ዩናይትድ ከሲቲ. . . ማን ያሸንፍ ይሆን?

ዩናይትድ ከሲቲ. . . ማን ያሸንፍ ይሆን? Image copyright Clive Brunskill

ማንችስተር ሲቲ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ከጀመረ ወዲህ የመጀመሪያውን ሽንፈት በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ አስተናግዷል። በፕሪሚዬር ሊጉ የመጀመሪያውን ሽንፈት ከዩናይትድ ጋር በሚኖረው ጨዋታ ያስተናግድ ይሆን?

የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ማርክ ላውረንሰን "በኦልድትራፎርድ የሚኖረው አየር ሞቅ ያለ ነው የሚሆነው" ይላል። ላውሮ ይህንን ጨምሮ የሌሎች ጨዋታዎችን ግምትም እንዲህ አስቀምጧል።

ቅዳሜ

ዌስትሃም ከቼልሲ

Image copyright BBC Sport

ባለፈው ሳምንት ከሲቲ ጋር ጨዋታውን ያከናወነው ዌስትሃም አቻ መውጣት የሚችልበትን ዕድል አምክኗል። በጨዋታው ዌስትሃም የነበረው አቋም ጥሩ ከመሆኑም በላይ ለዴቪድ ሞዬስ እጅግ አስፈላጊ ውጤት ይሆን ነበር።

የሰማያዎቹ አሠልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ የጨዋታ መደራረብ ቡድኔን እየጎዳው ነው ሲሉ ይሰማሉ፤ ከአርሴናል፣ ሲቲ፣ ሊቨርፑልና ዩናይትድ የላቀ ጨዋታ ባያደርጉም።

ዌስትሃም ለቼልሲ ፈታኝ እንደሚሆን አስባለሁ።

የላውሮ ግምት፡ 1 - 1

በርንሌይ ከዋትፎርድ

Image copyright BBC Sport

በርንሌዮች በሌይስተር 1 - 0 ከተሸነፉበት ጨዋታ ቢያንስ አንድ ነጥብ ሊያገኙ በተገባ ነበር። ነገር ግን ከነጥቡም በላይ አስከፊው ዜና እጅግ አስፈላጊ ተጫዋቻቸው ሮቢ ብራዲን በጉዳት ማጣታቸው ነው።

ባለፈው ሳምንት በ10 ሰው እየተጫወተ የነበረውን ቶተንሃም ማሸነፍ ያልቻሉት ዋትፎርዶች በዚህ ጨዋታ ይቀናቸዋል ብዬ አላምንም።

የላውሮ ግምት፡ 2 - 0

ክሪስታል ፓላስ ከቦርንማውዝ

Image copyright BBC Sport

ሮይ ሆጅሰን የአሰልጣኝነት መንበሩን ከተቆናጠጡት ወዲህ ፓላስ ቀስ በቀስ መልካም የሚባል ውጤት እያመጣ ነው፤ ከሰንጠረዡ ግርጌም መነሳት ችሏል።

ቀጣይ የሚሆነው ከወራጅ ቀጣና መውጣት ነው። በዚህ ሳምንት እንኳን ባይሆን በሚቀጥሉት ሳምንታት እንደሚሆን ግን አምናለሁ።

በቦርንማውዝ በኩል የሚያሳስበኝ ነገር ወጥ የሆነ አቋም አለማሳየቱ ነው። ቢሆንም ይወርዳሉ ብዬ ግን አላስብም።

የላውሮ ግምት፡ 2 - 1

ሃደርስፊልድ ከብራይተን

Image copyright BBC Sport

ሃደርስፊልዶች አራተኛ ተከታታይ ጨዋታቸውን ተሸንፈዋል። ከአንድ የውድድር ዘመን በኋላ ወደታችኛው ሊግ መልሰው ይንሸራተቱ ይሆን የሚለው ጥያቄም መነሳት ጀምሯል።

