የሕወሓት ግምገማና እርምጃ ወዴት ያመራ ይሆን?

የሕወሓት አርማ Image copyright FACEBOOK

ለረጅም ጊዜ ሲካሄድ የሰነበተው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ከሃላፊነታቸው በተነሱትና በተጓደሉት የፓርቲው መሪና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ቦታ ላይ ሽግሽግ በማድረግ ተጠናቋል።

በስፋት ሲነገር እንደነበረው ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል የድርጅቱ ሊቀመንበር፣ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር ምክትል ሊቀመንበር እንዲሆኑ ተወስኗል።

በተጨማሪም አቶ አስመላሽ ወ/ሥላሴ፣ ዶ/ር አብረሃም ተከስተ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ እና ወ/ሮ ኬርያ ኢብራሂም የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ሆነዋል።

ከሌላው ጊዜ በተለየ ለሁለት ወራት ያህል ሲገማገም የቆየው ሕወሓት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ድርጅቱ "ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብና አሠራር እንደወረረው፤ የተማረ ወጣት ኃይል አለማካተቱን እንዲሁም እርስበርሱ በመጠቃቃት እንደተጠመደ" አምኗል።

በተጨማሪም የተጠበቀውን ያህል ልማትና ዕድገት አለማስመዝገቡና መሰል ጉድለቶች መታየታቸውን መግለጫው ያትታል።

ድርጅቱ መሰል ትችቶችን የሚያንፀባርቁ መግለጫዎችን ሲያወጣ የመጀመሪያው አይደለም።

ለመጨረሻ ጊዜ ያወጣው መግለጫም ከዚህ በፊቶቹ የተለየ አንድምታ ያለው አልነበረም።

ነገር ግን ባለፈው ሰኞ አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳሳወቀው የድርጅቱ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አባይ ወልዱና አቶ በየነ ምክሩ ከሥራ አስፈፃሚ አባልነታቸው ተነስተው በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲያገለግሉ ውሳኔ ሰጥቷል።

የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ አባል የነበሩት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ደግሞ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው ታግደው እንዲቆዩ መወሰኑም ታውቋል።

ከዚህም በተጨማሪ ድርጅቱ ሁለት ስማቸው በይፋ ላልተገለፀ የሥራ አስፈፃሚ አባላት ማስጠንቀቂያ መስጠቱንም አስታውቋል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው በቀሪ አባላቱ ላይ የሚያካሂደው ሂስና ግለ-ሂስ ቀጥሎም ስብሰባውን አጠናቋል።

Image copyright TPLF OFFICIAL FB

"የዘገየ እርምጃ"

የድርጅቱ የቀድሞ አባልና የአየር ኃይል አዛዥ የነበሩት ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሃገሪቱ ውስጥ የተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ እልባት ያገኝ ዘንድ ኢህአዴግን የመሠረቱ ድርጅቶች የሚጨበጥ የፖለቲካ ለውጥና የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለባቸው በተለያየ ጊዜ ይገልፁ እንደነበር ይታወሳል።

ኦህዴድ ያደረገውን የአመራር ለውጥ አድንቀው ሕወሓትና ብአዴን ግን አስፈላጊውን ግምገማና ማሻሻያ ሳያደርጉ ቆይተዋል ሲሉ ይተቻሉ።

"ማዕከላዊ ኮሚቴው የወሰደው እርምጃ ቢያንስ ከሁለት ዓመት በፊት መሆን የነበረበትና የዘገየ ነው" በማለት ለቢቢሲ ይናገራሉ።

"አዳዲስ ወጣቶች ወደ ድርጅቱ የሚመጡ ከሆነ ትልቅ የለውጥ ምልክት ነው፤ ድርጅቱ ወዴት እንደሚሄድም አመላካች ነው" ባይ ናቸው ጄኔራሉ።

"ጉድለታቸውን ማመናቸው አንድ ነገር ነው። ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ ፀረ-ዲሞከራሲያዊ አስተሳሰብ እንዴት እንደሚወጡ መፍትሄ አበጅተዋል ወይ? የሚለው ነው" ሲሉ ይጠይቃሉ።

የቀድሞ የድርጅቱ አመራር የነበሩትና በ1993 ዓ.ም. ለሁለት ሲሰነጠቅ የተገለሉት አቶ ገብሩ አሥራት "ማዕከላዊ ኮሚቴው የወሰደው እርምጃ በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል የተፈጠረውን ክፍተት ማሳያ እንጂ የለውጥ ምልክት አይደለም" ይላሉ።

