በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የምትገኘው ቬኔዙዌላ ምናባዊ ገንዘብ ይፋ አደረገች

ፕሬዝዳንት ማዱሮ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ፕሬዝዳንት ማዱሮ

የቬኔዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ የሃገሪቱን የኢኮኖሚ ቀውስ ይቀንሳል ያሉትን ምናባዊ መገበያያ ይፋ አድርገዋል።

ፔትሮ የተሰኘው መገበያያ በቬኔዙዌላ ነዳጅ፣ ወርቅ እና አልማዝ ሃብት የሚደገፍ ይሆናል።

ተቃዋሚ የፓርላማ አባላት ግን ዕቅዱ ተቃውመውታል።

የቬኔዙዌላ ኢኮኖሚ በነዳጅ ዋጋ መቀነስ እና ቦሊቫር በተሰኘው የሃገሪቱ መገበበያ ገንዘብ መውደቅ ምክንያት እያሽቆለቆለ ይገኛል።

ፕሬዝዳንት ማዱሮ አሜሪካ ሃገራቸው ላይ የጣለችው ማዕቀብም እንቅፋት እንደሆነባቸው አስታውቀዋል።

እሁድ በቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ አዲሱ መገበያያ ገንዘብ ቬኔዙዌላ "የፋይናንስ ልውውጥ ለማድረግ እና ማዕቀቦቹን ለማለፍ የሚረዳ የገንዘብ ሉዓላዊነት እንዲኖራት ያደርጋል" ብለዋል።

"21ኛው ክፍለ ዘመን ደርሷል" ሲሉ በደስታ ለተቀበሏቸው ደጋፊዎች አስታውቀዋል።

አዲሱ መገበያያ ገንዘብ መቼ ወይም እንዴት በይፋ ተግባራዊ እንደሚደረግ አላሳወቁም።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የነዳጅ ምርት የሃገሪቱ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው

ውሳኔው ምናባዊ የሆነው እና ቢትኮይን የተሰኘው የመገበያያ ገንዘብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ፍላጎት መጨመሩን ተከትሎ የመጣ ነው።

140 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ ያለባት ቬኔዙዌላ አዲሱ መገበያያዋ የሆነውን ፔትሮስ ተጠቅማ ዕዳዋን ለመክፈል ማቀዷን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው።

ተቃዋሚ የፓርላማ አባላት በበኩላቸው አዲሱ መገበያያ ገንዘብ ኮንግረሱን ድጋፍ ይፈልጋል ሲሉ አንዳንዶች ደግሞ መሳካቱ ላይ ጥርጣሬ አላቸው።

"ማዱሮ ቀልደኛ እየሆነ ነው። ይህ ምንም ተዓማኒነት የለውም" ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑትና ተቃዋሚው ኤንጅል አልቫርዶ ለሮይተርስ የዜና ወኪል አስታውቀዋል።

የቬኔዙዌላ ኢኮኖሚ መሠረት ሆነው ነዳጅ ዋጋው ማሽቆልቆሉን ተከትሎ ሃገሪቱ ለኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ተጋልጣለች።

የሃገሪቱ መንግሥት የሚከተለው ጨቋኝ ፖሊሲ ነው በሚልም አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ማዕቀብ ጥለውባታል።

ባለፈው ወር ሩሲያ ቬኔዙዌላ ያለባትን 3.15 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ በረዥም ጊዜ እንድትከፍል የሚያስችላትን ስምምነት ተስማምተዋል።