ምድብ ስድስት፡ ጀርመን፣ ሜክሲኮ፣ ስዊዲን እና ደቡብ ኮሪያ

Germany Image copyright Getty Images

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ተጠናቆ አዘጋጇ ሩሲያን ጨምሮ ወደ ዓለም ዋንጫው ያለፉ 32 ሃገራት ተለይተዋል።

የአምስት ጊዜ አሸናፊዋ ብራዚልን ጨምሮ ያለፈው ጊዜ አሸናፊዋ ጀርመን፣ ሩሲያ፣ አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ቤልጂም፣ ኮሎምቢያ፣ ኮስታሪካ፣ ክሮሺያ፣ ዴንማርክ፣ ግብጽ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ አይስላንድ፣ ኢራን፣ ጃፓን፣ ሜክሲኮ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ፓናማ፣ ፔሩ፣ ፖላንድ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሴኔጋል፣ ሰርቢያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ስፔን፣ ስዊዲን፣ ስዊዘርላንድ፣ ቱኒዝያ እና ኡራጋይ ናቸው በ2018ቱ ዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉት።

እነዚህ ሃገራት እንዴት እዚህ ደረሱ? ለውድድሩ ያበቋቸው ኮከብ ተጫዋቾች እነማን ናቸው? ለውድድሩ ያበቋቸው አሰልጣኞችስ እነማን ናችው?

እያንዳንዱን ሃገር በምድብ ከፋፍለን እንመለከታለን።

ምድብ ስድስት

Image copyright Getty Images

ጀርመን

የቀደመ ታሪክ፡ ያለፈው ዓለም ዋንጫ አሸናፊ፤ የውድድሩ የአራት ጊዜ ባለ ድል እና የዓለም ቁጥር አንድ ቡድን።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ቶኒ ክሩስ። ከቶማስ ሙለር እና ሜሱት ኦዚል ውጭ የሪያል ማድሪዱ ተጫዋች የብሄራዊ ቡድኑ ነባር እና ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች አንዱ ነው። ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር የዓለም ዋንጫን ካነሳ በኋላ ሁለት የሻምፒዮንስ ሊግ፤ አንድ የላ ሊጋ እና ሁለት የፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? ዮሃኪም ሎው። ከ2004 እስከ 2006 ድረስ የየርገን ክሎፕ ምክትል በመሆን የሰሩ ሲሆን ከዛ በኋላ ደግሞ ዋና አሰልጣኝ ሆነዋል። አርጀንቲናን በማሸነፍ ዓለም ዋንጫን ያነሱ ሲሆን በ2008 የኮንፈደሬሽን ዋንጫ ባለቤት ለመሆንም በቅተዋል። በ2008ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ሁለተኛ ሲወጡ ከአራት ዓመት በኋላ ደግሞ ሶስተኛ ለመሆን በቅተዋል።

ስዊዲን

የቀደመ ታሪክ፡ የሩሲያው የዓለም ዋንጫ ለስዊዲን 12ኛው በመድረኩ የተሳተፈችበት ወድድር ነው። ከ2006 በኋላ ግን የመጀመሪያቸው ነው። በ1958 ለፍጻሜ ቢደርሱም በብራዚል የተሸነፉ ሲሆን በ1994 ደግሞ ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ዝላታን ኢብራሂሞቪችን መተካት ከባድ ቢሆንም የአል አይኑ አጥቂ ማርከስ በርግ በአስር የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ስምንት ጎሎችን አስቆጥሯል። ምድቡን ከፈረንሳይ በመቀጠል ሁለተኛ ሆነው ቢያጠናቅቁም ከጣሊያን ጋር ባደረጉት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ወደ ወድድሩ ተቀላቅለዋል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? የ55 ዓመቱ ጃን አንደርሰን በአይ ኤፍ ኬ ኖርኮፒንግ የነበራቸውን የአምስት ዓመት ቆይታ በማጠናቀቅ በ2016 ነው ብሔራዊ ቡድኑን የተረከቡት። በመጀመሪያ ማጣሪያ ውድድራቸውም ቡድኑን ለዓለም ዋንጫ አብቅተውታል።