"እርምጃው የሕዝቡን በተለይ ደግሞ የወጣቱን ጥያቄ ያልመለሰ ነው" ሲሉም ያስረግጣሉ።

ከዚህ በፊት እርሳቸውን ጨምሮ በርካቶች ሲባረሩ የቀደሞው የድርጅቱ ሊቀ-መንበር መለስ 'ሙስና' እና 'ፀረ-ዲሞከራሲ' የመሳሰሉ አጀንዳዎችን ተጠቅመው እንደነበር የሚያወሱት አቶ ገብሩ፤ አሁንም 'ፀረ-ዲሞከራሲ' የሚለው ስያሜ የተወሰኑ ሰዎችን ለመምታት የተሸረበ እንደሆነ ያምናሉ።

"ለምልክት እንኳን የሚሆን ለውጥ አልታየም። የሥልጣን ሽኩቻ መሆኑን የሚያሳየው ነገር ደግሞ ግልፅ የሆነ ለሃገርና ለህዝብ የሚጠቅም አጀንዳ እንኳን አልተነሳም" ይላሉ።

Image copyright TPLF OFFICIAL FB

ወዴት ወዴት. . . ?

ጄኔራል አበበ ከአቶ ገብሩ በተለየ ቢዘገይም ድርጅቱ ራሱን ካደሰ በሃገሪቱ ውስጥ የሚታዩ የተወሳሰቡ ቀውሶች መፍትሄ ይገኝላቸዋል ብለው ያምናሉ።

ጄኔራሉ "ምናልባት ድርጅቱ ለህዝብ ሲታገሉ የቆዩ ወጣቶችን ማካተት ከቻለ ለውጥ ይመጣል" የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።

ድርጅቱ ውስጥ ያሉም ይሁን ውጭ ያሉ ወጣቶች ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ያሰምራሉ ጄኔራል አበበ።

ምሁራንና ወጣቶችን ወደ ድርጅቱ ማምጣት ከተቻለ ቢያንስ በግማሽ ያህል እንኳን መዋቅራዊ ለውጥ እንደሚቻል ይናገራሉ።

"አረንቋ ውስጥ ነው ያሉት"

"ከሁለት ወይም ከሦስት ሰዎች ውጪ በሥራ አስፈፃሚው ውስጥ ንፁህ አባል የለም" ይላሉ ጄኔራል አበበ። "ጭቃ ውስጥ ነው ያሉት። ከዚህ ጭቃ መውጣት ይችላሉ ወይ?" በማለት ይጠይቃሉ።

የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለም መብራህቱ በበኩላቸው "ድርጅቱ ውስጥ እየተከናወነ ያለው ትግል የተሻለ ነገር ለማምጣት ነው" ሲሉ ይናገራሉ።

"የመጠቃቃት ሳይሆን የመገማገምና መስመርን የማጥራት ሥራ ነው እየተሠራ ያለው" ብለውም ያምናሉ።

"አሁንም ብዙ አቅም ያለው አመራር አለ፤ ጠንካራና ቅን ወጣቶች ከድርጅቱ ሸሽተዋል ብዬ አላምንም" ባይ ናቸው።

ከዶክተሩ ሃሳብ ሌላ ጫፍ የሚገኙት ጄኔራል አበበ አሁን ያለውን አመራር "የበሰበሰ" እና "ሐሳብ የማያመነጭ" ሲሉ ይገልፁታል። "ድርጅቱ አሁን ባለው አቅም ችግር መፍታት አይችልም" ሲሉ ይደመድማሉ።

የህወሓት የሥራ አስፈፃሚ አባላት እነማን ናቸው

ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል

በትግራይ ሽረ ወረዳ የተወለዱት ዶ/ር ደበረፅዮን ከልጅነታቸው ጀምሮ በጣም ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩ መረጃዎች ያመላክታሉ። አራት ነጥብ ይዘው ወደ አዲስ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተቀላቀሉበት በአጭር ጊዜ ትመህርታቸውን አቋርጠው ነበር ወደ ትጥቅ ትግሉ ያመሩት።

ከዝያም በድርጅቱ ወደ ጣልያን አገር ተልከው በመገኛኛ ቴክኖሎጂ ስልጠና የወሰዱ ሲሆን፤ በ1972 ዓ/ም የድርጅቱ ሬድዮ ጣብያ "ድምፂ ወያነ ትግራይ" በማቋቋም ግንባር ቀደም ተዋናይ እንደነበሩ ይነገራል።

በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት መረጃ ሰንሰለት ሰብረው በመግባትና በማክሸፍ ይታወቃሉ። እንዲሁም ደግሞ በድርጅቱ "ባዶ ሽድሽተ" በመባል የሚታወቀው የድርጅቱ የደህንነት ክፍልም ውስጥ አገልግለዋል።

