ምድብ አምስት፡ ብራዚል፣ ስዊዘርላንድ፣ ኮስታሪካ እና ሰርቢያ

Neymar Image copyright Getty Images

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ተጠናቆ አዘጋጇ ሩሲያን ጨምሮ ወደ ዓለም ዋንጫው ያለፉ 32 ሃገራት ተለይተዋል።

የአምስት ጊዜ አሸናፊዋ ብራዚልን ጨምሮ ያለፈው ጊዜ አሸናፊዋ ጀርመን፣ ሩሲያ፣ አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ቤልጂም፣ ኮሎምቢያ፣ ኮስታሪካ፣ ክሮሺያ፣ ዴንማርክ፣ ግብጽ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ አይስላንድ፣ ኢራን፣ ጃፓን፣ ሜክሲኮ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ፓናማ፣ ፔሩ፣ ፖላንድ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሴኔጋል፣ ሰርቢያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ስፔን፣ ስዊዲን፣ ስዊዘርላንድ፣ ቱኒዝያ እና ኡራጋይ ናቸው በ2018ቱ ዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉት።

እነዚህ ሃገራት እንዴት እዚህ ደረሱ? ለውድድሩ ያበቋቸው ኮከብ ተጫዋቾች እነማን ናቸው? ለውድድሩ ያበቋቸው አሰልጣኞችስ እነማን ናችው?

እያንዳንዱን ሃገር በምድብ ከፋፍለን እንመለከታለን።

ምድብ አምስት

ብራዚል

የቀደመ ታሪክ፡ በ1958፣ በ1962፣ በ1970፣ በ1994 እና በ2002 የዓለም ዋንጫን አንስተዋል። ከአራት አመት በፊት ግን ራሷ ባዘጋጀችው የአለም ዋንጫ ላይ በጀርመን 7 ለ 1 ተሸንፋለች። ኔይማር ወደ ፓሪስ ሴይንት ዠርሜይን የተዘዋወረበት ገንዘብ በዓለም ከፍተኛው ተከፋይ የእግር ኳስ ተጫዋች አድርጎታል።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ኔይማር የዓለምን የተጫዋቾች የዝውውር ክብረወሰንን በመስበር የፈረንሳዩን ሀብታም ክለብ ፓሪስ ሴይንት ዠርሜይን ተቀላቅሏል። የብራዚል ኮከብ የሆነው ፔሌ የ25 ዓመቱን የብራዚል ምርጡ ተጫዋች ሲል ያንቆለጳጰሰው ሲሆን የፊፋን ምርጥ ተጫዋች ምርጫ እንዲያሸንፍም ድጋፉን ሰጥቶታል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? የቀድሞው የብራዚል የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋች ካርሎስ ዱንጋን በመተካት ቲቴ አሁን የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆነዋል። ዱንጋ በፈረንጆቹ 1994 የብራዚል ብሄራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫን ሲያነሳ አምበል የነበረ ሲሆን፥ ብሄራዊ ቡድኑንም እ.ኤ.አ ከ2006 እስከ 2011 ድረስ አሰልጥኗል። ቲቴ የብሄራዊ ቡድኑን ዝና እንዲመልሱ ከባድ ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

Image copyright EPA

ስዊዘርላንድ

የቀደመ ታሪክ፡ ይህ ለስዊዘርላንድ 11ኛው የዓለም ዋንጫ ነው። በ1954 ያዘጋጁትን ውድድር ጨምሮ ለሶስት ጊዜ ለሩብ ፍጻሜ ለመድረስ ችለዋል። በ2014 ደግሞ ከምድብ ድልድሉ በኋላ በአርጀንቲና ተሸንፋለች።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ዤርዳን ሻኪሪ። ባለተሰጥኦው የስቶክ ሲቲ ጨዋታ አቀጣጣይ ለብሔራዊ ቡድኑ 20 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። ባለፈው የዓለም ዋንጫ ሆንዱራስ ላይ ሶስት ጎሎችን በማስቆጠር ሃትሪክ ሠርቷል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? ቭላድሚር ፔትኮቪች ከ2014 ጀምሮ የስዊዘርላንድ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል። በ2016 የአውሮፓ ዋንጫ ቡድኑን ከምድቡ ማሳለፍ ችለዋል። ሳራዬቮ የተወለዱትና የስዊዲን ዜግነት ያላቸው ፔትኮቪች የላዚዮ አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት የኮፓ ጣሊያንን ዋንጫ እ.አ.አ በ2013 ማንሳት ችለዋል።

