ምድብ ሶስት፡ ፈረንሳይ፣ አውስትራሊያ፣ ፔሩ እና ዴንማርክ

Antoine Griezmann Image copyright EPA

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ተጠናቆ አዘጋጇ ሩሲያን ጨምሮ ወደ ዓለም ዋንጫው ያለፉ 32 ሃገራት ተለይተዋል።

የአምስት ጊዜ አሸናፊዋ ብራዚልን ጨምሮ ያለፈው ጊዜ አሸናፊዋ ጀርመን፣ ሩሲያ፣ አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ቤልጂም፣ ኮሎምቢያ፣ ኮስታሪካ፣ ክሮሺያ፣ ዴንማርክ፣ ግብጽ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ አይስላንድ፣ ኢራን፣ ጃፓን፣ ሜክሲኮ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ፓናማ፣ ፔሩ፣ ፖላንድ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሴኔጋል፣ ሰርቢያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ስፔን፣ ስዊዲን፣ ስዊዘርላንድ፣ ቱኒዝያ እና ኡራጋይ ናቸው በ2018ቱ ዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉት።

እነዚህ ሃገራት እንዴት እዚህ ደረሱ? ለውድድሩ ያበቋቸው ኮከብ ተጫዋቾች እነማን ናቸው? ለውድድሩ ያበቋቸው አሰልጣኞችስ እነማን ናችው?

እያንዳንዱን ሃገር በምድብ ከፋፍለን እንመለከታለን።

ምድብ ሶስት

ፈረንሳይ

የቀደመ ታሪክ፡ ፈረንሳይ ራሷ ያስተናገደችውን የ1998ቱን የዓለም ዋንጫ ያነሳች ሲሆን ከስምንት ዓመት በኋላ ደግሞ ለፍጻሜ ደርሳ በጣሊያን ተሸንፋለች። በ2014 ለሩብ ፍጻሜው የደረሱ ሲሆን በ2016 ባዘጋጁት የአውሮፓ ዋንጫ ላይ ሁለተኛ ለመውጣት ችለዋል።

ቁልፍ ተጫዋች፡ አንቶኒ ግሪዝማን። ፈረንሳይ ለ2016 የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ስትደርስ በስድስት ጎሎች ከፍተኛ ጎል አግቢ የነበረ ሲሆን ብሔራዊ ቡድኑ ቤላሩስን 2 ለ 1 አሸንፎ ለዓለም ዋንጫው ሲያልፍ አንድ ጎል ከመረብ አሳርፏል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? ዲዲዬ ዴሻምፕ ለብሄራዊ ቡድኑ 103 ጊዜ ተሰልፈው የተጫወቱ ሲሆን ፈረንሳይ የ1998 የዓለም ዋንጫን እና 2000 አውሮፓ ዋንጫን እንድታሸንፍ አግዘዋል። ከሰኔ 2012 ጀምሮ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ የሆኑ ሲሆን ቡድኑን ለአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ቢያደርሱም በፖርቹጋል 1 ለ 0 ተሸንፈዋል።

Image copyright EPA

አውስትራሊያ

የቀደመ ታሪክ: የዘንድሮው የአውስትራሊያ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ በተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን በአጠቃላይ ግን አምስተኛዋ ነው። ጥሩ ተሳትፎ አድርጋበታለች የሚባለው በ2006 (እአአ) በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ላይ ሲሆን፤ ከመጨረሻዎቹ 16 ቡድኖች ገብታ ገብታ ከጣሊያን ጋር ባደረገችው ጨዋታ በመጨሻዎቹ ደቂቃ በተሰጠባት ፍፁም ቅጣት ምት ተሸንፋ የወጣችበት ነው።