ግንቦት 20/1983 ዓ.ም. ኢህአዴግ ስልጣን በተረከበበት የደህንነት መ/ቤቱን ይመሩ የነበሩት የአቶ ክንፈ ገ/መድህን ምክትል ሆነውም አገልግሏል።

ቀደም ሲል ያቋረጡትን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ተከታትለው የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተቀብለዋል።

እንዲሁም ደግሞ የዶክትሬት ድግሪያቸው ከታዋቂው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ለንደን ያገኙ ሲሆን፤ በርካታ ፅሁፎቹን በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ማሳተማቸው ይነገራል።

በስማቸው የሚታወቅ የሶፍትዌር የፈጠራ ባለመብት ሲሆኑ፤ ሶፍትዌሩ በኣማዞን የኤሌክትሮኒክ ሽያጭ መረብ ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል። ።

በ1993 ዓ/ም በድርጀቱ ውስጥ በተፈጠረ መሰነጣጠቅ፤ የተሸነፊው ቡድንን ሃሳብ አራምደሃል ተብለው ወደ ወረዳ አስተዳደር ዝቅ ብለው እንዲሰሩ መደረጋቸው ይነገራል።

ሆኖም ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የኢንፎርሜሽንና ኮሙንኬሽን ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ፤ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የክላስተር አስተባባሪ ሆነውም ሰርተዋል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ማስተባበርያ ብሔራዊ ም/ቤት ሰብሰቢም ናቸው።

አሁን ሊቀመንበር ሆነው ከመሾማቸው በፊት ድርጅቱን በምክትል ሊቀመንበርነት ሲመሩት ቆይተዋል። ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው 12ኛ ጉባኤ ላይም የጉባኤተኛው ከፍተኛውን ድምፅ ያገኙ ሲሆን የድርጅቱ ሊቀመንበር ይሆናሉ የሚል ግምት ተስጥቷቸው ነበር።

አቶ ጌታቸው ረዳ

በ1965 በአላማጣ ከተማ የተወለዱት አቶ ጌታቸው ረዳ ካሕሳይ፤ በ"ታዳጊዋ ኢትዮጵያ" ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።፥

በ1990 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከህግ የትምህርት ክፍል የተመረቁት አቶ ጌታቸው፤ ከሌላ አሜሪካዊው ዜጋ በመሆን የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የህግ ፋኩልቲ መስራች ናቸው። ከዚያም የህግ አስተማሪ ሆነው ሰርተዋል። በትምህርታቸው በአሜሪካ የሚገኘው አላባማ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ውጤት ሁለተኛ ድግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፤ ቅርበት ያለቸው ሰው ለቢቢሲ እንደገለፀፁልን ተቋሙ የክብር ዶክተርትም ሰጥቷቸዋል።

አቶ ጌታቸው በ1997 ዓ/ም ምርጫ ማግስት ከፍተኛ ተነባቢ በነበረው በአዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ በሚያቀርቧቸው መከራከርያ ሓሰባቦችና ፅሁፎች ብዙዎቹ ያስታውሷቸዋል።

ከዚያም ቀጥሎ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርን የተቀላቀሉ ሲሆን፤ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ እና ኮምኒኬሽንስ ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር ጀነራል ሆነው ሰርተዋል። እንዲሁም ደግሞ 'ኤ ዊክ ኢን ዘ ሆርን' በመባል የሚታወቀው የመስሪያ ቤቱ ድረ ገፅ አዘጋጅና ፀሃፊ ነበሩ።

አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ውጭ ጉዳይና ምክትል ጠ/ሚኒስተር ሆነው በተመረጡበት ወቅት ልዩ አማካሪያቸው ሆነው የሰሩ ሲሆን፤ ጠ/ሚኒሰትር ሲሆኑ ደግሞ የእሳቸው ልዩ አማካሪ ሆነው መሾማቸው ይታውሳል።

ቀጥለውም የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው የተሾሙ ለሁለት ዓመት ተቋሙን መርተዋል። በአሁኑ ወቅት የህግ ማሻሻያ ተቋምን በዳይሬክተርነት ይመራሉ።

አቶ ጌታቸው በአሁኑ ወቅት በትጥቅ ትግሉ ያልተሳተፉ የሥራ አስፈፃሚ አባል ከሆኑት ጥቂቶች መካከል አንዱ ናቸው።

ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር (መንጀሪኖ)

