የዶናልድ ትራምፕ የጉዞ እገዳ ዕቅድ ተግባራዊ ሊሆን ነው

የትራምፕ የጉዞ እገዳ ዕቅድ ተግባራዊ ሊሆን ነው Image copyright AFP

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍድርድ ቤት ትራምፕ ከስድስት ሙስሊም ከሚበዛባቸው ሃገራት የሚመጡ ሰዎች ወደ ሃገራቸው እንዳይገቡ ያወጡት የጉዞ እገዳ ተግባራዊ እንዲሆን አዟል።

ውሳኔው ከቻድ፣ ኢራን፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ ሶሪያና የመን የሚመጡ ሰዎች ወደ ሃገሬ አይገቡም ሲሉ ትራምፕ የገቡትን ቃል ተፈፃሚነት እንደሚያረጋግጥላቸው እየተነገረ ይገኛል።

እገዳው ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ለሦስተኛ ጊዜ ያወጡት የጉዞ ማገጃ ዕቅድ ሲሆን ብዙ ተቃውሞ ገጥሞትም እንደበረ ይታወሳል።

ዕቅዱ ላይ ብይን ለመስጠት ከተቀመጡት ዘጠኝ ዳኞች መካከል ሰባቱ ዕቅዱ እንዲፀድቅ የደገፉ ሲሆን የተቀሩቱ ተቃውሟቸውን ገልፀዋል።

በቀጣይ. . .?

ምንም እንኳ ዕቅዱ ተግባራዊ እንዲሆን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ብይን ይስጥ እንጂ እገዳው አሁንም ብዙ እክሎች ከፊቱ እንዳሉ እየተነገረ ነው።

ሳን ፍራንሲስኮ፣ ካሊፎርንያ፣ ሪችሞንድና ቨርጂኒያ ግዛቶች ብይኑን በመቃወም ይግባኝ የጠይቁ ሲሆን የየግዛቶቹ ፍርድ ቤቶች ይግባኙን በዚህ ሳምንት ቀጠሮ ይዘዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኞቹ ተሰምተው ውሳኔ እንዲሰጥባቸውም አዟል። የይግባኝ መስማት ሂደቱ ከተከናወነ በኋላ በስተመጨረሻም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ብይን ይሰጥበታል።

የዕለተ ሰኞ ውሳኔ የአሜሪካ ከፍተኛ የሕግ አካል የሆነው ጠቅላይ ፍርድ ቤት አሁን ሥልጣን ላይ ያለውን አስተዳደር ሊደግፍ እንደሚችል ፍንጭ ሰጭ ነው ይላሉ ዳቪድ ሌቪን የተባሉ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሰር።

Image copyright Getty Images

የዋይት ሃውስ ቃል-አቀባይ ሆጋን ጊድሌይ የትራምፕ አስተዳደር በውሳኔው አለመገረሙን ተናግራዋል።

የአሜሪካው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጄፍ ሴሺንስ በበኩላቸው ውሳኔውን "ለአሜሪካውያን ደህንነት እጅግ አስፈላጊ ብይን" ሲሉ አሞካሽተውታል።

የአሜሪካው ሲቪል ሊበርቲስ ሕብረት ግን ትራምፕ ለሙስሊሞች የመረረ ጥላቻ ያላቸው ናቸው ሲል ይኮንናል፤ ባለፈው ሳምንት የእንግሊዝ ቀኝ ዘመም አክራሪ ሃይል በበይነ መረብ የለቀቀውን ምስል ፕሬዚደንቱ በትዊተር ገፃቸው ላይ ማጋራታቸውን በማስታወስ።

በቅርቡ በለንደን፣ ፓሪስ፣ ብራሰልስና በርሊን የደረሱትን አደጋዎች በማስታወስ፤ ትራምፕ ፖሊሲው አሜሪካንን ከሽብርተኞች በትር ይታደጋታል ሲሉ ይከራከራሉ።

የሕግ ሰዎች ግን ፖሊሲው በደህንነት ሽፋን ሙስሊሞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚደረግ ሤራ ነው ሲሉ ይሞግታሉ። በአብዛኛዎቹ ግዛቶች ያሉ ዝቅተኛ ፍርድ ቤቶች ዕቅዱን እንደተቃወሙትም የሚዘነጋ አይደለም።