''ኢትዮጵያዊያንን የባሕር ላይ አደጋ መሞከሪያ ያደርጉ ነበር''

ሌንጮ አብዱልሰመድ Image copyright LENCHO ABDUSAMAD

የ20 ዓመቱ ሌንጮ በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ እስከ መሰናዶ ትምህርት ድረስ ተምሯል። "ብዙ ታሪክ አሳልፌያለሁ" የሚለው ሌንጮ አሁን ጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ነው የሚኖረው።

እንዴት ከሐገር ወጣ?

እ.ኤ.አ በ2014 በነበረው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ሰልፍ ላይ በመሳተፉ እስር ቤት ገባ። ከእስር ከወጣም በኋላ ለዳግም እስር ላለመዳረግ በማለት ከሀገር እንደወጣ ይናገራል። ከባሌ ሮቤ አዲስ አበባ ከዛም ባህር ዳር ተጓዘ። በመቀጠልም መተማ በመግባት የኢትዮጵያ ድንበርን አቋረጠ።

"ሱዳን እንደደረስን እስር ቤት አስገብተው ፀጉራችንን ላጩን፤ ከቤተሰቦቻችንም ብር እንድናስልክ አስገደዱን " ይላል ሌንጮ። የተጠየቀውን ገንዘብ ከፍሎ ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ በደላላ በሰሃራ በረሃ ውስጥ ለስድስት ቀናት ተጉዞ ሊቢያ ገባ። ደላላውም ለሚቀጥለው ደላላ አሳልፎ ሸጠው።

"ሶስት ጊዜ ለተለያዩ ነጋዴዎች ተሽጫለሁ"

"ሬሳና ፅም እያዩ መራመድ"

ከሱዳን የተነሱት 87 ኢትዮጵያውያን ነበሩ።

"በአንድ መኪና እስከ 50 የምንሆን ሰዎችን ጭነውን በሚሄዱበት ወቅት ከመኪናው ላይ የሚወድቁ ሰዎች ነበሩ፤ ሰው ወድቋል ብሎ ማቆም አይታሰብም። ዝም ብለው ይነዳሉ።" ከዚህ በተጨማሪ ይላል ሌንጮ "በሰሃራ በረሃ ውስጥ በምንሄድበት ወቅት የብዙ ሰዎች ሬሳ እና አፅም እየተመለከትን ነበር" በማለት ሐዘኑን ይገልፃል።

በሊቢያ አይዳቢያ በምትባል ከተማ ይዟቸው የመጣው ደላላ ሸጧቸው ሄደ። እነዚህም ደላሎች "ገንዘብ አልተከፈለላችሁም በማለት በትንሽዬ ኮንቴይነር ውስጥ ከተቱን" ይላል፤ ". . .ኮንቴይነሩ በጣም ትንሽ በር እንጂ መስኮት የሌለው ሲሆን ከአንድ መቶ በላይ የምንሆን ሰዎችን እዛ ውስጥ ከተቱን። የከፈሉ ሰዎች ከኮንቴይነሩ ሲወጡ ያልከፈልነው ግን እዛ ውስጥ ቀረን።" በማለት ያስታውሳል።

አጭር የምስል መግለጫ ከሱዳን የተነሱት 87 ኢትዮጵያውያን ነበሩ።

"ቀን በሐሩሩ የተነሳ መቆምም ሆነ መቀመጥ አስቸጋሪ ነው። ሌሊት ደግሞ ብርዱ አጥንትን ዘልቆ ይሰማል" ከዚህ በተጨማሪም ይላል ይህ ሌንጮ "ከሁለት እና ከሦስት ቀን በላይ እዛ ውስጥ ቆይተህ ስትወጣ ሰውነትህ ነጭ ይሆናል" በተጨማሪም በዚያ በረሃ ውስጥ ውሃ ማግኘት ህልም ነው ይላል።

"ውሃ ፊት ለፊትህ ያስቀምጡና ልጠጣ ስትል ይደፉታል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ተጨንቀን ከቤተሰቦቻችን ገንዘብ እንድናስልክ ነው።"

