ምድብ ሁለት፡ ፖርቹጋል፣ ስፔን፣ ሞሮኮ እና ኢራን

Cristiano Ronaldo Image copyright Reuters

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ተጠናቆ አዘጋጇ ሩሲያን ጨምሮ ወደ ዓለም ዋንጫው ያለፉ 32 ሃገራት ተለይተዋል።

የአምስት ጊዜ አሸናፊዋ ብራዚልን ጨምሮ ያለፈው ጊዜ አሸናፊዋ ጀርመን፣ ሩሲያ፣ አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ቤልጂም፣ ኮሎምቢያ፣ ኮስታሪካ፣ ክሮሺያ፣ ዴንማርክ፣ ግብጽ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ አይስላንድ፣ ኢራን፣ ጃፓን፣ ሜክሲኮ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ፓናማ፣ ፔሩ፣ ፖላንድ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሴኔጋል፣ ሰርቢያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ስፔን፣ ስዊዲን፣ ስዊዘርላንድ፣ ቱኒዝያ እና ኡራጋይ ናቸው በ2018ቱ ዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉት።

እነዚህ ሃገራት እንዴት እዚህ ደረሱ? ለውድድሩ ያበቋቸው ኮከብ ተጫዋቾች እነማን ናቸው? ለውድድሩ ያበቋቸው አሰልጣኞችስ እነማን ናችው?

እያንዳንዱን ሃገር በምድብ ከፋፍለን እንመለከታለን።

ምድብ ሁለት

ፖርቹጋል

የቀደመ ታሪክ፡ በዩሮ 2016 ፍጻሜ ላይ አዘጋጇ ፈረንሳይን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ፖርቹጋል የወቅቱ አውሮፓ ሻምፒዮን ለመሆን በቅታለች። በዓለም ዋንጫ ያላቸው ምርጥ ውጤት በ1966 ሶስተኛ ሆነው ያጠናቀቁበት ነው። በ2006 ለግማሽ ፍፋሜ መድረስ ቢችሉም በብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ከምድባቸው ማለፍ አልቻሉም።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ክርስተያኖ ሮናልዶ። ከእሱ ውጭ ማን ሊሆን ይችላል? ለአራት ጊዜ የዓለም ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ለመመረጥ በቅቷል። ለብሔራዊ ቡድኑ ብዙ ጨዋታዎችን በማድረግና ብዙ ጎሎችን በማስቆጠር ክብረ ወሰኑን ይዟል። በዓለም ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታዎች ወቅት የአራት ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው 15 ጎሎችን ለማስቆጠር ችሏል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? ፍርናንዶ ሳንቶስ መስከረም 2014 ሥራው ከተረከቡ በኋላ ዩሮ 2016ን በማሸነፍ ፖርቹጋል የመጀመሪያዋን ዓለም አቀፍ ድል እንድታስመዘገብ ረድተዋል። በ2014ቱ የዓለም ዋንጫ ወቅት የግሪክ አሰልጣኝ የነበሩት ሳንቶስ፤ ቡድኑን ከምድቡ ቢያሳልፉም በኮስታሪካ ተሸነፈው ከውድድሩ ውጭ ሆነዋል።

Image copyright Getty Images

ስፔን

የቀደመ ታሪክ፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም ሃገራት የፊፋ ደረጃ 11ኛ ደረጃን ይዘዋል። ከ2008 እስከ 2013 ባለው ጊዜ ግን አንደኛ ደረጃን ይዘው ቆይተዋል። ስፔን 2010 የዓለም ዋንጫን እና የ2008 እና 2012 የአውሮፓ ዋንጫን ማንሳት ችላለች።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ሪያል ማድሪዱ የአጥቂ አማካይ ኢስኮ በማጣሪያው ላይ ድንቅ ነበር። ባለፉት የስፔን ሰባት ጨዋታዎች ስድስት ጎሎችን ሲያስቆጥር አንድ ለጎል የሚሆን ኳስም አመቻችቶ አቀብሏል። ለብሔራዊ ቡድኑ ባደረጋቸው 23 ጨዋታዎች ሰባት ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? ዩለን ሎፔትይ ሰኔ 2016 የተሾሙ ሲሆን ባደረጓቸው 13 ጨዋታዎችም ሽንፈት አላስተናገዱም። ከስፔን የ21 እና የ19 ዓመት በታች ቡድን ጋር የአውሮፓ ዋንጫን ማንሳት ቢችሉም በትልቅ ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ግን አልተፈተኑም።

