ስዊዘርላንድ በሳኒ አባቻ ዘመን የተዘረፈ ገንዘብ ለናይጄሪያ ልትመልስ ነው

አጭር የምስል መግለጫ የቀድሞ የናይጄሪያ ወታደራዊ መሪ ሳኒ አባቻ 2.2 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብ ከናይጄሪያ ማዕከላዊ ባንክ እንደዘረፈ ይታመናል።

የስዊዘርላንድ መንግሥት በሳኒ አባቻ ዘመን የተዘረፈ ነው የተባለ 320 ሚሊዮን ዶላር የመሚደርስ ገንዘብ ለናይጄሪያ ልትመልስ እንደሆነ አስታውቃለች።

ገንዘቡ በአውሮፓውያኑ 2014 ወደ ሳኒ አባቻ ልጅ አባ አባቻ ከመዛወሩ በፊት በስዊዝ ፍርድ ቤት እንዳይንቀሳቀስ እግድ እንደተጣለበት ይታወሳል።

320 ሚሊዮኑ ዶላር ከ1993 እስከ 1998 ባለው ጊዜ የቀድሞ የናይጄሪያ ወታደራዊ መሪ ሳኒ አባቻ ከናይጄሪያ ማዕከላዊ ባንክ ዘርፈውታል ከሚባለው ገንዘብ ኢምንቱ እንደሆነም ተነግሯል።

ናይጄሪያ በአባቻ ዘመን የተዘረፉ ያለቻቸውን ገንዘብ እና ንብረቶች ማስለመስ ላይ ትገኛለች። የወቅቱ የናይጄሪያ ፕሬዚደንት ሙሐሙዱ ቡሐሪ በአባቻ ዘምን የተዘረፉ ገንዘቦችን ማስመለስ ትልቁ አጀንዳቸው እንደሆነ 2015 ላይ የምርጫ ቅስቀሳ ቢሚያደርጉበት ወቅት ተናግረው ነበር።

የናይጄሪያ ፍትህ ሚኔስቴር፣ የዓለም ባንክ እንዲሁም የስዊዘርላንድ መንግሥት ከወርሃ መጋቢት ጀምሮ ገንዘቡን በማስመለሱ ጉዳይ ሲመክሩ እንደበረ አይዘነጋም። ነገር ግን ሕጋዊ ሂደቶች ዝውውሩን እያጓተቱት ይገኛል።

ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ ግን ዕለተ ሰኞ ሦስቱ አካላት ገንዘቡን ወደ ናይጄሪያ ባንክ በማስመለሱ ጉዳይ ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተሰምቷል።

ባለፉት አስር ዓመታት የስዊዘርላንድ መንግሥት ቢያንስ 700 ሚሊዮን ዶላር ለናይጄሪያ መክፈሉና አሀን ላይ የሚመለሰው 320 ሚሊዮን ዶላር ስዊዝ ውስጥ ከሚገኘው ገንዘብ የመጨረሻው ክፍያ እንደሆነም ታውቋል።

የናይጄሪያ መንግሥትና የዓለም ባንክ በሚደርሱት ስምምነት መሠረት ገንዘቡ ተከፋፍሎ በሃገሪቱ ያሉ የፋይናንስ ተቋማታን ለማገዝ ጥቅም ላይ እንደሚውልም ታውቋል።

ከዚህ ቀደም መሰል ገንዘቦች ሲመለሱ ቀጥታ ለመንግሥት የሚሰጥ ሲሆን አሁን ግን ልማት ላይ ማዋል ያስፈለገው ገንዘቡን ከዳግም ዝርፍያ ለመከላከል እንደሆነም ተነግሯል።

የስዊዘርላንድ መንግሥት በሕገ-ወጥ መልክ በሃገሪቱ ባንኮች ያሉ ሃብት ንብረቶችን በመመለስ ሥራ መጠመዱን አስታውቆ፤ መሰል ገንዘቦችን ለባለቤቶቹ የመመለሱ ሥራ ወደፊትም እንደሚቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ አትቷል።