ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋዋ ለሁለት የጦር ሰራዊቱ አባላት ቁልፍ የሚኒስትር ቦታ ሰጡ

ኤመርሰን ምናንጋዋ የፕሬዝዳንትነት ቃለመሃላ ከፈፀሙ በኋላ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋዋ ለሁለት ከፍተኛ የጦር ሃላፊዎች የሚንስትርነት ሹመት ሰጡ።

የዚምባብዌ አዲሱ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋዋ አዲሱን ካቢናቸውን ያዋቀሩ ሲሆን ሁለት ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ቁልፍ ለሆኑ የሚንስትር ቦታ ሾመዋል።

ምናንግዋ በቴሌቪዥን ቀርበው የሙጋቤን ከስልጣን መውረድ ያወጁትን ሲቡሲሶ ሞዮን አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድርገው ሾመዋል።

የዚምባብዌ አየር ሃይል ፕሬንስ ሺሪን ደግሞ የግብርናና መሬት ጉዳዮች ሚኒስትር አድርገው ሾመዋል።

አዲሱ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ስልጣን ለመልቀቅ ከተስማሙ በኋላ ቃለ መሃላ የፈፀሙት ባለፈው ሳምንት ነበር ።

ዚምባብዌን ለ37 ዓመታት የመሩት ሙጋቤ ምናንጋዋን ከምክትል ፕሬዚዳንትነት ስልጣናቸው ማባረራቸውን ተከትሎ ሰራዊቱ ጣልቃ ገብቶ ነበር ከስልጣን የወረዱት።

አዲሱ ፕሬዚዳንት በርካታ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሚኒስትሮቸን መልሰው የሾሙ ቢሆንም ወደስልጣን ያመጧቸውን የጦር መኮንኖችንም አልረሱም።

ከሞዮ እና ሺሪ በተጨማሪ የቀድሞ ጦር ሰራዊት ማህበር አመራሮች የሆኑ እና ሙጋቤን ከስልጣን ለማውረድ የረዷቸውንም ሰዎች የካቢኔ አባል አድርገዋቸዋል።

ቡድኑን የመሩት ክሪስ ሙታስንጋዋ አሁን የማስታወቂያ ሚንስትር ሆነዋል።

Image copyright DEWA MAVHINGA
አጭር የምስል መግለጫ ጀነራል ሲቡሲሶ ሞዮ

ይህ ሹመት የዚምባብዌ መንግስትን በመተቸት የሚታወቁትን ቴንዳይ ቢቲን ዚምባብያውያን ለውጥ መጠበቃቸው ስህተት ነበር እንዲሉ አድርጓቸዋል።

ፕሪንስ ሺሪ በ1980 የሙጋቤ ተቃዋሚ የነበሩት ላይ ወታደራዊ እርምጃ በመውሰድም ይታወቃሉ።

ያ እርምጃ 20000 ሰላማዊ ዜጎችን ህይወታቸውን ያሳጣ ነበር።

ምናንጋዋ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከሃገር ከመሰደዳቸው በፊት በምክትል ፕሬዚዳንትነት ማዕረግ ሃገራቸውን ያስተዳድሩ ነበር።

ከምክትል ፕሬዚዳንትነት ስልጣናቸው መነሰታቸውን ተከትሎ የጦር ሰራዊቱ እና ፓርቲያቸው ባደረጉት ጣልቃ ገብነት የጀግና አቀባበል ተደርጎላቸው ተመልሰዋል።

ህዳር 14 በዚምባብዌ ዋና ከተማ ሐራሬ አውራ ጎዳናዎች ላይ ታንክ የታየ ሲሆን ሙጋቤም በቤት ውስጥ የቁም እስር ውለዋል።

የጦር ሰራዊቱ መፈንቅለ መንግሥት እንዳላካሄደ የተናገረ ሲሆን እርምጃው ሙጋቤን የከበቧቸውን ወንጀለኞች ለመከላከል እንደሆነ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ሙጋቤን ማንን ይተካቸዋል ከሚለው የስልጣን ሽኩቻ በምናንጋዋ እና በግሬስ ሙጋቤ መካከል ከነበረው ሽኩቻ በኋላ ነበር።

ምናንጋዋ "አዲስ እጣ ፈንታ" ለዚምባቤያውያን ቃል ይግቡ እንጂ በርካቶች ሀገሪቱ ነፃነቷን በ1980 ካገኘች እና ዛኑ ፒ ኤፍ ስልጣን ከያዘ በኋላ ለተፈፀሙ ስህተቶች ተጠያቂ ናቸው ይሏቸዋል።

ተያያዥ ርዕሶች