በሩሲያው የዓለም ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ላይ እነማን ይገናኛሉ?

Lionel Messi, the Kremlin and Thomas Muller Image copyright Getty Images

የ2018 የሩሲያ ዓለም ዋንጫ የምድብ ድልድል ዕጣ የማውጣት ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሞስኮ በሚገኘው ክሬምሊን ቤተ መንግሥት ውስጥ ይካሄዳል።

ውድድሩ በሩሲያ ከሰኔ 7 እስከ ሐምሌ 8 ድረስ የሚከናወን ሲሆን፤ 32 ሃገራት በውድድሩ መሳተፋቸው አረጋገጠዋል። ግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል እና ቱኒዝያ ደግሞ አምስቱ የአፍሪካ ተሳታፊ ሃገራት ናቸው።

የዛሬው ዕጣ የማውጣት ሥነ- ሥርዓት ብሔራዊ ቡድኖቹ ከየትኛው ሃገር ጋር እንደሚጋጠሙ ይለያል።

እንዴት ይሰራል?

የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓቱ በቢቢሲው አቅራቢና እና ቀድሞ እንግሊዝ አጥቂ ጋሪ ሊንከር እና የሩሲያ ስፖርት ጋዜጠኛ ማሪኣ ኮማንድናያ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

ብሔራዊ ቡድኖቹ በህዳር ወር ፊፋ የዓለም ሃገራት ደረጃ መሠረት ተደልድለዋል። ስምንት ቡድኖችን የያዙ አራት ቋቶች አሉ። ሩሲያ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ሰባት ሃገራት ጋር በመጀመሪያው ቋት ስትገኝ ተከታይ ውጤት ያላቸው ሌሎች ስምንት ቡድኖች በሁለተኛው ቋትውስጥ ተካተዋል። በቋት ሶስት እና በቋት አራትም በተመሳሳይ በውጤታቸው መሠረት ስምንት ስምንት ቡድኖች ተካተዋል።

ከተዘጋጁት አራት ቋቶች ውስጥ አንድ አንድ ቡድን ተወስዶ አራት ቡድኖች በዓለም ዋንጫው አንድ ምድብ ውስጥ በጋራ ይካተታሉ። ይህ ሂደት ስምንት ጊዜ ተከናውኖ ከአንድ እስከ ስምንት ባሉት ቡድኖች ውስጥ አራት አራት ቡድኖች እንዲኖሩ ይደረጋል።

ከአውሮፓ ቡድኖች ውጭ ከአንድ አህጉር የመጡ ቡድኖች በጋራ አይደለደሉም። በአንድ ምድብ ከሁለት የአውሮፓ ሃገራት በላይ እንዲካተቱ አይደረግም።

እነማን ተሳታፊ ሆኑ?

Image copyright Getty Images

ቋት 1

ሩሲያ (አዘጋጅ)፣ ጀርመን(የፊፋ ደረጃ 1ኛ)፣ ብራዚል (የፊፋ ደረጃ 2ኛ)፣ ፖርቹጋል (የፊፋ ደረጃ 3ኛ)፣ አርጀንቲና (የፊፋ ደረጃ 4ኛ)፣ ቤልጂየም (የፊፋ ደረጃ 5ኛ)፣ ፖላንድ (የፊፋ ደረጃ 6ኛ)፣ ፈረንሳይ (የፊፋ ደረጃ 7ኛ)

ቋት 2

ስፔን(የፊፋ ደረጃ 8ኛ)፣ ፔሩ (የፊፋ ደረጃ 10ኛ)፣ ስዊዘርላንድ (የፊፋ ደረጃ 11ኛ)፣ እንግሊዝ (የፊፋ ደረጃ 12ኛ)፣ ኮሎምቢያ (የፊፋ ደረጃ 13ኛ)፣ ሜክሲኮ (የፊፋ ደረጃ 16ኛ)፣ ኡራጓይ (የፊፋ ደረጃ 17ኛ)፣ ክሮሺያ (የፊፋ ደረጃ 18ኛ)

ቋት 3

ዴንማርክ (የፊፋ ደረጃ 19ኛ)፣ አይስላንድ (የፊፋ ደረጃ 21ኛ)፣ ኮስታሪካ (የፊፋ ደረጃ 22ኛ)፣ ስዊዲን (የፊፋ ደረጃ 25ኛ)፣ ቱኒዝያ (የፊፋ ደረጃ 28ኛ)፣ ግብጽ (የፊፋ ደረጃ 30ኛ) ፣ሴኔጋል (የፊፋ ደረጃ 32ኛ)፣ ኢራን (የፊፋ ደረጃ 34ኛ)

ቋት 4

ሰርቢያ (የፊፋ ደረጃ 38ኛ)፣ ናይጄሪያ (የፊፋ ደረጃ 41ኛ)፣ አውስትራሊያ (የፊፋ ደረጃ 43ኛ)፣ ጃፓን (የፊፋ ደረጃ 44ኛ)፣ ሞሮኮ (የፊፋ ደረጃ 48ኛ)፣ ፓናማ (የፊፋ ደረጃ 49ኛ)፣ ደቡብ ኮሪያ (የፊፋ ደረጃ 62ኛ)፣ ሳዑዲ አረቢያ (የፊፋ ደረጃ 63ኛ)