የአምባገነኖች ሚስቶችን ለምን እንጠላለን?

President Robert Mugabe and his wife Grace pictured in August 2017 Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ግሬስ ሙጋቤ ከባለቤታቸው በላይ አደገኛ ተደርገው ተቆጥረዋል።

አምባገነን መሪን የምታገባ ሴት በእርግጠኝነት ሁለት ነገሮችን ታገኛለች፡ የተቀናጣ ኑሮ እና መጥፎ ስም።

በብዙሃን ዘንድ እነዚህ ሚስቶች ትችትን ያስተናግዳሉ።

ካላቸው የማይጨበጥ ባህሪ በተጨማሪ ዴሞክራሲን ከማይቀበሉ፣ የሃገራቸውን ኢኮኖሚ ከሚያቀጭጩ ወይም የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ከሚገድሉና ከሚያሸሹ ወንዶች ጎን ቆመዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው እነዚህ ሰዎች መሪዎቹን ቢጠሏቸው ማን ይወቅሳቸዋል።

ቀዳማዊ እመቤቶቹ እንደዚህ የሚጠሉት ግን ሴቶች ስለሆኑ ይሆን?

"ወደ አልተገባ መንገድ መርተውታል"

በቅርቡ ከስልጣን የለቀቁት ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ሚስት ግሬስ ሙጋቤ አፍሪካ ውስጥ ከሚጠሉ ቀዳሚዊ እመቤቶች የመጀመሪያዋ ሊሆኑ ይችላሉ።

ለ37 ዓመታት በስልጣን ላይ የቆዩት አምባገነን ባለቤታቸውን ለመተካት ፈልገው የነበረ ቢሆንም ጠንካራው ያገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ግን ይህ እንዳይሆን አድርጓል።

ብዙ ዚምባብያዊያን በሮበርት ሙጋቤ ላይ ቅሬታ ቢኖራቸውም ለሃገራቸው ነጻነት በሠሩት ሥራ ያከብሯቸዋል።

ባለቤታቸው ግሬስን ደግሞ ሙጋቤን "ወደ አልተገባ መንገድ መርተዋል" በሚል ይተቻሉ።

Image copyright Hulton Archive/Getty Images/Reuters
አጭር የምስል መግለጫ የሙጋቤ የቀድሞ ባለቤት ሳሊ (በግራ በኩል ያሉት) በበጎ ሲነሱ ግሬስ ግን ጠብ አጫሪ ተደርገው ይነሳሉ

በለንደኑ ኪንግስ ኮሌጅ መምህር የሆኑት ዶ/ር አሊስ ኤቫንስ ጉዳዩ አድልዎ መሆኑን ጠቅሰው ሰዎች ያላቸውን ዕምነት የሚያረጋግጡበት መረጃ እየፈለጉ ነው ይላሉ።

"ያለንን ርዕዮት የምናቆይበት መንገድ ነው። ለምሳሌ ሙጋቤ እንደ ጀግና ከተቆጠረ ሁሉም መረጃዎች ይህንን የሚደግፍ መሆን አለበት። ስለግለሰቡ መጥፎ መረጃ ካለንም ይህን ያደረገው ሌላ ሠው እንደሆነ እንገልጻለን" ብለዋል።

ግሬስ ሙጋቤ ችግር ፈጣሪ ናቸው። የሙጋቤ የቀድሞ ባለቤት ሳሊ ሃይፍሮን በከባድ ህመም ውስጥ እየተሰቃዩ እንኳን ከሙጋቤ ጋር ግንኙነት ነበራቸው።

ነባር የፖለቲካ ሰዎችን ከማንቋሸሽ ባለፈ በሆንግ ኮንግ እና ደቡብ አፍሪካ አካላዊ ጥቃት በማድረስም ተከሰዋል።

ሙጋቤ ጠቅላይ ሚንስትር ሲሆኑ እና ዚምባብዌ ነጻነቷን ስታገኝ 15 ዓመታቸው ነበር።

ከሶስት ዓመታት በኋላ ማታቤላንድ ላይ የአገሪቲ ደህንነት ሀይሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሲገደሉና ሲደፈሩ ግሬስ ዕድሜያቸው ገና ለመምረጥ መድረሱ ነበር።

ነገር ግን ግሬስን ከአይቮሪ ኮስት የቀድሞ ቀዳማዊ እመቤት ሲሞኔ ባግቦ ጋር አያወዳድሯቸውም።

ሲሞኔ ባለቤታቸው በምርጫ መሸነፋቸውን ተከትሎ የተነሳውን አመጽ ለማስቆም ራሳቸው የገዳይ ቡድን በማቋቋም ጦር መሳሪያ አስታጥቀዋል።