ሌንጮም ብር ሞልቶለት ከኮንቴይነሩ ውስጥ በህይወት መውጣት ቻለ። እድለኛ ያልሆኑ አራት ወጣቶች ግን ከነሌንጮ ተለይተው እዛው ቀሩ። ከዛም በኋላ ሌላ ደላላ መጥቶ በሜዲትራንያን ዳርቻ በምትገኘውና የሊቢያ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ትሪፖሊ ጉዞ ጀመሩ።

በላንድ ክሩዘር መኪና ላይ 'እንደ ሸቀጥ በመደራረብ' ለሌላ ደላላ አሳልፈው ሰጧቸው። እነዚህም ደላሎች የሱዳን፣ የኤርትራ እና የሱማሌ ወጣቶችን በመጨመር ከ200 በላይ የሚሆትን በጭነት መኪና ላይ አሳፈሯቸው።

የተጫኑበት መንገድ በጣም ዘግናኝ እንደነበር ሊንጮ ያስታውሳል። "ጭነት መኪናው ላይ ካሳፈሩን በኋላ ከላያችን ላይ እንጨት ረበረቡብን ከዛም እጆቻችንን ከተረበረበው እንጨት ጋር አሰሩት። ከዚያም በኋላ መኪናውን ሸራ አለበሱት። በዚህ ሁኔታ ውስጥ መተንፈስ ከባድ ነበር። አጠገቤ የነበረ ልጅ አረፋ ደፍቆ ሲሞት አይቻለሁ።"

በመሃል እነዚህ ወጣቶች ተጨንቀው ሸራውን በመበጣጠስ ጮሁ። ኬላ ላይም የሃገሪቱ ፖሊሶች ይዘዋቸው ወደ እስር ቤት አስገቧቸው። በዚህ እስር ቤትም ለአስራ አምስት ቀናት ቆዩ።

"ፈጣሪ ልባቸውን አራርቶልን ከእስር ተለቀቅን" ይላል ሌንጮ። ከዚያ ከወጡ በኋላ በባህር ላይ በማሻገር ወደ አውሮፓ የሚያደርሱ ደላሎች ጋር ተወሰዱ። እነዚህም ከሌሎቹ ደላሎች በምንም አይለዩም ነበር። 32ሺህ የኢትዮጵያ ብር እንዲከፍሉ ጠየቋቸው ።

"ቤተሰብ ደግሞ ልጆቻችን ከሚሞቱ ብለው ያላቸውን ጥሪት አሟጠው ይልኩልናል።"

Image copyright LENCHO ABDUSAMAD
አጭር የምስል መግለጫ "በሰሃራ በረሃ ውስጥ በምንሄድበት ወቅት የብዙ ሰዎች ሬሳ እና አፅም እየተመለከትን ነበር።"

ባርነት በእርሻ ቦታ

ከዚህ ጉዞ በኋላ ሌንጮ እና ሌሎች ወጣቶች አውሮፓ ለመግባት ያላቸው ህልም የቀረበ መሰላቸው። ተስፋቸው ግን ለረጅም ጊዜ አብሯቸው አልቆየም፤ በመሃል ያልታሰበ ነገር ተከሰተ።

"ወደ ባህር ጭነውን እየሄድን በነበረበት ወቅት እንደ ወታደር የለበሱ እና የታጠቁ ሰዎች መሃል መንገድ ላይ አስቆሙን።" ከነበሩበት መኪናም አስወርደዋቸው ወደሌላ መኪና ተዛወሩ። በበረሃ ውስጥ በግምት ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ እንደሄዱ የሚናገረው ሌንጮ ለሁለት ቀናት በአንድ ክፍል ውስጥ ቆይተው ወደ እርሻ ቦታ እንደወሷቸው ያስታውሳል።

"ቀኑን ሙሉ በእርሻ ውስጥ ሲያሰሩን ውሃ ስናጠጣ እንዲሁም ቆሻሻ ስንለቅም ውለን ማታ ገብተን ነው ምግብ የሚሰጡን።"

"አንድ ቀን ማሳው ውስጥ ደክሞኝ ብቆም በፌሮ መጥቶ ወገቤን መታኝ። ለብዙ ቀናት ታመምኩ" በማለት ያሳለፈውን ስቃይ ያስታውሳል።

ከ 15 ቀን በኋላ እነዚሁ የያዟቸው ሰዎች መጀመሪያ ያስቆሟቸው ቦታ መለሷቸው። በመጨረሻም ባህር ዳርቻ ደረሱ።

"መሞከሪያ አደረጉን"

