ፌስቡክን ለልጆች?

ልጆች የቪድዮ መልዕክት መቀያየር Image copyright FACEBOOK
አጭር የምስል መግለጫ ልጆች ከጓደኞቻቸውና ፍቃድ ካላቸው ትልቅ ሰዎች ጋር የቪድዮ መልዕክት መቀያየር ይችላሉ

ማህበራዊ ድረ-ገጾችን ለመጠቀም ትንሹ ዕድሜ ስንት መሆን አለበት?

በእርግጥ ፌስቡክን ዕድሜያቸው 13ና ከዚያ በላይ የሆኑት ብቻ ነው እንዲጠቀሙ የሚፈቀደው።

ሆኖም ይህንንም ለመቆጣጠር ከባድ በመሆኑ ዕድሜያቸው ከ13 ዓመት በታች የሆኑ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ይጠቀሙበታል።

ለዚህም ነው ባለፈው ሰኞ ፌስቡክ ለልጆች ታሰቦ የተሠራን መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) ያቀረበው።

የወላጆችንን ፈቃድ የሚጠይቁ ከባድ የዕድሜ መቆጣጠሪያ መንገዶችንም ዘርግቷል።

ይህ 'ሜሴንጀር ኪድስ' የተሰኘው መተግበሪያ ዕድሜያቸው ከ13 በላይ ለሆኑት ከቀረበው ይልቅ ለአጠቃቀም ቀለል ያለ ነው።

''ወላጆች ልጆቻቸው ዘመናዊ ስልኮችንና የተለያዩ ዘመናዊ መሣሪያዎችን እንዲጠቀሙ በይበልጥ እየፈቀዱላቸው ይገኛሉ'' ይላሉ የ'ሜሴንጀር ኪድስ' ሥራ አስኪያጅ ሎረን ቼንግ።

''እናም እንደዚህ አይነት መተግበሪያዎች ለልጆቻቸው ታስበው እንዲሠሩ በውይይቶችና በጥናት ከወላጆች ጥያቄ ሲቀርብልን መሥራት እንደነበረብን እርግጠኛ ሆንን'' ብለዋል።

ፈቃድ ያሏቸው ጓደኞች

ሁለት ልጆች በ'ሜሴንጀር ኪድስ' ጓደኛሞች መሆን ቢፈልጉ የሁለቱም ወላጆች ፈቃድ መስጠት ይኖርባቸዋል።

ከጥቃትና ከችግር ነፃ መሆናቸውንም ሲያረጋግጡ ልጆቹ ከጓደኞቻቸው ጋር በቀጥታ በቪድዮ መነጋገርና ፎቶግራፎችና የጽሑፍ መልዕክቶችን መቀባበል ይችላሉ።

Image copyright FACEBOOK
አጭር የምስል መግለጫ የወላጆች ፈቃድ ማስፈለጉ የልጆቹን ደህንነት ይጠብቃል

መልዕክቶቻቸውንም በሚላላኩበት ጊዜ ከማንነታቸው ጋር የሚሄዱና በፈለጉት ሥዕላዊ መግለጫዎች እንዲገዙ ለልጆች ታስበው የተዘጋጁ 'ጂፍ'ና'ሰቲከር' የተሰኙ ይዘቶችን ይዟል።

ፈቃድ ያገኙ አዋቂዎችም ቢሆኑ ከልጆቹ ጋር መልዕክት መለዋወጥ ይችላሉ።

እነሱ ግን መልዕክቱን በነባር የፌስቡክ መልዕክት ሳጥን ነው የሚያገኙት።

ቀጣዩ ትውልድ

ፌስቡክ ይህን አዲስ መተግበሪያ ለዋናው ማህበራዊ ድረ-ገጽ የመረጃ ምንጭ እንደማይሆን ቃል ገብቷል።

ፌስቡክ ሊያገኝ የሚችለው ጥቅም ለወላጆች የታሰቡ ማስተዋወቂያዎችን በዚህ መተግበሪያ በመላክ ነው።

ካለበለዚያ ደግሞ ወጣቶችን ዒላማ ያደረጉ ማስተዋቂያዎችን በመልቀቅ ልጆቹ 13 ሲሞላቸው ወደ ዋነኛው ፌስቡክ እንዲሸጋገሩ ያደርግ ይሆናል።

ፌስቡክ ግን የተፈሩት ነገሮች እንደማይፈጠሩ ተናግሯል። መተገበሪያው የልጆቹን ዕድሜ እንደማያውቅና ሲያድጉ ወደ ዋነኛው ፌስቡክ እንደማይገፋቸው ገልጿል።

ልጆቹ ግን ዕድሜያችው ሲደርስ የፌስቡክ ማህበራዊ ገጽ መክፈት ቢፈልጉ እንኳ ከ'ሜሴንጀር ኪድስ' ጋር የማይያያዝ አዲስና እራሱን የቻለ እንደሚሆን ተናግረዋል።

Image copyright FACEBOOK
አጭር የምስል መግለጫ ፌስቡክ ያካተታቸው ሥዕላዊ ይዘቶች ለልጆች አዝናኝ እንደሚሆኑ ይገመታል

መውደድ

እራሳችንን መጠየቅ ያለብን ልጆች ከህፃንነታቸው አንስቶ ማህበራዊ ድረ-ገጾችን መጠቀም አለባቸው ወይ የሚለው ነው?