ኮስታሪካ

የቀደመ ታሪክ፡ በሩሲያ በሚካሄደው የ2018ቱ ዓለም አቀፍ ዋንጫ ሎስ ቲኮሶች ሲሳተፉ አምስተኛቸው ይሆናል። ከዚህ በፊት ብራዚል ተካሂዶ በነበረው የዓለም ዋንጫ ኡራጓይ፣ጣልያንና እንግሊዝን ጨምሮ ከነበረው ቡድን በመሪነት አጠናቃለች። በሆላንድም በሩብ ፍፃሜ በፍፁም ቅጣት ከውድድሩ ውጭ ሆናለች።

ቁልፍ ተጫዋች፡ የቦሎኛው ተከላካይ ጊያንካርሎ ጎንዛሌዝ በ2014ቱ የቢቢሲ ዓለም ዋንጫው ቡድን ውስጥ ተካቶ የነበረ ቢሆንም በቅርብ የነበረው የኮስታሪካ ስኬት ጀርባ ኬይለር ናቫስ አለ። የ30 ዓመቱ ጎል ጠባቂ ባለፈው የዓለም ዋንጫ ባሳየው ብቃት ሪያል ማድሪድን ሊቀላቀል ችሏል። ከዚያም ጊዜ ጀምሮ የስፔንን ላሊጋ እንዲሁም ሻምፒዮንስ ሊግን በማሸነፍ ችሎታውን አስመስክሯል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? በአውሮፓውያኑ 1990 ኮስታሪካ ለሁለተኛ ጊዜ ዓለም ዋንጫ ላይ ስትሳተፍ ከነበሩት መካከል ኦስካር ራሚሬዝ ይጠቀሳሉ። ጫማቸውን ከሰቀሉ በኋላ የአሰልጣኝነቱን ጎራ የተቀላቀሉ ሲሆን ባላቸው ብቃት፣ ፈጠራና የቴክኒክ ችሎታ ብዙ የሊግ ዋንጫዎችን አግኝተዋል።

Image copyright Getty Images

ሰርቢያ

የቀደመ ታሪክ፡ ሰርቢያ በዓለም ዋንጫ ላይ ስትካፈል የሩሲያው ዓለም ዋንጫ 12ኛዋ ነው። በ2006 እና 2010 ከምድብ ካለፉበት ውጭ ያስመዘገቡት ትልቅ ታሪክ የለም።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ብራኒስላቭ ኢቫኖቪች ለብሄራዊ ቡድኑ ያደረጋቸው ጨዋታዎች ወደ 100 የቀረቡ ሲሆን የቡድኑም ቁልፍ ተጫዋቾ ሆኖ ቀጥሏል። የብሄራዊ ቡድኑም አምበል ነው። ለዓለም ዋንጫው ማለፋቸውመን ካረጋገጡ በኋላም "ሩሲያ ላይ ለእናንተ ለመጫወት ዝግጁ ነን" ሲል ለደጋፊዎቻቸው አስታውቋል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? እ.አ.አ በ2016 የተሾሙት ስላቮልዩብ ሙስሊን ብዙ ቦታዎች ሄደው በመስራት ይታወቃሉ። በብሔራዊ ቡድንም ሆነ በትልቅ ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ሲሳተፉ ይህ የመጀመሪያቸው ቢሆንም የቡልጋሪያ ሊግን ማንሳት ችለዋል።