እዚህም ክፉ ክፉ ነገር አይቻለሁ ይላል ሌንጮ። የሜዲትራኒያን ባህር ሞገዱ ፀጥ የሚልበት እና ለጉዞ ተስማሚ የሚሆንበት ወቅት አለ። በሌላ ጊዜ ደግሞ ሞገዱ የሚበረታበት እና ለጉዞ አስፈሪ ይሆናል። ያኔ መርከብም ሆነ ጀልባ ይገለብጣል የሰው ሕይወትም ይጠፋል።

አብዛኞቹ ስደተኞች ጉዞ የሚያደርጉት ባህሩ ሲረጋጋ እና ሞገዱ ፀጥ ሲል ነው። ሌንጮ አየሁ የሚለው ግን "ሞገዱ በሚያይልበት እና ለጉዞ አዳጋች በሚሆንበት ወቅት 85 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ተመርጠው ለሙከራ ብለው ጀልባ ላይ ጫኗቸው።"

አጭር የምስል መግለጫ ሌንጮ በድምሩ ከ103000 የኢትዮጵያ ብር ( 4000 ዶላር ) በላይ ለህገወጥ አዘዋዋሪዎችና ደላሎች ከፍሏል

ከሁለት ቀናት በኋላ እነ ሌንጮ ሲሰሙ እነዛ ልጆች ሁሉ ውሃ በልቷቸዋል። "የማውቃቸው ጓደኞቼም እዛ ውስጥ ነበሩ" ይላል ሌንጮ።

አራት ቀናትበባህር ላይ መንከራተት

ይህንን አሳዛኝ እና አሰቃቂ ዜና ከሰሙ በኋላ እነ ሌንጮ ለመሄድ በዝግጅት ላይ ነበሩ። ከእንጨት በተሰራች አንድ አነሰተኛ ጀልባ ላይ 410 ሰዎች በምሽት የባህር ላይ ጉዟቸውን ጀመሩ።

ሴቶችና ህፃናቶችም በጀልባዋ ላይ አብረው ነበሩ። ከብዙ መከራ በኋላ ተጉዘው ዓለም አቀፍ የውሃ ድንበር ላይ ሲደርሱ የነፍስ አድን ሰራተኞች በአካባቢው አልነበሩም።

ሌንጮ "ቀኑ እሁድ ስለነበር የነፍስ አድን ሰራተኞቹ ሥራ ላይ አልነበሩም። ጉዟችንን በመቀጠል አንድ መርከብ ስናይ ያድነናል ብለን ተስፋ ብናደርግም የአሳ አጥማጆች መርከብ ነበር" በማለት ያስታውሳል።

እንደዚህ እያሉ አራት ቀናትን በባህር ላይ አሳለፉ። በአራተኛው ቀን የነፍስ አድን ሰራተኞች መርከብ በመምጣት ወደ ጣልያን ወሰዷቸው። ከጥቂት ጊዜያት በኋላም ወደ ጀርመን ተሻገረ።

አሁን ላይ መለስ ብሎ ሲያስታውሰው "የሚሰቀጥጠኝ ሴቶች ላይ የሚደርሰው እንግልት ነው " ይላል።

ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ወጣት ሴቶች አብረዋቸው እንደነበሩ የሚናገረው ሌንጮ፤ እነዚህን ሴቶች ወስደው የፈለጉትን ነገር ያደርጓቸዋል። ተዉ ብሎ መሃል የሚገባ ካለ ይደበደባል። በማለት ከሰው ልጅ የማይጠበቅ ነገር እንደሚፈፅሙ በሐዘን ስሜት ውስጥ ሆኖ ያስረዳል።

ሌንጮ ከሃገር ወጥቶ የጣልያንን መሬት እስከሚረግጥበት ድረስ በድምሩ ከ103000 የኢትዮጵያ ብር (4000 ዶላር) በላይ ለህገወጥ አዘዋዋሪዎችና ደላሎች ከፍሏል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