ምድብ ሰባት፡ ቤልጅየም፣ ፓናማ፣ ቱኒዝያ እና እንግሊዝ

England failed to progress from the group stages of the World Cup in 2014 Image copyright Getty Images

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ተጠናቆ አዘጋጇ ሩሲያን ጨምሮ ወደ ዓለም ዋንጫው ያለፉ 32 ሃገራት ተለይተዋል።

የአምስት ጊዜ አሸናፊዋ ብራዚልን ጨምሮ ያለፈው ጊዜ አሸናፊዋ ጀርመን፣ ሩሲያ፣ አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ቤልጂም፣ ኮሎምቢያ፣ ኮስታሪካ፣ ክሮሺያ፣ ዴንማርክ፣ ግብጽ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ አይስላንድ፣ ኢራን፣ ጃፓን፣ ሜክሲኮ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ፓናማ፣ ፔሩ፣ ፖላንድ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሴኔጋል፣ ሰርቢያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ስፔን፣ ስዊዲን፣ ስዊዘርላንድ፣ ቱኒዝያ እና ኡራጋይ ናቸው በ2018ቱ ዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉት።

እነዚህ ሃገራት እንዴት እዚህ ደረሱ? ለውድድሩ ያበቋቸው ኮከብ ተጫዋቾች እነማን ናቸው? ለውድድሩ ያበቋቸው አሰልጣኞችስ እነማን ናችው?

እያንዳንዱን ሃገር በምድብ ከፋፍለን እንመለከታለን።

ምድብ ሰባት

Image copyright Getty Images

ቤልጂም

የቀደመ ታሪክ፡ ባለፉት ሁለት የዓለም ዋንጫዎች መሳተፍ የቻሉት የቤልጂየሞች በ2014ቱ የብራዚል የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ደርሰው በአርጀንቲና ተሸንፈዋል። ቀያይ ሴጣኖቹ እ.አ.አ በ1986 አራተኛ ሆነው የጨረሱበት በዓለም ዋንጫው ታሪክ ትልቁ ውጤታቸው ነው።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ኤዲን ሃዛርድ። ውጤታማ የሆነው የቼልሲው አጥቂ በፍጥነቱ፣ ኳስን በመቀጣጠርና በማቀብል ብቃቱ ተከላካዮችን ማለፍ ይችላል። የሮቤርቶ ማርቲኔዝን ቡድንም በአምበልነት ይመራል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? ሮቤርቶ ማርቲኔዝ በእንግሊዝ ያስመዘገቡት ትልቁ ድል እ.አ.አ በ2013 ኤፍ ኤ ዋንጫን ማንሳታቸው ነው። ሆኖም ከሶስት ቀናት በኋላ ከፕሪሚር ሊጉ ወርደዋል። የቀድሞው የስዋንሲና የኤቨርተን አሰልጣኝ በክለብ ቆይታቸው በማጥቃቱ በኩል የሚሰሩት ቡድን ጥሩ ቢሆንም በመከላከል ረገድ ክፍተት አለባቸው። ይህ ግን ለዚህኛው የቤልጂም ቡድን ከባድ አይመስልም። ምክንያቱም የቶተንሃሞቹን ያን ቬርቶገን እና ቶቢ አልደረዊርልድ እንዲሁም የማንቸስተር ሲቲው አምበል ቪንሰንት ኮምፓኒ በተከላካይ መስመር አማራጭ ናቸው።

ፓናማ

የቀደመ ታሪክ፡ በዓለም ዋንጫ ምንም ዓይነት ታሪክ የሌላት ፖናማ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሳተፍም ኮስታሪካን ከማሸነፏ በተጨማሪ የአሜሪካ በትሪንዳድና ቶቤጎ መሸነፍ ጠቅሟታል። በ2013ም በኮንካካፍ ጎልድ ካፕም ሁለተኛ ሆነው አጠናቀዋል።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ሉዊስ ተጃዳ፡ ዕድሜው 35 ቢሆንም 42 ጎሎችን በማስቆጠር ክብረወሰን አስመዝግቧል። ሉዊስ ተጃዳ በሩሲያ ላይ በሚደረገው ዓለም ዋንጫ የፓናማ ተስፋ ነው።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? ኮሎምቢያዊው ሄርናን ዳሪዮ ጎሜዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአሰልጣኝነት ልምድ ያላቸው ሲሆን ለሀገራቸውም ሁለት ጊዜ አሰልጣኝነት አገልግለዋል። ይህ ሶስተኛው የዓለም ዋንጫ ተሳትፎአቸው ነው። በአውሮፓውያኑ 1998 ኮሎምቢያ ጋር ለፍፃሜ ደርሰው በእንግሊዝ ተሸንፈዋል። በ2002ም የነበራቸው ተሳትፎ በኢኳዶር ተገትቷል።