ዚምባብዌያዊያን ዋናውን ሰው መተቸት ሲያቅታቸውም ቀዳማዊ እመቤቷን መተቸትን ተግባራዊ አድርገውታል።

ውድ ኮቶች እና የዲዛይነር ጫማዎች

የግሬስ ሙጋቤ ቅጽል ስም "ጉቺ ሙጋቤ" ነው።

ይህ ቅጽል ስም ከፍተኛ ወጪ እንደሚያወጡ የሚያሳይ ነው።

አብዛኛውን ጊዜ የቀዳማዊ እመቤቶቹ ተግባር እንጂ እነሱን ለዚህ ያበቋቸው ወንዶች አይወቀሱም።

ከ20 ዓመታት በላይ የፊሊፒንስ ቀዳማዊ እመቤት የነበሩት ኢሜልዳ ማርኮስ ከአንድ ሺህ በላይ ጥንድ ጫማዎች እንደነበሯቸው የሚታወስ ነው።

እአአ በ1986 ፈርዲናንድ ማርኮስ በህዝባዊ አብዮት ከስልጣን ሲወርዱ ብዙ ፊሊፒናዊያን በድህነት ውስጥ ከመሆናቸውም በላይ ባዶ እግራቸውን ነበሩ።

Image copyright TED ALJIBE/AFP/Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ኢሜልዳ ማርኮስ አሁን በፊሊፒንስ ኮንግረስ አባል ናቸው

ሮማንያን ለሃያ አራት ዓመታት ከ1965 እስከ 1989 ድረስ የመሩት ኒኮል ሶሴስኩ ባለቤት የሆኑት ኤሌና ሶሴስኩ ከጫማቸው ይልቅ በኮቶቻቸው ይታወቃሉ።

ከቀበሮ፣ ከሜዳ አህያ፣ ከአቦ ሸማኔ እና ከነብር. . . ቆዳ የተሰሩ ኮቶች አሏቸው።

ለምን የቀዳማዊ እመቤቶች ቁሳቁሶች እና መዋቢያዎች እንደዚህ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሚስቡት?

ሌላው የሃገሪቱ ክፍል በችግር ሲሰቃይ ይህን መሰሉ ጉዳይ የሞራል ጥያቄ ያስነሳል።

እንደ ዶ/ር ኤቫንስ ከሆነ ደግሞ ስህተት በመሰራቱም ጭምር ነው ይላሉ። ከማይታወቁት የፓርቲ አባላትና የደህንነት ሰዎች በላይም በግልጽ ስለሚታወቁ ነው።

"ይቀለድባቸዋል"

የማይወደዱ ፖለቲከኛ ሚስቶች መጥፎ እንደሆኑ ተደርጎ ይሳላል።

የጋዜጣ አምደኞችና የዜና አውታሮች የመጀመሪያዋ መጥፎ ቀዳማዊ እመቤት ተደርገው ከሚወሰዱት ሌዲ ማካቤት ጋር ያወዳድሯቸዋል።

ኬንያ ውስጥ የቀድሞዋ ቀዳማዊ እመቤት ሉሲ ኪባኪ እአአ ከ2005 በኋላ ክብር አልሰጡንም ካሏቸው ዲፕሎማቶች እና ጋዜጠኞች ጋር ግጭት ውስጥ በመግባታቸው ጥሩ ስም አልነበራቸውም።

በአንድ አጋጣሚ ሉሲ ኪባኪ ጎረቤታቸው የነበሩትና በወቅቱ የዓለም ባንክ የኬንያ ዳይሬክተር የነበሩት ማክታር ዲዮፕ ባዘጋጁት ፓርቲ ላይ በእኩለ ለሊት ተገኝተው የሙዚቃው ድምጽ እንዲቀነስ ጠይቀዋል።

ተቃዋሚዎች ደግሞ ሚስታቸውን መቆጣጠር ያልቻሉ እንዴት ሃገር ይመራሉ በሚል ፕሬዝዳንት ምዋይ ኪባኪን ችግር ውስጥ ከተዋቸዋል።

"ሴቶችን በተለያየ መልኩ የመፈረጅ ጉዳይ አለ" ይላሉ የስነ-ጾታ መምህሯ ፕሮፌሰር ኢቫንስ ኤመሪቱስ።

"ለእነሱ አዲስ ስም መስጠት በጣም ቀላል ነው" ሲሉም ያስረዳሉ።

Image copyright STR/AFP/Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የኬንያ የቀድሞ ቀዳማዊ እመቤት ሉሲ ኪባኪ ለጋዜጠኞች ሲያወሩ

