ሰሜን ኮሪያ ትልቁን 'የባሌስቲክ' ሚሳኤል ሙከራዋን አደረገች

ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ሰሜን ኮሪያ የመጀመሪያውን ትልቁን የሚሳኤል ሙከራዋን ያደረገችው በሐምሌ ወር ነበር

ሰሜን ኮሪያ ሃገራትን አቋርጦ የመሻገር አቅም ያለውን ትልቁን የሚሳዔል ሙከራ በማድረጓ አለምን ላይ ስጋት ደቅናለች ሲሉ የአሜሪካ መከላከያ ፀሐፊ የሆኑት ጀምስ ማቲስ ገልፀዋል።

የሚሳኤል ሙከራው የተካሄደው እሮብ እለት ሲሆን የጃፓን ክልል የሆነው የውሃ አካል ላይ አርፏል።

4500 ኪሜትር ከፍ ብሎ 960 ኪሎ ሜትር የመጓዝ አቅም ያለው ሚሳኤል መሆኑንን የደቡብ ኮርያ መከላከያ አስታውቋል።

ይህ በቅርብ ጊዜ የተደረገ እና ውጥረቱን ከፍ ያደረገ የጦር መሳሪያ ሙከራ ነው።

ፒዮንግያንግ ከዚህ ቀደም የባሌስቲክ ሚሳኤል ሙከራዋን ያካሄደችው መስከረም ወር ላይ ነበር።

በዛው ወር ስድስተኛ የኒክውሌር ሙከራዋን አካሂዳ ነበር።

ሰሜን ኮሪያ የአለም መንግስታት ቢያወግዟትም ማዕቀብ ቢጣልባትም የኑክሌር ማበልፀግና የሚሳኤል ፕሮግራሟን ን ቀጥላበታለች።

የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አሁን የተደረገውን ሙከራ በማስመልከት አስቸኳይ ስብሰባ ሊያካሂድ ነው።

አጭር የምስል መግለጫ የአሜሪካ መከላከያ ፀሐፊ ፣ ጀምስ ማቲስ

ሚስተር ማቲስ የተወነጨፈው ሚሳኤል" እውነቱን ለመናገር ከዚህ በፊት ካስወነጨፉት ርቆ መሄድ የቻለ ነው" ብለዋል።

ሰሜን ኮሪያ " በየትኛውም የአለም ክፍል የሚገኝ ህዝብ ስጋት ላይ የሚጥል ባሌስቲክ ሚሳኤል እየገነባች ነው" ሲሉም አክለዋል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ሚሳኤሉ አየር ላይ እያለ ገና ስለሁኔታው ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ዋይት ሐውስ አስታውቋል። በማስከተልም "እንከታተለዋለን" ብለዋል።

መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉ እና ሁኔታው ያሳሰባቸው ሳይንቲስቶች ደግሞ ሚሳኤሉ ከ 13000 ኪሎ ሜትር በላይ መምዘግዘግ የሚችል ሲሆን "የአሜሪካ የትኛውም ግዛት ላይ መድረስ ይችላል" ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል።

የእሮብ እለቱ ሚሳኤል የተወነጨፈውከደቡብ ፒዮንግያንግ ግዛት ከሆነችው ፒዮንግሶንግ እንደሆነ የደቡብ ኮሪያ ዜና ኤጀንሲ ዮንሃፕ ዘግቧል።

የጃፓን ባለስልጣናት እንደገለፁት ደግሞ ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ሙከራዎች ሁሉ ሚሳኤሉ ተወንጭፎ 50 ደቂቃ ያህል ከተጓዘ በኋላ 250 ኪሎ ሜትር ላይ በሚገኘው ሰሜናዊ የባህር ዳርቻ አካባቢ አርፏል።

የአውሮጳ ህብረት የሰሜን ኮሪያ ሙከራ የአለም አቀፍ ግዴታዎችን "ህግን የተላለፈ ሙከራ" ያለው ሲሆን በተባበሩት መንግስታት የእንግሊዝ አምባሳደር ደግሞ "ሃላፊነት የጎነደለው ተግባር" ሲሉ ኮንነውታል።