በውጊያና በፖለቲካ ኣቋማቸው በስፋት ከሚታወቁት ሴት ታጋዮች መካከል አንዷ ናቸው። የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በኤርትራ መንደፈራና አስመራ ከተሞች "እንዳደናግል" የጣልያን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

ወ/ሮ ፈትለ ወርቅ በትምህርታቸው ጎበዝና ተሸላሚ ተማሪ እንደነበሩ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ወንደማቸው ይናገራሉ። በ1967 ዓ/ም ወደ ዓድዋ በማምራት የዘጠነኛ ክፍል በንግስተ ሳባ ትምህርት ቤት በመከታተል ላይ ሳሉት ነበር ትምህርታቸውን ኣቋርጠው በ1971 ዓ/ም ወደ ትጥቅ ትግል ያመሩት።

የትጥቅ ትግሉን መጠናቀቅ ተከትሎ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መጀመርያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን በግላቸው በለንደን ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው በኢኮኖሚክስ የትምህርት ክፍል ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል።

ወ/ሮ ፈትለወርቅ ፊት ለፊት መናገር የሚወዱና በፖለቲካ ብስለታቸው ብዙ ጓዶቻቸው የሚያደንቋቸው ሲሆኑ በተለይ አቶ መለስን በጣም ከተቹ ጥቂቶች መካከል እንደሆኑ ይነገራል። በዚህም ምክንያት ክድርጅቱ አመራር ጋር መጠነኛ ቅራኔ ውስጥ ገብተው ነበር ።

መንጀሪኖ የትግል ስማቸው ሲሆን ወንድማቸው ታጋይ ሰለሞን(ሓየት) እና ሁለት እህቶቻቸው (አልማዝና ረግበ) በትጥቅ ትግሉ ኣጥቷል። መንጀሪኖ በ1999 የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፣ በ2007 ደግሞ የፖሊት ቢሮ አባል ሆነው ተመርጠዋል።

ቀደም ሲል የፌደራል ፋይናንስ ኢንተሊጀንስ ማዕከል ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ቀጥለው ደግሞ የድርጀቱ ህዝብ ግንኙነት ሆነው ነበር። ባለፈው ዓመት ደግሞ በኢህአዴግ ሴክሬታርያት የከተማ ሴክተር ሃላፊ ሀኖው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ወ/ሮ ፈትለወርቅ የመጀመሪያዋ የድርጅቱ ሴት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጧል።

አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ

በትጥቅ ትግሉ የዓይናቸውን ብርሀን ሙሉ ለሙሉ ካጡት መካከል የሆኑት አቶ አስመላሽ ላለፉት ሁለት ዓመታት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የመንግሥት ተጠሪ ናቸው።

አቶ አስመላሽ በለያዩ ወቅቶች በሚሰጧቸው ህግ ነክ ማብራሪያዎች በፓርላማ የሚታወቁ ሲሆን የመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪያቸው በህግ ሰርተዋል።

እንዲሁም ደግሞ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በአሁኑ ወቅት የዶክትሬት ድግሪ እጩ ናቸው።

ዶ/ር ኣብርሃም ተከስተ

የዶክትሬት ድግሪያቸው በኢኮኖሚክስ ከስዊዘርላንድ ያገኙ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በትጥቅ ትግሉ ያልተሳተፉ የህወሓት የፖሊት ቢሮ አባል ከሆኑ ሦስት ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።

ብሔራዊ ፕላኒንግ ኮሚሽን ለሁለት ዓመታት ሚኒስትር ዲኤታ ሆነውም ሰርተዋል። ቀጥለውም የፋይናነስና ኢኮኖሚ ትብብርን በሚኒስትርነት ዲኤታነት ያገለገሉ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የተቋሙ ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ወ/ሮ ኬርያ ኢብራሂም

በድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ አባል ሆነው ከተመረጡት አራት አዳዲስ አባላት መካከል አንዷ ሲሆኑ፤ ከዚህ በፊት በክልሉ በተለያዩ የሃላፊነት ስፍራዎች ማገልገላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይ ደግሞ በትግራይ ምስራቅዊ እና ደቡብ ምስራቅ ዞኖች በተለያዩ ወቅቶች በሃላፊነት ሰርተዋል።

እንዲሁም ደግሞ በመቐለ ከተማና በክልል ደረጃ የሴቶች ጉዳይ ቢሮዎች ውስጥ አገልግለዋል።

ወ/ሮ ኬርያ እምብዛም በህዝብ የማይታወቁ ሲሆን የእሳቸው መመረጥ በብዙዎች ዘንድ የተጠበቀ አልነበረም።

ተያያዥ ርዕሶች