የፕላስቲክ ብክለትን እንደሚያስቆም ተስፋ የተደረገበት ስምምነት

የፕላስቲክ ብክለት

ከጥቂት ቀናት በኋላ በሚደረገው የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ሃገራት ፕላስቲክ ቆሻሻዎች ባህሮችን እንዳይበክሉ የሚያስችሉ ጠንካራ ስምምነቶችን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በአካባቢ ደህንነት ላይ ትልቅ ችግር የሚያስከትሉት የፕላስቲክ ቁሳቁሶች የአካባቢ ጥበቃ ስምምነቶች ትኩረት መሆናቸውን ኤክስፐርቶች ይናገራሉ።

ስለዚህም ተስፋ በተጣለበት ስብሰባ ፕላስቲኮች የሚያስከትሉትን የአካባቢ ቀውስ የሚያስቆም ጠንካራ ስምምነት እንዲደረግ በኬንያ ናይሮቢ የከተሙት ልዑካን ዝግጅት እያደረጉ ነው።

ስምምነቶቹ በጠንካራ እርምጃ የሚታገዙ እንደሚሆኑም ይታመናል።

ልዑካኑ ፕላስቲኮችና ጥቃቅን ፕላስቲክ ነክ ቆሻሾች የሚያስከትሉትን ችግር ለመቅረፍ የሚረዱ አማራጮችንም እየተመለከቱ ነው።

አሜሪካ አሁን በውይይቱ ላይ ለመሳተፍ ፍቃደኝነቷን ብታሳይም እስካሁን ምንም አይነት ዓለም አቀፍ ስምምነት ላለማድረግ ወደ ኋላ ስትል ነበር።

ምን ያህል ፕላስቲኮች ከየት ተነስተው ወደ ባህር እየገቡ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎችን ማግኘት ለቀጣዩ እርምጃ ወሳኝ እንደሆነ የአካባቢ ጥበቃ ኤክስፐርቶች ይናገራሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ አ አ በ2025 የፕላስቲክ ቆሻሻን በጉልህ መልኩ መቀነስን ዓላማ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም እንደ ኖርዌይ ያሉ አገራት ደግሞ የረዥም ጊዜ እቅድ መሆን ያለበት ሙሉ በሙሉ የፕላስቲክ ችግርን ማስወገድ ነው የሚል የመፍትሄ ሃሳብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

ተያያዥ ርዕሶች