የኮንጎ ቀውስ ከመካከለኛው ምስራቅ እንደሚያይል እየተነገረ ነው

More than seven million people are struggling to feed themselves, aid workers say Image copyright AFP

በአህጉረ አፍሪካዋ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰተው የእረስ በርስ ግጭት መፈናቀልን ካስከተሉ ግጭቶች ሁሉ የከፋ ነው ሲሉ የእርዳታ ድርጅቶች አሳሰቡ።

ሃገሪቱ ታጣቂዎች መንግሥትን ከሥልጣን ለማውረድ ትግል ከጀመሩ ወዲህ ሰላም አጥታ ቆይታለች።

በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ባለፈው ዓመት ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ቢጠበቅም ሳይሳካ በመቅረቱ ወደ ከፋ አረንቋ እንድትገባ አድርጓታል።

"በመካከለኛው ምሥራቅ በተለይ ደግሞ በኢራቅ፣ የመንና ሶሪያ ግጭትን ሸሽተው ከሚሰደዱ ሰዎች በላይ በኮንጎ መኖሪያቸውን ጥለው የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር እጅግ እያየለ ነው" ይላሉ የኖርዌይ እርዳታ ድርጅት የኮንጎ ኃላፊ ኡልሪካ ብሎም።

በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት እንደሚየሳየው በያዝነው ዓመት ብቻ ቢያንስ በየቀኑ 5 ሺህ ሰዎች መኖሪያቸውን ጥለው ይሰደዳሉ።

ለዚህም እንደ ዋነኛ ምክንያት እየተጠቀሱ ያሉት አዳዲስ ግጭቶች፣ የነባር ግጭቶች ማገርሸትና ምርጫው ባለመካሄዱ ምክንያት የተከሰተው ፖለቲካዊ ሽኩቻ ነው።

እስካሁን 4 ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያቸው ከመፈናቀላቸውም በላይ 7 ሚሊዮን የሚሆኑ የኮንጎ ዜጎች የምግብ እርዳታ እንደሚያሻቸው ነው ኃላፊዋ የሚያስረግጡት።

"አሁኑኑ ፈጥነን ምላሽ መስጠት ካልቻልን የከፋ ረሃብ ተነስቶ የሰው ሕይወት እንደ ቅጠል መርገፉ አይቀሬ ነው" ሲሉም ያስጠነቅቃሉ።

Image copyright NRC/CHRISTIAN JEPSEN

የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የማስታወቂያ ሚኒስትር ላምበርት ሜንዴ ግን የእርዳታ ድርጅቶቹን ስጋት ችላ በማለት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በታች ነው ይላሉ።

ሚኒስትሩ ለቢቢሲ 'ፎከስ ኦን አፍሪካ' ዝግጅት እንደተናገሩት "እየወጡ ያሉ ዘገባዎች ሃሰት ናቸው፤ ይልቁንም ዜጎች ከተሰደዱበት እየተመለሱ ናቸው" ብለዋል።

ዓለም የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክን ጉዳይ ፊት ነስቶታል ይላል የቢቢሲው ጄምስ ኮፕናል። ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ይላል. . ."ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ያለውን ቀውስ የሚዘግቡ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሃገሪቱ ውስጥ የሉም።"

"ወጣም ወረደ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እንደ ሶሪያ ያለ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትም ሆነ ተፈላጊነት የላትም፤ ለዛም ነው ዓለም ፊት የነሳት" ሲልም ይከራከራል።

ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የሰፊ ግዛት ባለቤትና በርካታ የተፈጥሮ ሃብት ያላት ሃገር ብትሆንም ለተከታታይ ዓመታት በሃገሪቱ የተከሰተው ግጭት ሰዎች በድህነት እንዲማቅቁና መሰረት ልማቶች እንዳይስፋፉ አድርጓል።

በአውሮፓውያኑ 2001 ላይ በተገደሉት አባታቸው ሎረንት ካቢላ ቦታ ተተክተው ሥልጣን የያዙት ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ ሁለት ጊዜ ምርጫ ቢያሸንፉም ለሦስተኛ ጊዜ ለመወዳደር ሕገ-መንግስቱ አይፈቅላቸውም።

ተቺዎች ምርጫው የተጓተተው ካቢላ በሥልጣን እንዲቆዩ ታስቦ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

የመንግሥት ተቃዋሚዎች ይበዙበታል ተብሎ በሚታሰበው ማዕከላዊ ካሳይ በተከሰተ ግጭት እስካሁን 400 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።