በኢትዮጵያ 76 በመቶ የሚሆኑት ወጣት ሴቶች ስለ ኤችአይቪ እውቀት የላቸውም ተባለ

የጸረ ኤች አይ ቪ ኤድስ ሪቫን Image copyright FAROOQ NAEEM

በኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በተደረገ ጥናት እድሜያቸው ከ15-24 የሚሆኑ ወጣቶች ስለኤች አይቪ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ እንደሆነ ታውቋል።

በተለይም ደግሞ በዚህ የእድሜ ክልል ከሚገኙ ሴቶች 76 በመቶ የሚሆኑት የኤች አይቪ መተላለፊያ እና መከላከያ መንገዶችን አያውቁም።

ወንዶች ቢሆኑ እውቀቱ ያላቸው 39 በመቶ ብቻ ናቸው።

በፌደራል የኤች አይቪ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳንኤል በትረ ለዚህ የተለያዩ አካላት ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸውን ምክንያት ያደርጋሉ።

እነዚህ አካላትም የህዝብ ምክር ቤቶች፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ግለሰቦች ማህበራት፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ የጎሳ መሪዎችና አጋር ድርጅቶች ናቸው።

መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስለ ኤች አይቪ ኢድስ በንቃት በሚያስተምሩበት ወቅት የዛሬዎቹ ወጣቶች ጨቅላ ህፃናት ነበሩ።

አሁን ግን ስለኤች አይቪ በማይወራበት ጊዜ ለአካለ መጠን በመድረሳቸው ለቫይረሱ ተጋላጭ ሆነዋል ይላሉ አቶ ዳንኤል።

ኢትዮጵያ፡ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ወረርሽኝ አዲስ ስጋት ፈጥሯል

"እነዚህ ወጣቶች በአብዛኛው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በትላልቅ የአበባ እርሻዎች፣ በፋብሪካዎች እና በኃይል ማመንጫ ግንባታዎች ላይ የሚገኙ ናቸው።"

እናም በኢትዮጵያ ከአፍላ ወጣቶች ግንዛቤ ማነስ ጋር በተያያዘ የኤች አይቪ ስርጭትም በዚሁ የእድሜ ክልል ከፍተኛ ምጣኔ ይታይበታል ።

Image copyright Getty Images

አቶ ዳንኤል ጨምረው እንደገለፁት በኤች አይቪ የሚሞቱ ሰዎች እንደሀገር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ዝምታንና መዘናጋትን ፈጥሯል።

በተቃራኒው ደግሞ በወጣቶች መካከል ለኤች አይቪ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ጨምረዋል።

ስለዚህ ምንም እንኳ ዛሬ የስርጭት መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም የአጋላጭ ሁኔታዎች እየጨመረ መምጣት ግን ነገ የስርጭት መጠኑ እንዲጨምር ያደርገዋል።

አቶ ዳንኤል "መዘናጋቱ ነገ ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል" በማለት የሁኔታውን አሳሳቢነት ይገልፃሉ።

ከነዚህ ወጣቶች ባሻገር ለኤች አይቪ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት እና የስርጭት መጠኑ ከፍ ያለው በወሲብ ንግድ ስራ ላይ በተሰማሩ ሴቶች፣ የረጅም ርቀት መኪና አሽከርካሪዎች እና በማረሚያ ቤት የሚገኙ ግለሰቦች ላይ ነው።

ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም፤ በየጊዜው የኤች አይቪ ምርመራ እና ክትትል የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥርም አነስተኛ ነው ሲሉ አቶ ዳንኤል ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ምንም እንኳን የትምህርት ሚኒስቴር ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ በቋንቋ፣በሥነ-ዜጋ፣ በሥነ-ሕይወት የሥርዓተ ትምህርቶች ውስጥ ቢካተትም የተጠበቀውን ያህል ለውጥ እንዳልመጣ አቶ ዳንኤል ይገልፃሉ።

በየአመቱ ህዳር 22 የሚከበረው የፀረ ኤች አይቪ ቀን የዘንድሮ መሪ ቃል "አሁንም ትኩረት ለኤች አይቪ መከላከል" የሚል ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