ቁልፍ ተጫዋቾች፡ ቲም ካሂል ምንም እንኳን 37 ዓመቱ ቢሆንም ለብሔራዊ ቡድኑ አሁንም ኮከብ መሆኑን ቀጥሏል። የኤቨርተን የቀድሞ የመሃል ሜዳ ተጫዋች የነበረው ካሂል በማጣሪያ ውድድር ከሶሪያ ጋር በተደረው የመልስ ጨዋታ ወሳኝ ሁለት ጎሎችን ጨምሮ ለብሔራዊ ቡድኑ 11 ግቦችን አስቆጥሯል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? ግሪክ የተወለዱት አውስትራሊያዊ አንጌ ፖስቴኮግሉ አውስትራሊያ ውስጥ እግር ኳስን ተጫውተዋል እንዲሁም አሰልጥነዋል። አሰልጣኙ የአውስትራሊያ ቡድን ሦስቱንም የምድብ ጨዋታዎች በሽንፈት ያጠናቀቀበትን ነገር ግን ባሳየው ጥረት የተወደሰበትን የ2014 (እአአ) የዓለም ዋንጫ ላይ አሰልጣኝ ነበሩ።

ፔሩ

የቀደመ ታሪክ፡ ፔሩ 32ኛውና የመጨረሻው ወደ አለም ዋንጫ ያለፈ ቡድን ነው። ፔሩ በጄፈርሰን ፋርፋን እና በክርስቲያን ራሞስ በተቆጠረ ግብ ኒው ዚላንድን 2 ለ 0 በማሸነፍ ወደ አምስተኛውን የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋ ያረጋገጠችው። በ1970 ሰባተኛ ሆነው ያለፉ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ዓለም ዋንጫ ያለፉት በ1982 ነው። በፊፋ የደረጃ ሰንጠረዥ መሠረት ፔሩ ከአለም 10ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ቁልፍ ተጫዋች፦ ለሎኮሞቲቭ ሞስኮው የሚጫወተው ፋርፋን ለፔሩ 79 ጊዜ ተጫውቶ 23 ጎሎችን አስቆጥሯል። የ33 ዓመቱ ተጫዋች በፍጥነቱ የሚታወቀው ሲሆን በማጣሪያውም ሶስት ጎሎችን አስቆጥሯል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? አርጀንቲናው ሪካርዶ ጋርሲያ በቅፅል ስማቸው "ነብሩ" እየተባሉ የሚታወቁ ሲሆን ፔሩን ከ 2015 ጀምሮ እያሰለጠኑ ይገኛሉ። ለአርጀንቲና 20 ያህል ጊዜ የተጫወቱ ሲሆን 20 ዓመት በአሰልጣኝነት ሰርተዋል።

የ59 ዓመቱ አሰልጣኝ ፔሩን ከማሰልጠናቸው በፊት ቡድኑን በስነ-ልቦና ባለሙያነት አገልግለዋል።

Image copyright Getty Images

ዴንማርክ

የቀደመ ታሪክ፡ ዴንማርክ እ.አ.አ ከ2010 በኋላ በዓለም ዋንጫው ስትሳተፍ የመጀመሪያዋ ቢሆንም ይህ ግን በአጠቃላይ አምስተኛ ተሳትፎዋ ነው። በብራዚል ከውድድሩ በወጡበት የ1998ቱ የዓለም ዋንጫ እስከ ሩብ ፍጻሜ ለመጓዝ ችለዋል።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ሁሉም የዴንማርክ ምርጥ እንቅስቃሴዎች የቶተንሃሙን አማካይ ክርስቲያን ኤሪክሰንን ያካተቱ ናቸው።ለጎል የሚሆን ኳስ አመቻችቶ ከመስጠት በተጨማሪ ለብሔራዊ ቡድኑ 74 ጨዋታዎችን አድርጎ 18 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? ሞርተን ኦልሰን ቡድኑን ለአውሮፓ ዋንጫ ማብቃት ባለመቻላቸው ነበር በ64 ዓመቱ ኤጅ ሃሬዴ የተተኩት። የቀድሞው የማንቸስተር ሲቲ እና ኖርዊች ተከላካይ በተጫዋችነት ዘመናቸው የስዊድኒን ሊግ ዋንጫን ሁለቴ አንስተዋል። የዴንማርክ እና የኖርዌይ ሊጎችን ደግሞ በአሰልጣኝነት አንስተዋል።