''የአውደ ዓመት ግርግር ሁልጊዜ ይናፍቀኛል''

ፍሬሕይትና ቲዎድሮስ ከልጆቻቸው ጋር

ፍሬሕይወት ወንድሙ (ዶክተር) እባላለሁ ፤ እኔ ደግሞ ባለቤቷ ቴዎድሮስ አክሊሉ (ዶክተር) ነኝ። ከስድስት ዓመታት በፊት ነበር በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ በምትገኘው ሲራክዩዝ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዕድል አግኝተን ወደ አሜሪካ የመጣነው።

መጀመሪያ የትምህርት ዕድሉን ያገኘችው ባለቤቴ ፍሬ ነበረች። እኔ ደግሞ በጥገኝነት እርሷን ተከትዬ ብመጣም እድል ቀናኝና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የእኔም ማመልከቻ ተቀባይነት አግኝቶ ትምህርቴን ጀመርኩኝ ።

ሁለታችንም በግንቦትና በሐምሌ በ2009 ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቀናል።

አሁን ደግሞ ሁለታችንም በትልቅ ተቋም ውስጥ በካንሳስ ግዛት ዊቺታ ከተማ የማስተማርና ሌላም የቢሮ ሥራ ዕድል አግኝተን ከሁለት ወራት በፊት በዚሁ ከተማ መኖር ጀምረናል።

በፊት የነበርንባት ኒውዮርክ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የምታስተናግድ ከተማ በመሆኗ መርካቶን ታስታውሰኝ ነበር። ለኑሮም ቢሆን በጣም የምትመች ከተማ ናት።

ሰው ሁሉ ኑሮው በጥድፊያ የተሞላ ስለሆነ ማህበራዊ ግንኙነቱ በጣም ደካማ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ግን በጣም ደስ የሚል ግንኙነት ነበረን፤ በደስታም ሆነ በሃዘን ጊዜ በደንብ እንተጋገዝ ነበር፤ ቤተክርስቲያንም በጋራ እናገለግል ነበር፤ ትንሿ ኢትዮጵያ እንደሆነች ነበር የሚሰማኝ።

ሆኖም ሲራኪዩስ መልክዓምድሯና አየረንብረቷ በጣም ከባድ ነበር። በአሜሪካ በረዶ ክፉኛ ከሚጥልባቸው ከተሞች አንዷ ስለሆነች በዓመት እስከ ሰባት ወር ድረስ በረዶ አይጠፋባትም።

በዓመት ውስጥ በአማካይ እስከ 100 ኢንች (200 ሴ.ሜ) ድረስ በረዶ ከመጣሉ የተነሳ እጅግ ቆፈናማ ነበር።

ይህም ብቻ አልነበረም ለእኔም ሆነ ለባለቤቴ እየተማርን እና እየሠራን አንድ ወንድና አንድ ሴት ልጆችን ስላፈራን እነርሱን መንከባከቡ ጥንካሬያችንን ይፈትን ነበር።

ያኔ ደግሞ ልጆቻችን ወደማቆያ የመውሰድ አቅም ስላልነበረን የግድ ሁለታችንም ድካሙ ቢኖርም ጊዜውን እንደምንም አመቻችተን በፈረቃ ነበር የምንንከባከባቸው።

Image copyright Frehiwot

ቴዎድሮስ፦ እኔ ካህን ነኝ፤ ቤተክርስቲያን በቄስነት አገለግላለሁ። አስታውሳለሁ ሁለተኛ ልጃችን ስትወለድ በምናገለግልበት የቅድስት አርሴማ ገዳም ዓመታዊ ንገስ ነበር።

ለወትሮው አብረውኝ የሚሰሩ አገልጋዮች በተለያዩ ምክንያቶች ስላልነበሩ ሙሉ ኃላፊነቱ እኔ ላይ ነበር የወደቀው። ከዚያ በበዓሉ ዋዜማ ፍሬ ምጧ መጣና ሆስፒታል ገባች።

በአቅራቢያችን የነበረው ሰው ሁሉ በዝግጅት ላይ ስለሆነ ቤት ማንም አልነበረም፤ ማንን እንደምጠራ ግራ ገባኝ።

የጭንቁ ጊዜ አልፎ 10 ሰዓት ገደማ ስትገላለገል እርሷን ለሰዎች አደራ ብዬ ወደ አገልግሎቴ ሄድኩ፤ ነገር ግን ልቤን ቅር እያለውና እያመነታሁ ነበር የሄድኩት።

በኋላ ግን ማህበራችን በጣም ጠንካራ ስለነበረ ጓደኞቻችን የሆኑ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ሳይሰለቹ በየጊዜው እየተመላለሱ በደንብ አረሱልኝ፤ ስሟንም አርሴማ አልናት።

የሀገር ልጅ የማር እጅ

ከሲራኪዩስ አንጻር ዊቺታ ከገባን በኋላ በጣም የሚጎልብኝ ነገር (ፍሬሕይወት) ልጆቼ ሮጥ ብለው፣ ጓደኛዬ ብለው የሚሄዱበት ቦታ አለመኖሩ ነው፤ ኒውዮርክ እያሉ ብዙ ጓደኞች ነበሯቸው።