ሞሮኮ

የቀደመ ታሪክ፡ ሞሮኮ በ20 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ትሳተፋለች። በ1998 በፈንሳይ በተካሄደው ውድድር ማሸነፍ፣ አቻ መውጣትና መሸነፍ በቂ ስላልነበር በጊዜ ከውድድሩ ተሰናብታ ነበር። በ1986ቱ የሜክሲኮ ዓለም ዋንጫም ወደ ሁለተኛው ዙር አልፋ 16ቱ ውስጥ ብትገባም በምዕራብ ጀርመን 1 ለ 0 በመሸነፏ ከዛ በላይ መጓዝ አልቻለችም።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ለቡድኑ ጁቬንቱስ ቋሚ ሆኖ ባይጫወትም ተከላካዩ መድሂ ቤናቲያ በጣሊያኑ ክለብ ትልቅ ግምት የተሰጠው ተጫዋች ነው። የ30 ዓመቱ ተጫዋች የሞሮኮ አምበል ሲሆን 52 ጊዜም ለብሄራዊ ቡድኑ በቋሚነት መሰለፍ ችሏል። ቡድኑ ወደ ሩሲያ ማቅናቱን ባረጋገጠበትና አይቮሪኮስትን 2 ለ 0 ባሸነፉበት ጨዋታም አንድ ጎል ማስቆተር ችሏል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? ፈረንሳዊው ሃርቬ ሬናርድ በ1998 ጫማቸውን ከሰቀሉ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ ሲያሰለጥኑ ቆይተው ከ2016 ጀምሮ የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነዋል። ከዛምቢያ እና ከአይቮሪኮስት ጋር በ2012 እና በ2015 የአፍሪካ ዋንጫን ማንሳት ችለዋል። በሊል ከነበራቸው ውጤታማ ያልነበረ ቆይታ በኋላ ነው ሞሮኮ ማሰልጠን የጀመሩት።

Image copyright Getty Images

ኢራን

የቀደመ ታሪክ፡ ይህ የዓለም ዋንጫ ለኢራን አምስተኛ ተሳትፎዋ ሲሆን በውድድሮቹ ብቸኛውን ድል የተቀዳጀችው በፈረንሳዩ የ1998 (እአአ) የዓለም ዋንጫ አሜሪካንን 2ለ1 በማሸነፍ ነበር።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ሳርዳር አዝሙን ከኢራን አልፎ በእሲያ ከሚጠቀሱ አጥቂዎች መካከል አንዱ ነው።ለሩሲያው ሩቢን ካዛን ቡድን የሚጫወተው የ22 ዓመቱ አዝሙን በሁሉም በኩል አስደናቂ ብቃት እንዳለው ይነገርለታል።

አሰልጣኙ ማነው? ከዓለም አቀፍ የእግር ኳስ አሰልጣኞች መካከል ሰፊ ልምድ ያላቸው ካርሎስ ኬሮዥ የቡድኑ መሪ ናቸው። ስፖርቲንግ ሊዝበን፣ ሪያል ማድሪድን፣ የአሌክስ ፈርጉሰን ምክትል ሆነው ማንችስተር ዩናይትድን፣ የደቡብ አፍሪካን እና ሌሎችንም አሰልጥነዋል። ያለፉትን ስድስት ዓመታትም የኢራን ብሔራዊ ቡድንን እያሰለጠኑ ይገኛሉ።