ብራይተንም በተመሳሳይ ከነበረበት ሥፍራ መንሸራተት ጀምሯል። በዚህ ወቅት የማስበው አሠልጣኞቹ ላይ ሊኖር የሚችለውን ጫና ነው።

ሁለቱም ክለቦች ሶስት ነጥብ ለማግኘት ብለው ቁማር ውስጥ እንደማይገቡ እምነቴ ነው።

የላውሮ ግምት፡ 1 - 1

ስዋንሲ ከዌስት ብሮም

Image copyright BBC Sport

ዌስት ብሮሞች ላለፉት 14 ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻሉም። ነገር ግን ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ደግሞ ሽንፈት አላስተናገዱም።

ስዋንሲዎች በበኩላቸው ካፉት ሰባት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ነው ማግኘት የቻሉት፤ ወደ ሰንጠረዡ ግርጌም ተወርወርዋል።

የላውሮ ግምት፡ 1 - 1

ቶተንሃም ከስቶክ

Image copyright BBC Sport

ስቶክ ባለፈው ሳምንት ባደረገው ጨዋታ 1 - 0 ከመመራት ተነስቶ ሶስት ነጥብ ማግኘት ችሏል፤ ትንሽም ቢሆን ከመንሸራተት ድኗል።

ቶተንሃም ምንም እንኳ ከሰሞኑ ነጥብ እየጣለ ቢገኝም መልሶ እንደሚያንሰራራ ግን ምንም ጥርጥር የለውም።

የላውሮ ግምት፡ 2 - 0

ኒውካስል ከሌይስተር

Image copyright BBC Sport

ኒውካስል ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ነው ማግኘት የቻለው።

ሌይስተር በአንፃሩ በርንሌይን በማሸነፍ በክላውድ ፑየል ዘመን ጥሩ ለውጥ ማምጣት ችሏል።

ቀበሮዎቹ አሁን ላይ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን የሚመጥናቸው ቦታ ላይ እንደሚገኙ አስባለሁ። ነገር ግን ኒውካስል ይህንን ጨዋታ እንደሚረታ ግምቴ ነው።

የላውሮ ግምት፡ 2 - 1

እሁድ

ሳውዝሃምፕተን ከአርሴናል

Image copyright BBC Sport

ከቦርንማውዝ ጋር ጨዋታ የነበረው ሳውዝሃምፕተን ከኋላ ተነስቶ አቻ መለያየት ችሏል። አሁንም ከአርሴናል ጋር የሚኖረውን ጨዋታ በአቻ ውጤት እንደሚያጠናቅቅ እገምታለሁ።

ዩናይትድ የአርሴናልን አጥር እንደፈተነው ሳውዝሃምፕተን ይፈትናል ብዬ ባላምንም ጎል እንዲቆጠርባቸው ያደርጋሉ የሚል እምነትም የለኝም።

የላውሮ ግምት፡ 1 - 1

ሊቨርፑል ከኤቨርተን

Image copyright BBC Sport

ኤቨርተን አዲስ አሠልጣኝ ቀጥሯል፤ ሳም አላርዳይስን። ካለፉት ሶስት ጨዋታዎች ሁሉንም ማሸነፍም ችሏል።

ጨዋታው እጅግ ፍትጊያ የሚበዛበት እንደሚሆን ባስብም ሊቨርፑል በተቻለው መጠን የግብ ክልሉን እንደሚያስጠብቅ ነው የሚሰማኝ።

የላውሮ ግምት፡ 2 - 0

ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ማንቸስተር ሲቲ

Image copyright BBC Sport

ፖል ፖግባ በዚህ ወሳኝ ጨዋታ ላይ አይሳተፍም፤ ዳቪድ ሲልቫም እንደማይሰለፍ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም ማገገሙ ታውቋል። ለዩናይትድ ጥሩ ዜና የሚሆነው የተከላካዩ ቪንሴንት ኮምፓኒ አለመሰለፍ ነው።

በዚህ ጨዋታ ወሳኙ ነገር ሞርኒሆ ይዘውት የሚገቡት ታክቲክ ነው። እቅዱን ከብዙ ጨዋታዎች በፊት ጀምሮ እንደሚያስቡበት አልጠራጠርም። ለዚህም ነው ግምቴ ወደ ዩናይትድ የሚያደላው።

ላውሮ፡ 2 - 1