የእንግሊዝ የእርዳታ ገንዘብ በሶሪያ ለሚገኙ አክራሪዎች ውሏል ተባለ

Koknaya

የቢቢሲ ፓናሮማ ፕሮግራም የምርምር ዘገባን ተከትሎ የእንግሊዝ ታክስ ከፋዮች ገንዘብ ሶሪያ ለሚገኝ አክራሪ ቡድን ውሏል በሚል የእንግሊዝ መንግሥት አንድ የእርዳታ ፕሮጀክትን አግዷል።

በእንግሊዝ የሚደገፍ የሶሪያ ፖሊስ ሃይል በፍርድ ቤቶች ጣልቃ በመግባት አሰቃቂ የሚባሉ ፍርዶችንም እንደሰጡና ጫና ማድረጉንም ዘገባው ጨምሮ ያስረዳል።

ይህንን ዘገባ ተከትሎ የእንግሊዝ መንግሥት ቃል አቀባይ ለአሸባሪዎች የሚደረግ ትብብርን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያየው ተናግረዋል።

የታገደውን ፕሮጀክት እየሰራ እየተገበረ የነበረው አዳም ስሚዝ ኢንተርናሽናል የተባለው ድርጅት በበኩሉ ውንጀላውን ክዶታል።

ዘ ፍሪ ሲሪያን ፖሊስ ( የሶሪያ ፖሊስ ነፃ አውጪ) የተቋቋመው የሶሪያ አመፅን ተከትሎ ሲሆን አላማውም በተቃሚው ኃይል ቁጥጥር ስር የነበሩ ግዛቶች ላይ ህግና ስርአትን ማስፈን ነው።

አዳም ስሚዝ ኢንተርናሽናል ደግሞ ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ ይህንን ፕሮጀክት ሲቆጣጠር ነበር።

እንግሊዝን ጨምሮ ስድስት ሀገራት ለዚህ ፕሮጀክት የሚለግሱ ሲሆን አማፂያን በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች አሌፖ፣ኢድሊብና ዳራ ግዛቶች ላይ በፕሮጀክቱ አማካኝነት የማህበረሰብ ፓሊስ ስራ ይሰራል።

ዋና አላማው የነበረውም የሲቪል ፖሊስ ሃይልን ማሰማራትና ከአክራሪ ቡድን ጋር አለመተባባር የሚል ቢሆንም የቢቢሲ ፓናሮማ ዘገባ ግን ፕሮጀክቱ በተቃራኒው ከአክራሪ ቡድኑ ጋር ግንኙነት እንደነበረው አሳይቷል።

ዘገባው ፕሮጀክቱን ከወነጀለበት ምክንያቶች አንዳንዶቹም

  • ፖሊስ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የሞት ቅጣትን ከሚወስኑ ፍርድ ቤቶች ጋር የተባበረ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ሁለት ሴቶች በድንጋይ ተወግረው የተገደሉበት ፍርድ ይገኝበታል።
  • ለፖሊስ ገንዘብ መለገስ ይሄም ገንዘብ አካባቢውን ለሚቆጣጠረው አክራሪ ቡድን እንዲዘዋወር ማድረግ
  • የሞቱና የሀሰት ሰዎች በፖሊስ የደመወዝ ክፍያ ዝርዘር ውስጥ መካተት ይገኙበታል።

የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ፀሐፊ ቦሪስ ጆንሰን በባለፈው ሚያዝያ የእንግሊዝ መንግስት የሶሪያ ፖሊስ ነፃ አውጪ ለሚደግፈው 'አክሰስ ቱ ጀስቲስ ኤንድ ኮሚዩኒቲ ሴኩሪቲ' አራት ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚለግሱ አስታውቀው ነበር።

'አክሰስ ቱ ጀስቲስ ኤንድ ኮሚዩኒቲ ሴኩሪቲ' እንደሚለው ከሆነ የሶሪያ ፖሊስ ነፃ አውጪ መሳሪያን የማይታጠቅ ከማህበረሰቡ የተውጣጣ የፖሊስ ኃይል ሲሆን በጦርነት ፍርስርሷ ለወጣው ሃገር የህግ የበላይነትንና ለሚሊዮኖች ደግሞ ደህንነትን ለማስፈን በሚል የተቋቋመ ነው።

የዚሁ ድርጅት ቃል አቀባይም " የቢቢሲ ፓኖራማ ውንጀላን በፍፁም አንቀበለውም ፤ የታክስ ከፋዮችን ገንዘብ ሽብርን ለመከላከል፣ በጦር ዞን ውስጥ ለሚገኙ ማህበረሰቦች የደህንነት ከለላን ለመስጠት ነው ያዋልነው" ብለዋል።

"ድርጅቱ በፕሮጀክቱ ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን በጣም ፈታኝና ከፍተኛ አደጋ ባለባቸው አካባቢዎች መድረስ የቻለ ሲሆን ፕሮጀክቱ በውጭ ጉዳይ፣ በኮመንዌልዝ ቢሮና አምስት መንግስታት ትብብር የሚደገፍ ነው" በማለት ጨምረውም

ገንዘብ ለፖሊስ የሚለግሱት አማራጭ ስላልነበርና የእንግሊዝ መንግሥትም ስለ ክፍያዎቹ እንደሚያውቁ ይገልፃሉ።