ፕሬዝዳንት ኬንያታ ለመጨረሻው የሥልጣን ዘመናቸው ቃለ መሐላ ፈጸሙ

ኡሁሩ ቃለመሃላ ሲፈጽሙ Image copyright AFP

ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ለመጨረሻውና ለሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው ዛሬ ቃለ መሃላ ፈጸመዋል።

ከፍተኛ የደህንነት ጥበቃ ባልተለየው በዓለ-ሲመት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን ጨምሮ ከ20 በላይ መሪዎችና ሚኒስትሮች ተገኝተዋል።

ከድጋሜ ምርጫው ራሳቸውን አግልለው የነበሩት የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ራይላ ኦዲንጋ ምንም እንኳ በፖሊስ ቢታገድም የተቃውሞ ሰልፍ ጠርተዋል።

በነሐሴ የተደረገው ምርጫ አንዳንድ ክፍተቶች ታይተውበታል በማለት የከፍተኛው ፍርድ ቤት በድጋሜ ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ አሳልፎ ነበር።

የድጋሜ ምርጫው የተካሄደው ባለፈው ጥቅምት ወር ሲሆን ፕሬዝዳንት ኬንያታ 98% በማግኘት አሸናፊ ሆነዋል።

Image copyright AFP

በተከፋፈለ ሕዝብ መካከል የሚካሄድ በዓለ ሲመት

ዛሬ ማክሰኞ በናይሮቢ ስታዲየም በተካሄደው በዓለ ሲመት ላይ ከ60,000 በላይ ሰዎች ታድመዋል።

የበዓለ ሲመቱ አዘጋጆች ወደስታዲየሙ መግባት ላልቻሉ ደግሞ ትላልቅ ስክሪኖች በስታዲየሙ ዙሪያ አቁመዋል።

የፕሬዝዳንት ኬንያታ ምክትል የሆኑት ዊሊያም ሩቶም ዛሬ ቃለ-መሐላ ፈጽመዋል።

በበዓለ ሲመቱ ላይ ከተገኙት መሪዎች የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የዩጋንዳው ዩዌሪ ሙሴቪኒና የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ ይጠቀሳሉ።

የኬኒያ የተቃዋሚዎች ቅንጅት ለደጋፊዎቹ የበዓለ ሲመቱ ላይ እንዳይገኙ ጥሪ ያስተላለፈ ሲሆን ከነሐሴ ጀምሮ በነበሩ ተቃዎሞዎች ሕይወታቸውን ያጡትን ለማሰብ ሰልፍ ጠርቷል።

ፖሊስ ቅንጅቱን ምንም አይነት ሰልፍ እንዳያካሄድ ቢያስጠነቅቅም ይህን ተላልፈው ሰልፍ ለማካሄድ ከሞከሩ ተቃዋሚዎች ጋር ተጋጭቷል።