ጥበብን በወር-አበባና በአጽም

በወር አበባ ደም የሳለቻቸው የምህረት ስራዎች

የወር አበባ ደም እንደ ፀያፍና ነውር ተደርጎ በሚታይበት ሀገር ታዋቂዋ ሰዓሊ ምህረት ከበደ በወር አበባዋ የሳለችው ስዕል አነጋጋሪና ጥያቄንም ፈጥሯል።

ይህ ፕሮጀክቷ ለሁለት አመታት እንደቆየ የምትናገረው ምህረት የወር አበባዋንም በመጠቀም ስዕሎቿን እንደሳለች ትናገራለች።

የወር አበባ ከቆሻሻነትና እርግማን ጋር እንደሚያያዝ የምትናገረው ምህረት በአጠቃላይ መወገድ ያለበትና አላስፈላጊም ነገር ተደርጎ ይታያል ትላለች።

" የወር አበባ ቆሻሻ ወይም እርግማን ከሆነ የሰው ልጅ እዚህ የመጣበትን ሂደት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል" ትላለች።

"ሀሳቤን ብቻ ሳይሆን እኔነቴም የሰፈነበት ስራ ነው" በማለት ምህረት ትናገራለች።

በአጠቃላይ ፕሮጀክቷ አባታዊ ስርዓት (ፓትርያርካል) በሆነው አለም ላይ ሴት መሆን ምን ማለት ነው የሚል አንድምታ እንዳለው ትናገራለች።

"የወር አበባ ደሜን መጠቀሜ በራሴ መልዕክት አለው" በማለት የምትናገረው ምህረት " ሴቶች በዚህ ስርአት ላይ እንዴት ነው የሚኖሩት፤ በምንስ መንገድ ነው የሚታዩት? ለሚሉት ጥያቄዎችም በታሪክ ውስጥ ምንም አይነት ሚና እንደሌለን ተደርገን ነው የምንታየው። ይሄም ስራየ ለነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ይሞክራል" ትላለች።

በማህበረሰቡ ውስጥ የወር አበባ ደም የሚታይበትን መንገድም ለመቀየርም ስትነሳ ፈታኝ እንደሆነ ከመጀመሪያው ተሰምቷታል።

"በሃገራችን የወር አበባ ደም የምታይ ሴት የዕምነት ቦታዎች ላይ መገኘት እንደሌለባት ማህበረሰቡ ያስባል። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ የወር አበባ ደም እያዩ ያሉ ሴቶች"ንፁህ" እስኪሆኑ ከማህበረሰቡ ተነጥለው ለብቻቸው የሚቆዩበት ሁኔታም አለ።" የምትለው ምህረት የሷም አስተዳደግ በዚህ ተፅእኖ ስር መሆኑ "ሴት ማለት ምንድን ናት" የሚለውን ጥያቄ በተደጋጋሚ እንድትጠይቅ አድርጓታል።

"ወላድነት" (ፈርቲሊቲ) የሚለው ሀሳብ በዚህ ጥበብ ስራዋ ዋና ማዕከል ሲሆን የጥበብ ስራውም አቀራራረብ በትልቅ ሰሀን ውስጥ አፈር ሞልታ፣ እንቁላል እንዲሁም በወር አበባ ደም የተሳሉ 40 ስዕሎቿን አሳይታለች።

ይህንንም ስራዋን በሞደርን አርት ሙዚየም ገብረ-ክርስቶስ ደስታ ማዕከል 'ፋና ወጊ' በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን በዚህ አውደ ርዕይም ላይ የሌሎችም አርቲስቶች ስራዎች አብሮ ቀርቧል።

ይህ ስራዋ ቀለል ተደርጎ አልታየም ብዙ ያውቃሉ ብላ በምትጠብቃቸው ወንድ አርቲስቶች መካከል ራሱ "ለምን እጇን ትጨብጠዋለህ? የሚሉ አስተያየቶች መምጣታቸው ማህበረሰቡ ውስጥ ስር ሰዶ የገባውን "ንፁህ አለመሆን" የሚለውን ሃሳብ በግልፅ ያሳየኝ ነው" ትላለች።

የምህረት ብቻ ሳይሆን በዚሁ አውደ-ርዕይ ላይ ስራዋን አቅርባ የነበረው ሄለን ዘሩም በእናቷ አፅም የሰራችው የጥበብ ስራ አነጋጋሪ ነበር።

"ይከሰሱ" የሚሉ ወሬዎችም እንደነበሩ ሁለቱም ይናገራሉ።

የሁለቱም ሰዓሊዎች ስራዎች የተከተሉት ዘይቤ በአለም ላይ በአሁኑ ዘንድ ታዋቂነትን እያተረፈ ያለውን 'ፐርፎርማንስ አርት' ወይም ሰውነትን ወይም የሰውነትን አካል እንደ አንድ የጥበብ መሳሪያ አድርጎ መጠቀም ማለት ነው።

ከተለመደው የስዕል ጥበብ በመውጣትም የማሀበረሰቡን እሳቤ፣የተለያዩ ርዕዮተ አለማትንም ሆነ ሌሎች ሀሳቦችን ማህበረሰቡንም በቀጥታ በሚያሳትፍ መልኩ በአርቲስቶች የሚሰራ የጥበብ አይነት ነው።

