'ገዳይ ጨረር' እንዴት ራዳርን ለመፈብረክ ረዳ?

የራዳር ስክሪን Image copyright Getty Images

በአየር ትራንስፖርት ላይ ላለን መተማመን በርካታ ፈጠራዎችን ልንጠቅስ እንችላለን፤ የአውሮፕላኑ ሞተር ወይም ራሱ አውሮፕላኑን ሊሆን ይችላል።

አንዳንድ ጊዜ ፈጠራዎችን ራሳቸውን በሙሉ አቅማቸው ለመጠቀም ሌላ ፈጠራ ያስፈልጋቸዋል።

የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ታሪክ የሚጀምረው በአውሮፓውያኑ 1935 ላይ ወደ ኋላ ተጉዞ ከገዳይ ጨረር መፈብረክ ወይም ከመሞከር ነው።

በእንግሊዝ ጦር ሚኒስቴር ውስጥ ከናዚ ጀርመን የቴክኖሎጂ እሽቅድምድም ጋር ወደኋላ የመቅረት ስጋት ነበር።

የዛን ጊዜ የገዳይ ጨረር ሃሳብ መስጧቸው ነበር፣ ይህንን ሃሳብ ይዞ ማዳበር ለቻለ የ1000 ፓውንድ ሽልማት አዘጋጁ፤ ነገር ግን ማንም ብቅ አላለም።

እንዲህ አይነት ተግባራዊ ጥናቶችን በገንዘብ መደጎም ያስፈልግ ይሆን? የገዳይ ጨረር ሃሳብ ራሱ ምን ያህል ርቀት ያስኬዳል?

Image copyright Sasha
አጭር የምስል መግለጫ ሃሪ ግሪንዴል ማቲያስ በ1923 ገዳይ ጨረር እየተባለ የሚታወቀውን የፈጠረ ነበር፤ ነገር ግን የፈጠራ ስራውን የብሪታኒያ መንግስት እንዲገዛው ማሳመን አልቻለም።

ይህንኑ ሃሳብ ለሬዲዮ ጣቢያ ምርምር ሰራተኛው ሮበርት ዋትሰን ዋት እንደዋዛ ሹክ አሉት።

ዋትም ለስራ ባልደረባው ስኪፕ ዊልኪንስ የሒሳብ ቀመር ጥያቄ አቀረበለት።

"ምናልባት፣እንደው ምናልባት ከመሬት 1 ኪሎ ሜትር ከፍ ብሎ በ37 ዲግሪ ሴንትግሬድ የሚሞቅ 4 ሊትር ያህል ውሃ ቢኖርህና አንተ ግን በ 40.5 ዲግሪ ሴንትግሬድ ያህል ማፍላት ብትፈልግ ከ 5 ኪሎ ሜትር ላይ ምን ያህል የሬዲዮ ፍሪኬዌንሲ ያስፈልግሃል?" ነበር ጥያቄው።

መልካም አጋጣሚ

ስኪፕ ዊልኪንስ ሞኝ አልነበረም።

4 ሊትር ውሃ በአንድ ጎልማሳ ውስጥ ያለ የደም መጠን ያህል መሆኑን ያውቃል።

37 ዲግሪ ሴንትግሬድ ደግሞ የአንድ ጤናማ ሰው የሙቀት መጠን ነው።

40.5 ደግሞ ህይወትን ሊያሳጣ ወይም ራሳችንን እንድንስት ማድረግ የሚችል የሙቀት መጠን ነው። በአውሮፕላን አብራሪው ክፍል ቢኖሩም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው የሚሆነው።

ስለዚህ ዊልኪንስ እና ዋትሰን ዋት ተግባብተዋል፤ ወዲያውም በጣም ብዙ ኃይል ይወስዳል በማለት ገዳይ ጨረሩ ተስፋ እንደሌለው ተስማሙ።

ነገር ግን ሌላ መልካም እድል ታይቷቸዋል።

የጦር ሚኒስቴሩ በእርግጠኝነት በዚህ ምርምር ላይ ሊያውለው የሚችለው ገንዘብ እንዳለው ያውቃሉ።

ዋትሰን ዋት እና ዊልኪንስ ሌላ ገንዘቡን የሚያወጡበት መንገድ ይጠቁሙ ይሆን?

ዊልኪንስ ከግምት ውስጥ አስገብቶታል። የራዲዮ ሞገድን በመጠቀም አውሮፕላኑ እይታ ውስጥ ሳይገባ መምጣቱን ማወቅ እንደሚችል ሃሳብ አቀረበ።

ዋት በአየር ሃይል ውስጥ በቅርቡ ለተቋቋመው ሳይንሳዊ ጥናቶችን ለሚያየው ኮሚቴ ማስታወሻ ፃፈ። እንዲህ ያለው ሃሳብን ተቀብለው ለማስተናገድ ይፈቅዱ ይሆን? በርግጥም ይፈቅዳሉ።

ስኪፕ ዊልኪንስ የገለፀው ነገር ዛሬ ራዳር ብለን የምንጠራው ሆነ።

ሮበርት ቡድሪ አለምን ስለቀየሩ የፈጠራ ግኝቶች ባብራራበት መፅሐፉ ጀርመኖች፣ ጃፓኖች እና አሜሪካኖች በተናጠል መስራት መጀመራቸውን አስፍሯል።

አስደናቂ ግኝት

በ1940 እንግሊዝ የራዳር ማስተላለፊያ ግኝትን በማግኘት ቀዳሚ ሆነች።

በናዚ ቦንብ የሚደበደቡት የእንግሊዝ ፋብሪካዎች የራዳር ማስተላለፊያውን ለማምረት ስለተቸገሩ የአሜሪካ ፋብሪካዎች አመረቱት።

ለወራት የእንግሊዝ ባለስልጣናት መሳሪያውን አሜሪካውያን በሌላ ቦታ ያላቸውን ሚስጥር እንዲያካፍሏቸው እንደመደራረደሪያ ተጠቀሙበት።

