ናይጄሪያ በሊቢያ ያሉ ስደተኛ ዜጎቿን ለመመለስ ማቀዷን ገለፀች

Libyan has increased the repatriation of Nigerians in recent months Image copyright NCFRMI

በቅርቡ በሊቢያ የሚገኙ አፍሪካውያን ስደተኞች እንደ ሸቀጥ በጨረታ ሲሸጡ የሚያሳይ ምስል ከወጣ በኋላ ነው የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሐማዱ ቡሃሪ በሊቢያና በተለያዩ ሃገራት ያሉ ስደተኛ ዜጎቻቸውን ወደሃገራቸው ለመመለስ ቆርጠው መነሳታቸውን የተናገሩት።

ቡሃሪ ስደተኞቹ እንደ እንሰሳ ነው የተንገላቱት የሚል አስተያየት ካሰፈሩ በኋላ ናይጄሪያውን አስከፊውን ወደ አውሮፓ የሚደረግ ስደት የሚያቆሙበትን መፍትሄ ፍለጋ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የቡሃሪ እወጃ በተባበሩት መንግሥታት የሚመራው የሊቢያ መንግሥት ስደተኞችን ወደሃገራቸው የመመለስ ሥራ አጠናክሮ መቀጠሉን ካሳወቀ ከጥቂት ሰዓታት በኃላ ነው የተሰማው።

ማክሰኞ ምሽት ብቻ 240 የሚሆኑ ናይጄሪያውያን ስደተኞች በፈቃዳቸው የተባበሩት መንግሥታት ባዘጋጀላቸው በረራ ወደሃገራቸው ተመልሰዋል።

የአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲኤንኤን ነበር ባሳለፍነው ሳምንት ሊቢያ አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት ተስፋ አድርገው የወጡ አፍሪካውያን ስደተኞች በሕገ-ወጥ ሰው አዛዋዋሪዎች ተይዘው ለጉልበት ሥራ በጨረታ ሲሸጡ የሚያሳይ ምስል የለቀቀው።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ አሁን ላይ አንድ ሚሊዮን ገደማ ስደተኞች በሊቢያ እንደሚገኙ ይገመታል

በኪትዲቯር መዲና አቢጃን እየተካሄደ ያለው የአፍሪካና አውሮፓ ሕብረት የሁለትዮሽ ጉባዓ ዋነኛ ትኩረቱን በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት እየመከረ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

በጉባዔው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ቡሃሪ ባዩትና በሰሙት ነገር እጅግ መደንገጣቸውን ነው የተናገሩት። "አንዳንድ የሃገሬ ሰዎች ልክ እንደ ፍየል በጥቂት ዶላር ለጨረታ ሲቀርቡ ተመልክቻለሁ" ሲሉ ተደምጠዋል።

ቡሃሪ ተመላሾቹ ወደ መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲመለሱ ለማስቻል መንግሥታቸው ከፍተኛውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል።

አልፎም ቦኮ ሐራምን ለመደምሰስና ትምህርት በናይጄሪያ ለማስፋፋት ቃል የገቡት ፕሬዚዳንቱ ዜጎቻቸው ሃገር መልቀቅን እንደ ትክክለኛ አማራጭ እንዳይወስዱ አሳስበዋል።

ናይጄሪያ በምን መልኩ ስደተኛ ዜጎቿን ከሊቢያ ወደሃገራቸው እንደምትመልስ ግን በግልፅ የታወቀ ነገር የለም።