ስደተኛው የፊልም ባለሙያ

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
"መጪው ትውልድ ከእኛ ምን ይወርሳል? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን።"

አባቱ በፖለቲካ ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ ምክንያት ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት በመሸሽ ነበር ገመዶና ቤተሰቡ ሃገር ጥለው የተሰደዱት። የመጀመሪያ መዳረሻቸው ኬንያ ነበረች፤ ለጥቆም ኡጋንዳ፤ በስተመጨረሻም አሁን ያሉበት የኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ከተሙ።

ጅማሮ

ወጣቱ ፊልም ሰሪ ገመዶ ጀማል ከልጅነቱ ጀምሮ ለኪነጥበብ በተለይም ለስዕል ትልቅ ፍቅር እንደነበረው ይናገራል።

"በማሕበረሰባችን ውስጥ ያለውን የፊልም ጥበብ ክፍተት ለመሙላት በማሰብ ነው የጀመርኩት"ይላል ወደ ፊልም ዓለም የገባበትን ምክንያት ሲያስረዳ።

የካሜራ ጥበብ፣ የምስል እና ድምፅ አርትኦት፣ እንዲሁም የአዘጋጅነት ሙያዎችን ኖርዌይ በሚገኝ የስነጥበብ ትምህርት ቤት በመግባት ቀስሟል።

"ቤተሰቦቼ በጣም ያበረታቱኝ ነበር" የሚለው ወጣቱ ገመዶ በተለይ አባቱ ፍላጎቱን ከሁሉም በተለየ ይደግፉለት እንደነበረ ያስታውሳል።

"ለሕዝቤ በታማኝነት እንድሠራ ይመክረኝ ነበር። 'ላመንክበት ነገር ብቻህን እንኳን ብትቆም ከዳር አድርሰው' ይለኛል" በማለት የአባቱን ምክር ያስታውሳል።

Image copyright GAMMADO JAMAL

ጥበብ በስደት በራስ ቋንቋ

"ኦሮምኛ ፊልም ለመሥራት ፈልጌ በርካታ መሣሪያዎች እንዲሁም ዕውቀት ቢኖረኝም ትልቁ ፈተና የሆነብኝ በኦሮምኛ የሚተውኑ ተዋንያንን ማግኘት ነው" ባይ ነው።

በአንድ ወቅት ቀረፃ በመጨረሻቸው ወቅት አንድ ተዋናይ አቋርጦ መሄዱን አስታውሶ "በዚህም የተነሳ ፊልሙን ዳግመኛ እንደ አዲስ ለመቅረፅ ተገደን እንደነበር አልረሳም" ይላል።

ይህ መሰናከል ባይሆንበት ኖሮ እስከዛሬ ድረስ ብዙ ፊልሞችን መሥራት ይችል እንደነበር ይናገራል።

ይህንንና መሰል ውጣ ውረዶችን በፅናት በማለፍ እስካሁን ስድስት የኦሮምኛ ፊልሞችን እና በርካታ የሙዚቃ ቪዲዮዎችን ለመሥራት ችሏል።

ከነዚህም ውስጥ 'አማና' እና 'ጨባሳ' የተሰኙትን ፊልሞች በበርካታ ተመልካቾች እንደወደዱለት ይናገራል። አብዛኛዎቹ የገመዶ ፊልሞች የሚያጠነጥኑት በወቅታዊ የኦሮሞ ሕዝብ ጉዳዮች ላይ ሲሆን ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስሳል።

ከዚህም ባሻገር ገመዶ የፊልም አሰራር ጥበብን የተመለከቱ አጫጭር የቪዲዮ ትምህርቶችን በኦሮምኛ ቋንቋ ድረ-ገፆች ላይ ይጭናል። የሚሰጣቸው ትምህርቶች የፎቶ አነሳስ ጥበብ፣ የፊልም ቀረፃ እና አርትኦት ላይ ያተኩራሉ።

ወደጥበቡ መግባት ለሚፈልጉ የኦሮሞ ወጣቶች እንደመንደርደሪያ ሊያገለገላቸው እንደሚችል ገመዶ ይናገራል።

Image copyright GAMMADO JAMAL
አጭር የምስል መግለጫ '' ላመንክበት ነገር ብቻህን እንኳ ብትቆም ከዳር አድርሰው''

ወደፊት. . . ?

ቢሳካልኝ ወደ ሃገር ቤት ተመልሼ ጥበብን ማሳደግ እፈልጋለሁ የሚለው ገመዶ "ሃገር ቤት ያሉ የጥበብ ሰዎችን በሁሉም በኩል ማገዝ እፈልጋለሁ" ይላል።

"ትናንት ዛሬ አይደለም ዛሬ ደግሞ ነገን አይሆንም" የሚለው ገመዶ የኦሮሞ ሕዝብ ኪነ-ጥበብ አሁን እያደገ እንደሆነ ይናገራል።

በተለያዩ ቋንቋዎች ከሚሰሩ ፊልሞች አንፃር ካየነው ግን አድጓል ለማለት አያስደፍርም ሲል ያትታል ገመዶ።

ገመዶ አሁን ላይ አዲስ የኦሮምኛ ፊልም እያዘጋጀ መሆኑን ነግሮናል። "ይሀ ፊልም ከዚህ በፊት ከሠራኋቸው ፊልሞች አንድ ደረጃ ከፍ ያለ እንዲሆን ስለምፈልግ በጥሩ መንገድ እየሠራሁት ነው" በማለት ይገልፃል።

Image copyright GAMMADO JAMAL

የአምሮ ነፃነት

"በሰው ሃገር በአዕምሮ ባርያ ትሆናለህ ነገር ግን አዕምሮህን ተጠቅመህ ደግሞ ነፃ መውጣት ትችላለህ" የሚለው ገመዶ " የሰው ልጅ ምድር ላይ ሲኖር ሰላም እና ነፃነት ያስፈልጉታል" ሲል ያምናል።

ገመዶ አሁን በሚገኝባት የኖርዌይዋ ኦስሎ ከተማ በነፃነት ይኑር እንጂ ሃገሩን መናፈቁ እንዳለቀረ ይናገራል። "የራስ ሃገር ሁሌም እናት ነች፤ በሰው ሃገር አገኘሁ የምለው ነገር 'ስደተኛ' በሚል ስም መጠራት ብቻ ነው።"

ገመዶ መቼ ይሆን ሃገሬ የምገባው ዛሬ?. . . ወይስ ነገ? ሲል ይተክዛል። አንድ ቀን ግን እንደሚሳካለት ተስፋ ያደርጋል።

ተያያዥ ርዕሶች