ሩሲያ ከ2018ቱ የክረምት ኦሎምፒክ ታገደች

የፒዮንግቻንግ ኦሊምፒክ Image copyright Getty Images

ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከአበረታች መድሃኒት ጋር በተያያዘ ሩሲያ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት በፒዮንግቻንግ በሚደረገው ኦሊምፒክ ውድድር ላይ እንዳትሳተፍ እገዳ ጣለባት።

ነገር ግን አበረታች መድሃኒት አለመውሰዳቸውን ማረጋገጥ የሚችሉ የሩሲያ ሯጮች የሩሲያን ሳይሆን ነፃ ሰንቅ ዓላማ አንግበው መሳተፍ እንደሚችሉ ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል።

ይህ እገዳ እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 በሩሲያ ሶቺ ተዘጋጅቶ በነበረው ውድድር ላይ በመንግሥት እውቅናና ድጋፍ ስፖርተኞች አበረታች መድሃኒት ወስደዋል በሚል ምርመራ መደረጉን ተከትሎ ነው።

"ከዚህ ጥፋት በኋላ ጉልህ መስመር ማስመር ያስፈልጋል" ብሏል ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ።

የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውሳኔ በመላዋ ሩሲያ ተወግዟል። አንዳንድ ፖለቲከኞች ደግሞ ኦሊምፒክ ውድድሩ ላይ ጨርሶ አለመሳተፍ ያስፈልጋል በማለት ውትወታ ላይ ናቸው። ሌሎች ደግሞ ንፁህ ለሆኑ ሯጮች የመሳተፍ እድል መሰጠቱን በአዎንታዊነቱ ተመልክተውታል።

የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባህና ቦርዱ ውሳኔውን ማክሰኞ እለት በሎዛን ሲያስተላልፉ መጀመሪያ ላለፉት 17 ወራት በቀድሞ የስዊዘርላንዱ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ሽሚድ መሪነት የተደረገው የምርመራ ግኝትና ምክረ ሃሳብን በሙሉ ካነበቡ በኋላ ነው።

ውሳኔውም በግልፅ ያስቀመጠው የሩሲያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መታገዱን፤ ነገር ግን ንፁህ ሯጮች "ሯጭ ከሩሲያ ኦሊምፒክ" ተብለው እንዲሳተፉ እንደሚጋበዙ ነው።

ምንም እንኳ ሩሲያ በተደጋጋሚ ብታስተባብልም የሺሚድ ሪፖርት ግን ሩሲያ የፀረ አበረታች መድሃኒት ህጉን በመተላለፍ ከአራት ዓመት በፊት ሯጮች አበረታች መድሃኒት እንዲወስዱ መንግሥት ነገሮችን ማመቻቸቱን ይጠቁማል።

የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባህ "የሩሲያ ድርጊት የኦሊምፒክ ውድድሮችና የስፖርትን ክብር የሚነካ ነው። ስለዚህም ውሳኔው ለወደፊቱ አበረታች መድሃኒት ላይ ጠንካራ አቋም ለመያዝ የሚያስችል፤ ለደረሰው ጥፋትም የማያዳግም መስመር የሚያሰምር መሆን አለበት"ብለዋል።

በደቡብ ኮሪያዋ ፒዮንግቻንግ የሚካሄደው ኦሊምፒክ ውድድር እንደ አውሮፓውያኑ የካቲት ዘጠኝ የሚጀምር ሲሆን የስፖርቱ ማማ የሆነችው አገር ሩሲያ በሌለችበት የሚካሔድ ይሆናል።

የሩሲያ አሎምፒክ ኮሚቴ ለምን ታገደ?

ምርመራውና ሁሉም ነገር የጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 የሶቺ ውድድር ወቅት የሩሲያ ፀረ አበረታች መድሃኒት ቤተሙከራ ዳይሬክተር የነበረው ዶክተር ግሪጎሪ ሮድቼንኮቭ ነገሩን የይፋ ማውጣቱን ተከትሎ ነው።

ዶክተሩ በአገሪቱ የተቀናጀ ለስፖርተኞች አበረታች መድሃኒት የመስጠት አሰራር እንዳለ እሱም አበረታች መድሃኒቶችን ማዘጋጀቱን፤ በምርመራ እንዳይደረስበትም የሽንት ናሙናዎችን ያቀያይር እንደነበር ተናግሯል።

ዓለም አቀፉ ፀረ አበረታች መድሀኒት ኤጀንሲ (ዋዳ) ደግሞ የካናዳ የህግ ፕሮፌሰር እና የስፖርት ጠበቃው ዶክተር ሪቻርድ ማክላረን ጉዳዩን እንዲመለከቱት አድርጓል።

የማክላረን ሪፖርት እንደ አውሮፓውያኑ ከ2012 እስከ 2015 በተለያየ ስፖርት ውስጥ የነበሩ አንድ ሺህ ሯጮች አበረታች መድሃኒት እንዲጠቀሙ ከማድረግ እቅዱ ተጠቃሚ ሆነዋል።

ከሩሲያ ስፖርት ቤተሙከራ የወጣ ነው ተብሎ ዋዳ የደረሰው መረጃ ከማክላረን ድምዳሜ ጋር የሚጣጣም ነው። በውጤቱም በርካታ ሯጮች በቀደመ መረጃ ሁሉ እንዲታገዱ ተደርጓል። ሜዳሊያዎችም ተነጥቀዋል።

ባለፈው ሳምንት ደግሞ በስዊዘርላንዳዊው ጠበቃ ዴኒስ ኦስዋልድ የሚመራው የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሌላ ኮሚሽን ደግሞ ከዶክተር ሮድቼንኮቭ ለተገኘው መረጃ ምሉዕ ትንታኔ ሰጥቷል።

ተያያዥ ርዕሶች