ቋንቋችንን በተቻለን መጠን ለማስተማር እንሞክራለን። ነገር ግን ቤት ብቻ የሚሆን ነገር ስላልሆነ እና ከአካባቢው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጋር ገና ስላልተዋወቅን የሚያወሩት ሰው አለመኖሩ ትንሽ ሆድ ያስብሰኛል።

እኛ አዋቂ ስለሆንን በሕይወታችን በምንወስናቸው ውሳኔዎች የሚመጡ ነገሮችን ለመቀበል ራሳችንን አዘጋጅተናል። ሕጻናቱ ግን በቀድሞ ከተማችን አብረው የነበሩትን ጓደኞቻቸውን ይናፍቃሉ።

ሃገር ቤትን የማስበው ይህን ጊዜ ነው። ሀገራችን ቢሆን እኛ እንኳን ባንኖር ጎረቤትም ዘመድም አይጠፋም ነበር።

እዚህ ግን በአንጻራዊነት ቅርብ ነው የሚባለውን የኢትዮጵያ ምግብ ቤት እንኳ ለማግኘት ሁለት ሰዓት ተኩል መንዳት ይጠበቅብናል።

ስለዚህ ያለንን አማራጭ ለመቀጠም እንጀራ ቤት ውስጥ እንጋግራለን። ብዙ ጊዜ የምንመገበውም እንጀራ ነው።

ከዚያ ውጭ በፍስክም ሆነ በጾም ሩዝ በአትክልትና በስጋ ስልስ እንመገባለን። እኔ በአትክልት ሲሆን ይበልጥ እወደዋለሁ።

እኔ ግን (ቴዎድሮስ) ያው መቼም መብላት ስላለብኝ እንጂ እንጀራ ከሌለ ፆሜን ላድር ሁሉ እችላለሁ፤ እሱ እንኳን ባይኖር መጠባበቂያ ድርቆሽ ከቤታችን አይጠፋም ።

ለነገሩ በየቀኑ ከሥራ እየተመላለስን ምግብ መሥራት ስለሚከብደን በአንድ ጊዜ ለሶስት ለአራት ቀን ነው ምግብ የምናበስለው። ለዚህ አይነት አመጋገብ ደግሞ እንጀራ በደንብ ይመቻል።

ባናዘወትረውም ፓስታ፣ ሩዝ ፣አትክልት፣ ዓሣና ሌሎች ጥብሳ ጥብሶችንም እንሠራለን።

ከኢትዮጵያ የሚናፍቃችሁ ነገር አለ?

እኔ ካህንም ስለሆንኩ ኢትዮጵያ ሆኜ የምሰማቸው የቤተክርስቲያን የኪዳን፣ የቅዳሴ ድምጽ፣ ደውሉ ሁልጊዜ እንደናፈቀኝ ነው። ምክንያቱም አሜሪካ እንዲህ ያለ ነገር የለም።

አንድ ቀን መኖሪያ ቤታችን አቅራቢያ ወደሚገኘው ኦክልሃማ ስሄድ አሜሪካ ከመጣሁ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀይ አፈር አየሁ። ያኔ ታዲያ ጉለሌ ሰፈሬ ትዝ አለኝ።

ሌላ ደግሞ (ፍሬህይወት) ኒውዮርክ ባሉ መኖሪያ ቤቶች ምንም አይነት የውጭ አጥር አልነበረም። እዚህ ግን እንደሃገር ቤት ባይረዝሙም አብዛኞቹ ቤቶች የእንጨት አጥር ስላላቸው ሰፈሬንም የክፍለሃገር ጉዞዬንም ያስታውሱኛል።

ግን እስካሁንም እንደናፈቅኩት የቀረሁትን በዓይኔ የሚዞርብኝ የዓመት በዓል ግርግር ነው፤ ከሳምንት ጀምሮ ገበያው ዋዜማው የጎረቤት ዘመድ አዝማድ ስብስቡ በጣም ይናፍቀኛል።

የምንኖርበት ቤት በጣም ብዙ መስታወት አለው። በዚህ ውስጥ አሻግረን የምናየው በመኖሪያ ህንጻዎች መሃል የተንጣለለ በንጽህና የሚጠበቅ አረንጓዴ ለምለም ቦታ አለ።

ልጆቻችን ይጫወቱበታል። ድመትና ውሻዎችም ይዝናኑበታል። ልጆቻችንም እነርሱን እያዩ ሲዝናኑ በአንድ እይታ ሁለት ውብ ነገር እንመለከታለን።

ሁሉንም ነገር የመቀየር አቅም ቢኖረን ኖሮ በቅርቡ በሞት ያጣናትን እናታችንን እቴቴን ሕይወት ለማትረፍ የሆነ ነገር እናደርግ ነበር፤ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜም ከቤተሰባችን ጋር እንሆን ነበር።

በዊቺታ ያሉ ሐበሻ ወንድምና እህቶቻችን ብዙዎቹ ባያውቁንም በሃዘናችን ጊዜ አጠገባችን ሆነው አጽናንተውናልና በዚህ አጋጣሚ ምስጋናችን ይድረስልን።

ለክሪስቲን ዮሐንስ እንደነገረቻት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦

ካለሁበት 13፡ ''ለእኔ ስኬት ማለት ገንዘብ ማግኘት ብቻ አይደለም''

ካለሁበት 14፡ "ብርዱ ሲከፋ፣ ቀኑም ሲያጥር የሀገሬ አየር በስንት ጣዕሙ እላለሁ።"

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