አሜሪካ ከፍልስጤም ጋር ልታካሂድ አስባ የነበረውን ውይይት አቋርጣለሁ ስትል አስጠነቀቀች

"Pence you are not welcome", says graffiti in the West Bank city of Bethlehem Image copyright AFP/GETTY IMAGES

ምክትል ፕሬዚደንት ማይክ ፔንስ ከፍልስጤሙ መሪ መሐሙድ አባስ ጋር ሊያደርጉት ያሰቡትን የሰላም ድርድር ልትሰርዝ እንደምትችል አሜሪካ አስጠነቀቀች።

አንድ የፍልስጤም ከፍተኛ ባለሥልጣን ማይክ ፔንስ በፍልስጤም ተቀባይነት የላቸውም ማለታቸውን ተከትሎ ነው ማስጠንቀቂያው የመጣው።

ትራምፕ አሜሪካ ለዘመናት ስትከተል የነበረውን ፖሊሲ በመሻር እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና መዲና ናት በማለት እውቅና መስጠታቸው ይታወሳል።

ከእወጃው በኋላ ጋዛ ሰርጥ እና ዌስት ባንክ አካባቢ በተነሳ ግጭት ቢያንስ 31 ፍልስጤማውያን መቁሰላቸውም ታውቋል። የተቃውሞ ሰልፉ እንደሚቀጥልም ነው እየተነገረ ያለው።

የፍልስጤሙ እስላማዊ ቡድን 'ሃማስ' ከትራምፕ እወጃ በኋላ እንደ አዲስ አመፅ እንዲነሳ ቅስቀሳ ማካሄዱን ተያይዞታል።

እስራኤል በበኩሏ በመቶ የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ወደ ዌስት ባንክ አሰማርታለች።

በርካታ የአሜሪካ አጋር ሃገራት የትራምፕን ውሳኔ የተቃወሙት ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምከር ቤት እንዲሁም የአረብ ሊግ በውሳኔው ላይ መክረው አቋማቸውን በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ምክትል ፕሬዚደንት ማይክ ፔንስ ወደ ፍልስጤም በማቅናት ከአባስ ጋር በቀጣናው ሰላም በማስፈን ዙሪያ እንደሚመክሩና እስራኤልና ግብፅንም እንደሚጎበኙ ተነግሮ ነበር።

ነገር ግን ጂብሪል ራጆብ የተባሉ የፋታህ ፓርቲ ነባር አባል "ፔንስን ለመቀበል በራችን ክፍት አይደለም" ሲሉ ተደምጠዋል።

ሙሐሙድ አባስ በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ምንም ያሉት ነገር የለም።

እየሩሳሌም በክርስትና፣ እስልምና እንዲሁም አይሁድ እምነቶች ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣት ቦታ ስትሆን፤ እስራኤል ከስድስት ቀናቱ ጦርነት በኋላ ከተማዋ የእኔ ናት ብትልም ዓለም አቀፍ እውቅና ሳታገኝ ቀርታለች።

በእስራኤል ኤምባሲ ያላቸው ሁሉም ሃገራትም መቀመጫቸውን ቴል አቪቭ ማድረግ መርጠዋል።

አሜሪካ እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ናት ስትል ያወጀች የመጀመሪያዋ ሃገር ሆናለች።