ከዛም ዊንስተን ቸርችል ስልጣን ላይ ወጡ፤ በዛ አስቸጋሪ ወቅት ያንን ከባድ ውሳኔ አሳለፉ።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊኒስተን ቸርችል ብሪታኒያ የራዳር ጥናቷን ከአሜሪካ ጋር እንድትጋራ ወሰኑ

ያልተጠበቀው ግኝት

በማንኛውም ሁኔታ፣ በማያሻማ መልኩ የኤም አይ ቲ ጨረራ ቤተ-ሙከራ (ቀዩ ቤተ-ሙከራ) ውጤታማ ነበር።

10 ኖቤል ሎሬቶችን አፍርቷል። በቤተ ሙከራው የተሰሩት ራዳሮች፣ አውሮፕላኖችን እና ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን ለመለየት እንዲሁም ጦርነቱን ለማሸነፍ አግዘዋል።

ነገር ግን በጦርነት ወቅት ያለው ጥድፊያ በሰላም ወቅት ሊጠፋ ይችላል።

የመንገደኛ አውሮፕላኖችም በፍጥነት ማደጋቸው እንዳለ ሆኖ ራዳር እንደሚያስፈልግ የተገለጠ እውነት ሆነ።

በ1945 በጦርነቱ ማብቂያ ወቅት የአሜሪካ የመንገደኛ አውሮፕላኖች ሰባት ሚሊየን መንገደኞችን አጓጉዘው ነበር።

በ1955 ይህ ቁጥር ወደ 38 ሚሊየን አደገ።

ሰማዩ በአውሮፕላኖች ፍሰት ሲጨናነቅ ግጭቶችን ለማስወገድ ራዳር ወሳኝ ሆነ።

ነገር ግን ምርቱ በጣም ዘገምተኛ እና የተዝረከረከ ሆነ። አንዳንድ አየር መንገዶች ራዳር የገጠሙ ሲሆን ሌሎቹ ግን ገና ነበሩ።

በበርካታ የአየር ክልሎች አውሮፕላኖች ጭራሹኑ ክትትል አይደረግባቸውም ነበር። አውሮፕላን አብራሪዎች እቅዳቸውን አስቀድመው ያስገባሉ፤ በመርህ ደረጃ በነሱ የበረረ መስመር ሌላ አውሮፕላን እንዳይበር ለማድረግ ይረዳል።

ነገር ግን ግጭትን ለማስወገድ "እይ፣ በእይታ ውስጥ ሁን።" በሚል መርህ ብቻ የተወሰነ ሆነ።

ሰቅጣጭ ግጭት

በአውሮፓውያኑ ሰኔ 30 1956 ሁለት መንገደኞች የሎስ አንጀለሱን አየር መንገድ ለቀው ሄዱ፤ አንዱ ወደ ካንሳስ ሌላኛው ወደ ቺካጎ ነበር የሚበሩት።

የበረራ መስመራቸው የአንደኛው የሌላኛውን የሚያቋርጥ ቢሆንም ከፍታቸው ግን የተለያየ ነበር።

ሆኖም በመንገዳቸው ላይ መብረቅ ያዘለ ደመና በመፈጠሩ የአንደኛው አውሮፕላን አብራሪ ከደመናው በላይ ከፍ ብሎ ለመብረር ፍቃድ ጠየቀ።

የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪው ከደመናው በላይ 1000 ጫማ ከፍታ ላይ እንዲበር ፍቃድ ሰጠው። "እይ፣ በእይታ ውስጥ ሁን።" በሚል

በወቅቱ ምን እንደተከሰተ ማንም በርግጠኝነት መናገር አልቻለም፤ ያኔ ደግሞ አውሮፕላኖች የበረራውን ምልልስ ቀርፆ የሚያስቀር ጥቁሩ ሳጥን ካለመኖሩ በተጨማሪ ለወሬ ነጋሪም የተረፈ አልነበረም።

ከ4፡31 በኋላ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪው የሚንተፋተፍ "እየገባን ነው፤ ወደላይ ሳብ" የሚል የሬዲዮ ምልልስ ሰምቷል።

ስብርባሪያቸው በሸለቆው ወለል ላይ ተበታትኖ ሲገኝ አውሮፕላኖቹ በ25 ዲግሪ በደመና ውስጥ ተገናኝተው ሊሆን እንደሚችል መላምት ተሰጥቶ ነበር።

ምርመራውን ያካሄዱ አካላት ሁለቱም አብራሪዎች በደመና ውስጥ መንገድ በመፈለግ ተጠምደው መንገደኞች ደግሞ የደመናውን ውበት እያደነቁ ይበሩ እንደነበር ጠርጥረዋል።

ይህንንም ተከትሎ በሁለት አመት ውስጥ አሁን የፌደራል አቪየሽን ቦርድ የሚባለው በአሜሪካ ተቋቋመ።

አሁን የአሜሪካ ሰማይ 20 እጥፍ ያህል ባተሌ ሆኗል።

በዓለም ግዙፍ አውሮፕላን መንገዶች በደቂቃ ውስጥ የሚያርፉ እና የሚነሱ አውሮፕላኖች ብዛት በሁለት እጥፍ አድጓል።

ምንም አይነት ደመና ቢሆን ግጭቶች ኢምንት በሚባል መልኩ ቀንሰዋል።

ለበርካታ ነገሮች ምስጋና ይግባቸው፤ በይበልጥ ደግሞ ለራዳር።