ማልታ በካሩዋና ጋሊዚያ ግድያ 10 ሰዎችን አሰረች

Daphne Caruana Galizia arriving at a court in Malta, 27 April 2017 Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ካርዋና ጋሊዚያ የምርመራ ጋዜጠኛ ነበረች

የማልታ ፖሊስ ከጋዜጠኛ ዳፍኒ ካርዋና ግድያ ጋር በተያያዘ 10 ሰዎችን አስሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙስካት በማርሳ ፤ቡጊባና ዚቡግ አካባቢዎች ተጨማሪ የፖሊስ አሰሳዎች እንደሚደረጉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ካርዋና ጋሊዚያ ከሁለት ወራት በፊት ከቤቷ አቅራቢያ በቦምብ ጥቃት ነበር የተገደለችው።

ይህም በአገሪቱ ድንጋጤን ፈጥሮ ነበር።

የ53 አመቷ ካሩዋና ጋሊዚያ ፖለቲከኞችን በሚወነጅሉት ፅሁፎቿ ነበር የምትታወቀው።

መንግስት የካርዋናን ግድያ በሚመለከት መረጃ ለሚሰጥ የ አንድ ሚሊዮን ፓውንድ የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጥ አስታውቋል።

ኤፍ ቢ አይን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ኤክስፐርቶች በምርመራ እንዲያግዙም መንግስት ጥሪ አስተላልፏል።

በካሩዋና ግድያ የተጠረጠሩ ሰዎችን በማሰስ ሂደት መንገዶች ተዘግተዋል ፤ የቅኝት ጀልባዎችም ተሰማርተዋል።

ሙስካት እንደሚሉት ከተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከል የተወሰኑት ከዚህ ቀደምም በወንጀል የሚታወቁ ናቸው።

የተያዙት ስምንት ሰዎች በካርዋና ግድያ የተሳተፉ መሆናቸውን እንዲሁም የግድያው አቀነባባሪዎች ስለመሆናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ቀርቦላቸው መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

"እነዚህ ሰዎች እነማን እንደሆኑና ምን እንዳደረጉ ግልፅ መረጃ አለኝ፤ ነገር ግን በዚህ ጊዜ ዝርዝር መረጃ መስጠት አልችልም " ብለዋል።

'የማይፈሩ ጋዜጠኞች'

ካርዋና ጋሊዚያ በፅሁፎቿ በፓርቲዎች የተለያየ ደረጃ ላይ ያሉ የፖለቲከኞች ሙስናን በሚመለከት ያለመሰልቸት ትፅፍ እንደነበር ይታወቃል።

የቀድሞ የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ሉዊዝ ጋሊያ ለሶስት አስርት የዘለቀ ጋዜጠኝነቷን በመጥቀስ ካርዋናን "የማልታ በጣም ጠቃሚ፣ጉልህና ደፋር ጋዜጠኛ"ብለዋታል።

የቀብሯ ስነስርዐት ላይ በመቶ የሚቆጠሩ የተገኙ ሲሆን የአገሪቱ መሪዎች ግን ቀብሯ ላይ እንዳይገኙ ቤተሰቦቿ ከልክለዋል።

የካርዋና ሶስት ልጆች በነገሮች ደስተኞች አልሆኑም።

ይልቁንም ሙስካትን መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት አልቻሉም በሚል ወቅሰዋቸዋል።

ቢቢሲን ጨምሮ የስምንት ትልልቅ ሚዲያ አዘጋጆች፤ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ስራ አስፈፃሚ የካርዋናን ግድያ እንዲመረምሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በምላሹም የኮሚሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ፈራንስ ቲመርማንስ ከካርዋና ግድያ ምርመራ ጋር በተያያዘ የሚመለከታቸው አስፈላጊውን ነገር ሁሉ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ተያያዥ ርዕሶች