የፌስቡክ ቀዳሚ ኢንቨስተርና የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሻን ፓርከር ለማቋቋም ስላገዙት አገልግሎት አፍራሽ ሃሳቦችን አቅርበዋል።

''በልጆቻችን አዕምሮ ምን እንደሚመላስ የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው'' በማለት በፌስቡክ ላይ የምናጋራቸውን ይዘቶች ሌሎች መውደዳቸውን 'ላይክ' በማድረግ በሚያሳውቁበት ጊዜ በአዕምሮአችን ምን አይነት ስሜቶችን እንደሚፈጥርብን አስታውሰዋል።

ይህ የመውደድ ወይንም 'ላይክ' የማድረግ መሣሪያ የ'ሜሴንጀር ኪድስ' ዋናው አካል ነው።

ለዚህም ነው ዕድሜያቸው ከ6 ዓመት ጀምሮ ያሉ ልጆችን በዚህ መልኩ የአቻዎቻቸውን ተቀባይነት መለኪያ ማድረጉን እንደ ሕብረተሰብ ልናስብበት ይገባል ብለዋል።

'መልካሙ ሃሳብ --በፊ ላይ '

ለፌስቡክ ሥራም ጊዜያዊ የሆነ ተቀባይነት አለ። የብዙሃን ስሜትም ልጆች በድብቅ እነዚህን ማህበራዊ ድረ-ገጾች እየተጠቀሙ ስለሆነ ይህን መቆጣጠር በሚቻልበት መንገድና በማይጎዱበት ሁኔታ መመቻቸቱ ተገቢ ነው ብለዋል።

ኮመን ሴንስ ሚድያ የተሰኘው የልጆችንና የቤተሰብን ሕይወት የማሻሻል ዓላማ የያዘና ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት በልጆች የሚዘወተሩ የማህበራዊ ድረ-ገጽ አጠቃቅም ላይ ጥናት አካሂዷል።

''ላይ ላዩን ወላጆች ብቻ መመዝገብ የሚችሉበት ለ13 ዓመት በታች ላሉ ልጆች ታስቦ የተዘጋጀ ጥሩ ድረ-ገጽ ነው'' በማለት የድርጅቱ ዋና አስተዳዳሪ ጄምስ ስቴየር ተናረግዋል።

በመቀጠልም ''ግልጽ የሆነ የመረጃ መሰብሰቢያ ህግ ከሌለ ግን ልጆቹ የሚያጋሯቸው ይዘቶች ምን እንደሚደረጉ ስለማይታወቅ ሙሉ በሙሉ ለማመን ከባድ ይሆናል'' ብለዋል።

''ለጊዜው ይህን ገጽታውን እንወደዋለን ምክንያቱም ማስተዋወቂያ የለውም በዚያ ላይ ቁጥጥሩ ሙሉ በሙሉ በወላጆች እጅ ነው። ሆኖም ወላጆች ፌስቡክ ለልጆቻቸው በማሰብ ብቻ እንደሠራው እንዴት ማወቅ ይችላሉ?'' በማለት ይጠይቃሉ።

ፌስቡክም ቢሆን አዲሱ አገልግሎት ልጆችን ተጋላጭ ስለሚያደርግ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ከመግለጽ አልተቆጠበም።

ለልጆች ጎጂ የሆነ ማንኛውም ይዘት በ'ሜሴንጀር ኪድስ' ላይ ቢገኝ ለፌስቡክ ትልቅ ችግር እንደሚያስከትልም ያውቃል።

ዩቲየብም ለልጆች ታስቦ በተዘጋጀው 'ዩቲዩብ ኪድስ' ገጻቸው ላይ ለልጆች ጎጂ የሆኑ ይዘቶች በማምለጣቸው መቆጣጠሩ ከባድ እንደሆነ በልምድም ታይቷል።

ይህ መተግበሪያ ለጊዜው በአሜሪካ ያውም የአይኦኤስ ሲስተም ላላቸው ተገልጋዮች ላይ ብቻ የቀረበው ነው።

ተያያዥ ርዕሶች