ከነዚህም ውስጥ የሚያስደነግጡና የሚሰቀጥጡ ስራዎችም በዓለም ላይ ታይተዋል።

ከጥቂት አመታት በፊት በሩሲያው አርቲስት ፔትር ፓቭልንስኪ ሩሲያ ውስጥ ያለውን ጭቆና ለማሳየት ብልቱን ከወለሉ ጋር ማጣበቁ ለብዙዎች ከሰቅጣጭም በላይ ነው።

ከጥቂት አመታት በፊት ነበር አዲስ አበባን መልሶ በማልማት ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን መቃብር የተቀበሩ ሰዎችንም ቆፍረው እንዲያወጡ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ትዕዛዝ የመጣው።

ይሄም ሁኔታ በብዙዎች ዘንድ አሳዛኝ ትዝታዎችን እንዲሁም የተረሱ ሀዘኖችን ቀስቅሷል።

በዚሁም አጋጣሚ ነው ሄለን ዘሩ የእናቷንም መቃብር አውጥታ ወደ ሌላ ቦታ እንድትቀብር የተነገራት።

እናቷን በህፃንነቷ ብታጣም መቃብሯን እየተመላለሰች እንዳላየች ሄለን ትናገራለች።

እናቷም ከሞተች ከአስራ አምስት አመታት በኋላ ወደ መቃብሯ መመለስ ብቻ ሳይሆን አፅሟን አውጥቶ መቅበር የሷ ኃላፊነት ነበር።

ቁፋሮው ሲጀመር ቀላል እንዳልነበር የምትናገረው ሄለን " የየቀኑ ትግልም ነበር" ትላለች

ሁኔታው ከአዕምሮዋ ከምታስበው በላይ ስለነበር መቀበልም ከብዷት ነበር።

ሁኔታውንም ቀለል ለማድረግ ከቁፋሮው ጀምሮ መቅረፅ ጀመረች። በዚህም አጋጣሚ ነው ይህንን ማሰብ የሚከብድ ጉዳይ ወደ ጥበብ ስራዎች ለመቀየር ያሰበችው።

የመጀመሪያው ከቁፋሮው ጀምሮ እስከተቀበሩበት ደብረ-ዳሞ ገዳም ያለውን ጉዞ በቪዲዮ የመቅረፅ ስራ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከልጅነት ትዝታዎቿ በመቀንጨብ ወደ ጥበብ ስራ የቀየረችው ነው።

በዚህም ስራዋ እንደ ሬሳ ተገንዛ እናቷ ከ15 አመት በላይ በቆየችበት የመቃብር ስፍራ ውስጥ ትተተኛለች እንዲሁም ትንቀሳቀሳለች።

የመቃብር ስፍራውም በቀይ ዣንጥላ ተከቦ ነበር።

ቀይ ዣንጥላ እንደ ምልክትነት እንደተጠቀመችው የምትናገረው ሄለን "እናቴ ከመሞቷ በፊት ከሆስፒታል ስትመጣ ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁዋት ቀይ ዣንጥላ ይዛ ነበር" ትላለች።

ይህ "የልብ ስብራት" የፈጠረባትን ሂደትም የጥበብ ስራዋ ቀለል እንዳደረገላት ትናገራለች።

"የእናቴ መቃብር ሲከፈት ሀዘኑም እንደገና አገረሸ። በምን መንገድ ነው እንደገና የናቴን ቀብር ማየቱ ለኔ ብቻ ሳይሆን በጊዜው የሚወዷቸውን ሰዎች መቃብር አንሱ ለተባሉት የሚነካ ጉዳይ ነው" ትላለች።

ይህንን ጥልቅ ስሜት በስዕልም ሆነ በተለመዱ የጥበብ አይነቶች ማሳየቱ በቂ ስላልነበር ይህንን ዘዴ እንደመረጠች ትናገራለች።

በአውደ-ርዕዩ ላይም 15 ሜትር በከሰል የሳለችው ስዕል እንዲሁም 'ፐርፎርማንስ ጥበብ' (ትርኢት) ያሳየችበት ቪዲዮና፣ ሌላኛው እስከ ደብረዳሞ ቀብር ድረስ የነበረው ቪዲዮ ደግሞ በሬሳ ሳጥኑ መሰረት ዲዛይን የተደረገ ሳጥን ውስጥ ታይተዋል።

በተለይ ሳጥኑ የመቃብር አይነት ዲዛይን ስለነበረው ለብዙዎች ከፍተኛ የስሜት መናወጥ እንደፈጠረ ሄለን አልደበቀችም።

" በጣም የተደናገጡና ብዙዎችም አልቅሰዋል" ትላለች።

ሁለቱም አርቲስቶች የጥበብ ገደብ የለውም ብለው የሚያምኑ ሲሆን የፐርፎርማንስ ጥበብም በቀጥታ ከተመልካቹ ጋር እንዲገናኙ ዕድል እንደሰጣቸው ይናገራሉ።

ተያያዥ ርዕሶች