ሜክሲኮ

የቀደመ ታሪክ፡ ሜክሲኮ በባለፉት ስድስት የዓለም ዋንጫዎች ላይ ወደ ጥሎ ማለፉ የደረሰች ሲሆን በአውሮፓውያኑ 1986 ደግሞ ወደ ሩብ ፍፃሜ ደርሳለች።

ቁልፍ ተጫዋቾች፡ ሀይርቪንግ ሎዛኖ ፓቹካ ክለብን ጥሎ ፒ ኤስ ቪ ኤይንድሆቨንን ከተቀላቀለ ጀምሮ በሶስት ጨዋታዎች ሶስት ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። የ22 ዓመቱ ሎንዞ ሜክሲኮ ፓናማን ካሸነፈች በኋላ እንደብሄራዊ ጀግናም እየተቆጠረ ነው።

ሎንዞ ለፒ ኤስ ቪ ኤይንድሆቨን ባስቆጠራት ጎል የአርጀንቲናውን ታላቅ ተጫዋች ዲያጎ ማራዶናንም ያስደመመ ሲሆን ለቡድኑ ያስቆጠራት መጀመሪያ ጎልም የክለቡን ደጋፊዎች ቀልብ የያዘች ሆናለች።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? የቀድሞው የማንችስተር ሲቲ ረዳት አሰልጣኝ ጁዋን ካርሎስ ኦስሪዮ በዋናነት ይመራሉ። ነገር ግን ወርቃማ የሆነውን የዓለም ዋንጫ ዘመቻን ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ማህበር በስድስት ጨዋታዎች ላይ እንዳይገኙ ገደብ ስለጣለባቸው መገኘት አልቻሉም። ይህ ቅጣት የተጣለባቸውም የኮንፌዴሬሽኑ ውድድር በሚካሄድበት ወቅት ባለስልጣናቱን ስድብና ቁጣ ባዘለ መልኩ በመናገራቸው ነው።

ከሊቨርፑል ጆን ሙርስ ዩኒቨርሲቲ በእግር ኳስ ሳይንስ በዲፕሎማ የተመረቁት ኮሎምቢያዊው ጁዋን በዚህ ንግግራቸው ቢተቹም ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ደግፈዋቸዋል።

Image copyright Getty Images

ደቡብ ኮሪያ

የቀደመ ታሪክ፡ 'የቴጉክ ጦረኞች' በሚል ቅፅል ስም የሚጠራው የደቡብ ኮሪያ ቡድንን ያህል በዓለም ዋንጫ ላይ አህጉረ እስያን በማስጠራት ታሪክ ያለው ቡድን የለም። ሩሲያ ላይ የሚስተናገደውን የዘንድሮውን ጨምሮ ደቡብ ኮሪያ ለዘጠኝ ተከታታይ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ላይ የተሳተፈች ሲሆን በአጠቃላይ ለ10 ጊዜ በውድድሩ ላይ ቀርባለች።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ለቶተንሃም የሚጫወተው ሰን ሂዩንግ-ሚን በእግር ኳስ ችሎታው የተመሰከረለት ሲሆን ከቡድኑ ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው። የዓለም ዋንጫ ውድድር ሲጀመር 39 ዓመት የሚሆነው የቀድሞው የሚድልስቦሮ አጥቂ ሊ ዶንግ-ጉክም ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል ይገኛል።

አሰልጣኙ ማነው? በማጣሪያ ጨዋታዎች ቡድኑ ባሳየው ወጥ ያልሆነ አቋም ሳቢያ ከባድ ተቃውሞ ገጥሟቸው የነበሩት 'የእስያው ሞሪንሆ' በሚል ቅፅል የሚታወቁት ሺን ቴ-ዮንግ የደቡብ ኮሪያ ተጫዋቾችን ይመራሉ። ባለፈው ሐምሌ ቡድኑን የተረከቡት አሰልጣኙ ጊዜ ከተሰጣቸው ቡድኑን ወደተሻለ አቋም ያደርሱታል ተብሎ ይጠበቃል። የ48 ዓመቱ ሺን ቴ-ዮንግ ለ12 ዓመታት በደቡብ ኮሪያ ሊግ የተጫወቱ ሲሆን ለአጭር ጊዜ አውስትራሊያ ውስጥ ተጫውተው በ2005 (እአአ) ኳስ አቁመዋል።