Image copyright Rex Features

ቱኒዚያ

የቀደመ ታሪክ፡ መጪው የዓለም ዋንጫ ለቱኒዚያ በመጀመሪያው ዙር ከተሰናበተችበት የ2006 የጀርመን ውድድር ወዲህ የመጀመሪያዋ ይሆናል። በ1978፣ 1998 እና 2002 በውድድሩ ለመሳተፍ ከጫፍ ደርሰው ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

ቁልፍ ተጫዋች፡ የ28 ዓመቱ የመሃል ተከላካይ አይመን አብዴኑር ለቱኒዚያ የተከላካይ መስመር በልምድም በችሎታም ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። አሁን ከቫለንሺያ ወደ ፈረንሳዩ ማርሴይ በውሰት የተዛወረው አብዴኑር፤ በ57 ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። ከዚህ ቀደም በእንግሊዝ ፕሪሚያር ሊግ ወደ ኤቨርተን ወይም ቼልሲ ሊዛወር እንደሚችል ቢነገርም አሁን ደግሞ በዋትፎርዶች ዕይታ ውስጥ መግባቱ እየተዘገበ ነው።

አስልጣኙ ማን ናቸው? ናቢል ማሎል ለሁለተኛ ጊዜ ቱኒዚያን እያሰለጠኑ ነው። በ2013 ሰባት ጨዋታዎችን ካደረጉ በኋላ ሃገራቸውን ለ2014ቱ የዓለም ዋንጫ ማብቃት ባለመቻላቸው መልቀቂያ አስገብተው ተሰናብተው ነበር። በሚያዝያ 2017 ደግሞ በኳታሩ ኤል ጃይሽና በኩዌት ብሄራዊ ቡድን የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ ቡድኑ በድጋሚ ተመለሱ። ከዚህ ሁሉ በፊት ግን በ2004 ቱኒዚያ የ2004ን የአፍሪካ ዋንጫ ስታነሳ እንዲሁም በ2011 ኢ ኤስ ቱኒስ የሶስትዮሽ ዋንጫ ባለቤት ሲሆን የወቅቱ አሰልጣኝ ሮጀር ሌሜሬ ረዳት ነበሩ። በተጫዋችነት ዘመናቸውም በ1980ቹና 90ዎቹ በ74 ጨዋታዎች ለቱኒዝያ ተሰልፈዋል ተጫውተዋል። በ1988ቱ የሴኡል ኦሎምፒክም ሃገራቸውን ወክለዋል።

እንግሊዝ

የቀደመ ታሪክ፡ ብቸኛ ከሆነው የ1966ቱ የዓለም ዋንጫ ድል በኋላ እ.አ.አ በ1990 አራተኛ በመሆን ለማጠናቀቅ ችለዋል። ሶስቱ አንበሶች በ2014 ደግሞ በምድብ ማጣሪያው ላይ ተሰናብተዋል። ይህም ከ1958 በኋላ የመጀመሪያው ሲሆን በውድድሩ ሁለተኛ ጨዋታ ነው መሰናበታቸውን ያረጋገጡት።

ቁልፍ ተጫዋች፡ በመስከረም ወር ለሃገሩ እና ለክለቡ 13 ጎሎችን ያስቆጠረው አጥቂው ሃሪ ኬን በአሁኑ ወቅት ውጤታማ ከሆኑ የዓለማችን አጥቂዎች አንዱ ነው። በ2017 ያስቆጠራቸው 27 ጎሎች ከሊዮኔል ሜሲ በዘጠኝ ጎል ብቻ የሚያንሱ ናቸው።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? ጋሬት ሳውዝጌት የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ውድድራቸው ነው። አሰልጣኙ በጀርመን እና በፈረንሳይ ከደረሰባቸው ሽንፈት ሌላ በማጣሪያው ምንም ሽንፈት አላስተናገዱም።