እውነታው ሲጋለጥ፡ እውን 90 በመቶ ዚምባብዌያውያን ሥራ አጥ ናቸው?

እውን 90 በመቶ ዚምባብዌያውያን ሥራ አጥ ናቸው? Image copyright Getty Images

በእንግሊዝ ቤተ-ክርስትያን ሊቀ-ጳጳስ የሆኑት ጆን ሴንታሙ በዚምባብዌ 90 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች ሥራ አጥ ናቸው ሲሉ በቅርቡ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

የሃገሪቱ ስታትስቲክስ ቢሮ 2014 (እአአ) ላይ ባወጣው መረጃ መሠረት ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ ከሆኑ ዚምባብዌያውያን መካከል 11.3 በመቶ የሚሆኑት ሥራ አጥ ናቸው ይላል።

ይህ መረጃ ግን ከሚሰማው እጅግ ዝቅ ያለ ለመሆኑ ማስረጃ የሚሆነው ደግሞ በጎረቤት ሃገር ደቡብ አፍሪካ ከ15 ዓመት በላይ ከሆኑት ወጣቶች 24.9 በመቶ የሚሆኑት ሥራ አጥ መሆናቸው ነው።

አዳዲስ ሕግጋት

የስታትስቲክስ ቢሮው እንደሚገልፀው የ2014 አሃዝ ዝቅ ብሎ ሊታይ የቻለበት ምክንያት መረጃው በግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩትን ዜጎች ሥራ ያላቸው አድርጎ ስለመዘገበ ነው።

በአዲሱ የመረጃ አሰባሰብ ህግ መሠረት ግን በመሰል የሥራ መስክ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ሥራ አጥ ተብለው ነው የሚመዘገቡት ይላል ቢሮው።

ቢሮው በዚህ ዓመት ተመሳሳይ የመረጃ ስብሰባ ማካሄድ ቢኖርበትም በአቅም እጥረት ሳቢያ ለሚቀጥለው ዓመት ማቆየቱንም አስታውቋል።

የዓለም አቀፉ የሠራተኛ ድርጅት (ኤይኤልኦ) በበኩሉ በ2016 በሰበሰብኩት መረጃ በዚምባብዌ ከ15 ዓመታት በላይ ሥራ አጥ የሆኑት 5.2 በመቶ ብቻ ናቸው ይላል።

ያልተመዘገበ ምጣኔ ሃብት

ፎርብስ የተሰኘው የቢዝነስ ጋዜጣ በ2017 ወርሃ መጋቢት ባወጣው እትሙ "ሮበርት ሙጋቤ እንኳን ደስ ያሎት፡ ዚምባብዌ ውስጥ ሥራ አጥነት 95 በመቶ ደረሰ" ሲል መዘገቡ ይታወሳል።

ዓምደኛው 95 በመቶ የሚሆኑ ለሥራ ብቁ የሆኑ የዚምባብዌ ዜጎች ሥራ የለሽ ሆነው ተቀምጠዋል ሲል ሃሳቡን ያሰፍራል።

ነገር ግን መረጃው ከየት መጣ? ዓምደኛው መረጃውን ከዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንዳገኘው ይናገራል። ነገር ግን ኒው ዮርክ ታይምስ አሃዙ መደበኛ ባለሆነ ሥራ የተሰማሩ ሰዎችን ቁጥር የሚያሳይ እንጂ የሥራ አጥነት እንዳልሆነ ያስረግጣል። አሃዙም ከዚምባብዌ ስታስቲክስ ቢሮ እንደተገኘ ፅፏል።

መደበኛ ባልሆነ ሥራ ላይ የተሰማሩ መደበኛ ክፍያ የሌላቸው፣ በቤተሰብ ሥራ ላይ የተሰማሩ፣ የዓመት እረፍት መጠየቅ የማይችሉ ግለሰቦች እንደሆኑ ነው ቢሮው የሚያትተው።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያዋ ፕሮፌሰር ካትሪን ቡን ለአሃዞቹ መለያየት ዋነኛው ምንጭ መደበኛ ባልሆነ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች መብዛት ነው ይላሉ።

"በመደበኛ ሥራ ላይ ተሰማርተው በየወሩ ደሞዝ የሚከፈላቸውና ግብር የሚቆረጥባቸው ሰዎችን ብቻ የምንቆጥር ከሆነ ከፍተኛ የሥራ አጥነት አሃዝ ማግኘታችን እርግጥ ነው" ይላሉ ፕሮፌሰሯ።

መደበኛ ወዳልሆነው የሥራ መስክ ስንመጣ ግን በተቃራኒው ዝቅ ያለ አሃዝ ነው የምናገኘው ሲሉ ይሞግታሉ። ለምሳሌ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ በአማካሪነት የሚሰራ ሰው ሥራ ያለው ሆኖ ላይመዘገብ ይችላል በማለት ካትሪን ያስረዳሉ።

Image copyright Getty Images

የመንገድ ላይ ንግድ

የዚምባብዌ ሠራተኛ ማሕበራት ኮንግረስ የሥራ አጥነት አሃዙ 90 በመቶ ደርሷል ሲል ከተናገረ በኋላ፤ ተቃዋሚው ሞርጋን ሻንጋራይ "ሙጋቤ ሃገሪቱን ወደ መንግድ ላይ ንግድ ሥፍራነት ቀየሯት" ሲሉ መውረፋቸው ይታወሳል።

በመንገድ ላይ ንግድ የተሰማሩ ሰዎች ሥራ አጥ ናቸው? 90 በመቶ ሥራ አጥ ተብሎ ከተመዘገበ በመንገድ ላይ ንግድ የተሰማሩ ሰዎች ሥራ አጥ ወደሚባለው ምድብ ውስጥ መግባታቸው እሙን ነው።

የሥራ አጥነት መመዘኛን ለሃገራት የሚያወጣው የዓለም አቀፉ የሠራተኛ ድርጅት (ኤይኤልኦ) ዚምባብዌ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነው ነዋሪ፤ ሥራ አጥ የሚባለው ከሃቅ የራቀ እንደሆነ ይዘግባል። ነገር ግን በግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ከተካተተቡት በእርግጠኝነት ከ11.3 በላይ ነው ይላል።

አብዛኛዎቹ ዜጎች መደበኛ ባልሆነ የሥራ መስክ ላይ መሰማራታቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ አይኤልኦ ዚምባብዌ የሥራ አጥ ቁጥርን ከመቀነስ በላይ የዜጎቿን ሕይወት ማሻሻል ላይ ብትሰራ የተሻለ ነው ሲል ይመክራል።