በቅርቡ እንኳን ግሬስ ሙጋቤን ከጌም ኦፍ ትሮን ገጸ-ባህሪ ሴርሲ ላኒስተር ጋር ያወዳደሯቸው አልታጡም።

አንዳንዶች ግን ያላቸውን ምኞት እንዳያሳኩ እንቅፋት የሆነባቸውን ነገር በመጋፈጥ የራሳቸውን ስብዕና አሳይተዋል ሲሉ ይከራከራሉ።

"ዚምባብዌ ውስጥ ሰዎች ሁሌም ግሬስ ሙጋቤን እንደግለሰብ ሲዳኟት ነበር፤ እየዳኟትም ነው" ሲሉ በጆሃንስበርግ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሰሊና ሙዳቫንሁ ይገልጻሉ።

"ዚምባብዌዊያን በተለየ ዓለም ውስጥ በመሆናቸው የማህበራዊ ሚዲያን ተጠቅመው ይተቻሉ። በስልጣን ላይ በነበሩበትና የዚምባብዌ ቀዳማዊ እመቤት ሆነውም የግብር ከፋዩን ብር ተጠቅመው ውድ ነገሮችን ያዘወትራሉ በሚል ስለእሳቸው ብዙ ቀልዶች ይወሩ ነበር" ይላሉ።

"የሃገሪቱ እናት"

ለአምባገነኖች ሚስቶች ለምን ጥላቻ ኖረን? እነሱ በተደጋጋሚ ሁለት ገጽታ ስላላቸው እና እኛም አልታመንም የሚል ስሜት ስላለን ነው።

"በፖለቲካ ውስጥ አልገባም፤ እኔ የህዝቡ ነኝ" ሲሉ የቀድሞዋ የቱኒዝያ ቀዳማዊ እመቤት ለይላ ቤን አሊ ገልጸዋል።

ለይላ በማጭበርበር ወንጀል 35 ዓመት የተፈረደባቸው ሲሆን 'ማይ ትሩዝ' የሚል መጽሐፍም ለህትመት አብቅተዋል።

ኤሌና ሶሴስኩ "የሮማንያ ምርጥ እናት" ተብለው በባለቤታቸው የኮሙኒስት መንግሥት ሲወደሱ ቢቆዩም "ትሎቹ የቱን ያህል ቢበሉም አይጠረቁም" ሲሉ "ልጆቻቸውን" መናገራቸው ተዘግቧል።

ሁለቱም ሶሴስኩዎች በ1989 የሞት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

የኤክስተር የኒቨርስቲ የስነልቦና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ቴክላ ሞርገንሮት እንደሚሉት ሴቶች ከጨካኞች ጋር ሲያያዙ የበለጠ ያስደነግጠናል።

Image copyright Keystone/Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ኤሌና ሶሴስኩ "የሮማንያ ምርጥ እናት" ተብለው በባለቤታቸው የኮሙኒስት መንግሥት ሲወደሱ ቆይተዋል

"ሴቶች ለስላሳ ናቸው ብሎ ከማሰብም በላይ የሞራል የበላይነት አላቸው ተብሎ እንደሚታሰብ የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ" ብለዋል።

ለባሻር አል አሳድ ባለቤት አስማ አል አሳድም በ2012 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጀርመን እና የእንግሊዝ አምባሳደር ሚስቶች በሃገሪቱ ያለውን ደም አፋሳሽ ጭቆና እንዲያስቆሙ ተማጽኖ ልከውላቸዋል።

በቪዲዮ በተለቀቀው ተማጽኖ ላይ ቆስለው በሞት አፋፍ ላይ የሚገኙ ልጆች ምስሎች የሚታዩ ሲሆን "እነዚህ ልጆች በሙሉ ያንቺ ልጆቹ ሊሆኑ ይችላሉ" የሚልም መልዕክት አለው ።

የሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት እ.አ.አ በ2011 ከተጀመረ በኋላ ቢያንስ 400 ሺህ ሰዎች መገደላቸው ይገለጻል።

የአምባሳደሮቹ ሚስቶች ተማጽኗቸውን ከማቅረባቸው ከወራት በፊት እና የመንግሥት ጦር ሆምስ ከተማ ላይ ጥቃት ከመክፈቱ በፊት አስማ አል አሳድ ድረ ገጽ ላይ አምስት ሺህ ዶላር የሚያወጣ ጫማ ሲመለከቱ እንደነበረ ያፈተለከ የኢሜይል መረጃ ይፋ አድርጓል።

ተያያዥ ርዕሶች