለመታደግ ለፈለገው ጀስተስ ቮን ሊይቢግ ይህ አስደንጋጭ ነው።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ጨቅላ ህፃናትን የእናት ጡት ማጥባት በአመት ከ 800,000በላይ የህፃናት ሞትን እንደሚከላከል አጥኒዎች ያምናሉ

ኢኮኖሚያዊ አንድምታው

እርግጥ ነው ባደጉት ሃገራት የተበከለ ወተት እና ውሃ ጉዳይ ያን ያህል ራስ ምታት አይደለም።

የዱቄት ወተት ግን ሌላ ኢኮኖሚያዊ ገፅታ አለው።

በላንሰንት ጥናት መሰረት የእናታቸውን ጡት እየጠቡ ያደጉ ልጆች የአይ ኪው (IQ)መጠናቸው ከሌሎቹ በሶስት ነጥብ ከፍ ያለ ነው። ይህ ታዲያ ትውልዱን ሁሉ ባለ ምጡቅ አዕምሮ ለማድረግ ምን ያህል ይሆናል?

ጥናቱ ይህንንም አስልቶታል። በአመት 300 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ያህል ያስወጣል። ይህ ደግሞ የአለም የዱቄት ወተት ገበያ ያህልን ይሆናል።

ሊይቢግ ራሱ ለህፃናት ያዘጋጀው ሟሚ ምግብ ከእናት ጡት ወተት ይበልጣል ብሎ ተወራርዶ አያውቅም፤ በተቻለ መጠን በንጥረ ነገር ተመሳሳይ የሆነ ነገር እንደፈጠረ ግን ተናግሯል።