ኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ከቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም የማዛወር ዕቅድ የላትም

መለስ ዓለም

በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጠው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት የሊቢያ ስደተኞችን፣ የኢትዮ-ግብፅ ግንኙነት እንዲሁም የእየሩሳሌምን ጉዳይ ዋነኛ ትኩረቶቹ አድርጎ አርፍዷል።

በሊቢያ እየተካሄደ ባለው የባርያ ንግድ ዙሪያ ለተጠየቁት ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት የመሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም "የአውሮፓና የአፍሪካ ሕብረቶች በደረሱት ስምምነት መሠረት የሊቢያ መንግሥት በሃገሪቱ እየተከናወነ ያለውን የባርያ ንግድ ማስቆም ግዴታው ነው" ብለዋል።

ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሃገራት በተናጠልም ሆነ በጋራ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ እንደማይሉ አሳስበዋል።

"ሊቢያ ውስጥ በባርነት ከተሸጡት ስደተኞች መካከል ኢትዮጵያውያውን እንዳሉ ደርሰንበታል" ያሉት ቃል አቀባዩ "ሊቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያንን የመለየቱ ሥራ ተጠናቆ አሁን ላይ ሰነድ የመስጠት ሂደት ላይ ነን፤ በፈቃዳቸው መሠረትም ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ዝግጁ ነን" ሲሉ ተደምጠዋል።

በባርነት ንግድ ላዩ ከተሰማሩ ሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች መካከል ኢትዮጵያውያን እንዳሉበትም መጣራቱን አሳውቀዋል።

ኢትዮጵያና ግብፅ ስላላቸው ግንኙነት በተጨማሪ የተናገሩት አቶ መለስ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ወደ ካይሮ እንደሚያቀኑና በሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ዙሪያ እንደሚመክሩ ጠቁመዋል።

ኃይለማርያም ካይሮ መጥተው በሃገሪቱ ፓርላማ ንግግር እንዳያደርጉ 19 የግብፅ ፓርላማ አባላት ፊርማ ማሰባሰብ ላይ መሆናቸውን ያሳወቁት ቃል አቀባዩ "ከ600 በላይ አባላት ባሉት ፓርላማ 19 ሰዎች መሰል ሂደት መጀመራቸው የሚያሳስብ አይደለም" ብለዋል።

በሌላ በኩል ከኅዳር 6/2010 ጀምሮ ሳዑዲ ሕጋዊ ወረቀት የሌላቸውን ዜጎች ከሃገሯ እያስወጣች እንደሆነ ያሰመሩት አቶ መለስ እስከ ኅዳር 26 ባለው ጊዜ ከ10 ሺህ ባለይ ኢትዮጵያውያንን መንግሥት ማስመለሱን፤ ባለፈው ጊዜ የተመለሱትን ደግሞ መልሶ የማቋቋም ሥራ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።

በስተመጨረሻም ከሰሞኑ አበይት በሆነው የእየሩሳሌም ጉዳይ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ መለስ ""የፕሬዚዳንት ትራምፕ ውሳኔ የአሜሪካ ነው፤ እኛን የሚመለከተን ጉዳይ አይደለም" ብለዋል።

"በእስራኤልና ፍልስጤም ጉዳይ ኢትዮጵያ የምትደግፈው ሁለቱም የየራሳቸውን ራስ ገዝ አቋቁመው በሰላም ይኑሩ የሚለውን ነው" ይላሉ አቶ መለስ።

ኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ከቴል-አቪቭ ወደ እየሩሳሌም የማዛወር እቅድ እንደሌላት የተናገሩት ቃል አቀባይ አቶ መለስ "ኢትዮጵያና የአፍሪካ ሕብረት በሁለቱ ሃገራት መካከል ላለው አለመግባባት ሰላምን እንደብቸኛ አማራጭ ይወስዳሉ" ሲሉ መግለጫቸውን ደምድመዋል።