ቻይናዊያን ታዳጊዎች 80ኪሜ በአውቶብስ ስር ሆነው ተጓዙ

Two boys hiding under a bus in China Image copyright Southern Morning Post

ሁለት ቻይናዊያን ታዳጊዎች ከአውቶብስ ዕቃ መጫኛ ስር 80 ኪሎሜትር መጓዛቸው ሃገሪቱ ለህጻናት ደህንነት የሰጠችው ትኩረት አነስተኛ ነው በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎች ትችት አስከትሏል።

ስማቸው ያልተጠቀሰው ታዳጊዎች ዝቅተኛ ገቢ አላቸው ከሚባሉት ከደቡባዊ ጉዋንግዢ መንደሮች በጉዋንግዶንግ የሚሠሩትን ወላጆቻቸውን ለማየት ነው ጉዞውን ያደረጉት።

ተማሪዎቹ ህዳር 14 መጥፋታቸውን መምህራኖቻቸው የገለጹ ሲሆን በዛው ዕለት በአውቶብስ መነሃሪያ ውስጥ ተገኝተዋል።

ከአውቶብሱ ዕቃ መጫኛ ስር በጭቃ ተሸፍነውና ተጣብቀው የሚያሳዩ ምስሎችና ቪዲዮዎችም ወጥተዋል።

'ወላጆቻቸውን ፍለጋ'

እንደሳውዘርን ሞርኒንግ ፖስት ዘገባ ከሆነ ልጆቹ "የስምንት ወይንም ዘጠኝ ዓመት" ታዳጊዎች ሲሆኑ የተገኙትም በጸጥታ ሃይሎች ነበር ።

አምስት ኪሎሜትር የተጓዙት በጣም ቁልቁለት በሆነ ቦታ ላይ ቢሆንም ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው መገኘታቸው ግርምትን ፈጥሯል።

"ህጻናቱ ሰውነታቸው ቀጭን በመሆኑ ቦታው ጥሩ የመደበቂያ ቦታ ሆኗቸዋል" ሲል አንድ ሠራተኛ ለጋዜጣው አስታውቋል።

ልጆቹ ጥያቄዎችን ለመመለስ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ቢገለጽም አንድ ሠራተኛ ለሳውዘርን ሞርኒንግ ፖስት "በመጨረሻም ልጆቹ እናትና አባታቸውን መናፈቃቸውን ለመረዳት ችለናል" በማለት ገልጿል።

"ከዕቃ መጫኛ ስር የተደበቁት ወላጆቻቸውን ለማግኘት ነው" ብሏል።

ጉዳዩ ለህጻናቱ ዘመዶች የተነገረ ሲሆን በዛው ቀን ምሽትም ወስደዋቸዋል ተብሏል።

"ልብ የሚነካ'

Image copyright SINA WEIBO

ጉዳዩ የቻይናን ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከማስደንገጥ አልፎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስለጉዳዩ ዌቦ በተሰኘው ማህበራዊ ሚዲያ ተወያይተዋል።

ምስሎቹ በስፋት የተሰራጩ ሲሆን ብዙዎችም 'ልብ የሚነካ' ሲሉ ገልጸውታል።

"በጣም ብዙ ብዙ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ተለያይተዋል። ማን ተንከባክቦ ችግራቸውን ይፈታላቸዋል?" ሲል አንዱ ጠይቋል።

ሌላው ደግሞ "ለማህበረሱሰቡ ከባድ ፈተና" ሲል የገለፀ ሲሆን "ከወላጆቻቸው ለተለያዩ ልጆች ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል" ያለም አለ።

ወላጆቻቸው ለሥራ ወደከተሞች ያቀኑባቸው በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ልጆች በቻይና የገጠር መንደሮች ይገኛሉ።

አንዳንዶች ከአያቶቻቸው ጋር ሲኖሩ ሌሎች ደግሞ በራሳቸው የሚኖሩ ናቸው። ሁለቱ ህጻናት ግን በአዳሪ ትምህርት ቤት የሚማሩ ናቸው።

'የቻይና ህልም መራራ ሆኗል'

Image copyright KEVIN FRAYER/GETTY IMAGES

ብዙ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የኮሙኒስት ፓርቲ ሃሳብ የሆነውና ግላዊና ብሄራዊ ዓላማዎችን ይዞ የተነሳውን "የቻይና ህልም" ተሳልቀውበታል።

ከእነዚህ ህልሞች መካከል አንዱ በ2020 ድህነትን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ነው። "ቻይና ዕድገት መሠረቱን ያደረገው በሚሰደዱ ሰራተኞች እና በሚበዘበዝ ጉልበታቸው ላይ ነው" የሚል አስተያት ከአንድ ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ቀርቧል።

ለእነዚህ ሁለት ታዳጊዎች "የቻይና ህልም መራራ ሆኗል" ብሏል ሌላኛው።

"የቻይና ህልም ማለት እነዚህ ህጻናትስ ፍላጎት ማለት አይደለም?" ሲሉ የጠየቁም አሉ።