ካለሁበት 13፡ ''ለእኔ ስኬት ማለት ገንዘብ ማግኘት ብቻ አይደለም''

አብዱልሰላም ጠንካራ ሰራተኛ ሲሆን ሕይወቱን ለመለወጥ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፏል Image copyright ABDULSELAM ABAJEBEL
አጭር የምስል መግለጫ አብዱልሰላም ሕይወትን ለማሸነፍ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፏል

አብዱሰላም አባጀበል እባላለሁ በአሜሪካ በኒው ዮርክ ከተማ የ'ኦሲስ ጅማ ጁስ ባር' ባለቤት ነኝ።

ተወልጄ ያደኩት በጅማ ከተማ አካባቢ ልዩ ስሙ ሸቤ በሚባል ቦታ ነው።

ዕድሜዬ ለትምህርት ሲደርስ ሸቤ ትምህርት ቤት በመግባት እስከ 7ኛ ክፍል ድረስ ተምሬያለሁ። ከዚያም ሌላ ቦታ እስከ 8ኛ ክፍል ለመማር ዕድሉን ባገኝም በአባቴ ሞት ምክንያት ትምህርቴን ለማቋረጥ ተገደድኩ።

ያደኩት በሰፊ ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን ከእናቴና አባቴ የተወለዱ 14 እህትና ወንድሞች ሲኖሩኝ ወደ 30 የሚጠጉ ደግሞ የጉዲፈቻ እህቶችና ወንድሞች አሉኝ።

አባቴ ሰዎችን ሰብስቦ ማብላትና ማጠጣት ይወዱ ነበር። ነገር ግን ሲሞቱ ያሁሉ እየጠፋ መምጣት ጀመረ።

ከ8ኛ ክፍል ወደ ክሊኒክ ባለቤትነት

ትምህርቴን በማቋረጥ ቤተሰቦቼን ለመርዳት ስል ሥራ መፈለግ ጀመርኩኝ። በመጀመሪያም ሳዶ ወደምትባል አካባቢ በመሄድ ከአባቴ ባገኘሁት የሕክምና ሞያ ክሊኒክ ከፈትኩኝ። የተወሰነ ያህል ከሠራሁኝ በኃላ መንግስት ፈቃድ የለህም ስላለኝ ክሊኒኩን ዘግቼ ለመሄድ ተገደድኩኝ።

ሆኖም ግን ወደ ቤተሰቦቼ አልተመለስኩም። ሠርቼ ገንዘብ አገኝበታለሁ ብዬ ወዳሰብኩት በባህላዊ መንገድ ወርቅ ወደሚቆፈርበት ዲማ ወደሚባለው አካባቢ አመራሁ።

እንዳጋጣሚ ሆኖ ብዙ ወርቅ ላገኘ ወዲያው ሃብታም የመሆን ዕድል አለ የሚል ነገር በልጅነቴ ሰምቼ ነበር። እኔም የሆነ ነገር አግንቼ ራሴን አሻሽላለሁ በሚል ሃሳብ ተነሳስቼ በ16 ዓመቴ ወደ ዲማ አቀናሁ። የተባለበት ቦታ ስደርስ ግን የሚወራውና እውነታው በጣም የተለያየ ነበር።

ምግብ ቤት ላላቸው ሰዎች ከወንዝ ውሃ ከመቅዳት እስከ በረሃ ወርዶ ወርቅ ፍለጋ ድረስ ታግያለሁ። እንዲሁም ምግብ ሠርቼ ለሌሎች በማቅረብና የጤና ችግር ያለባቸውን ከአባቴ ሥር ሆኜ በቀሰምኩት እውቀት በማገልገል በማገኘው ገቢ ኑሮዬን ለማሸነፍ ጥረት አድርጌ ነበር።

በዚያ አይነት ሁኔታም ለአንድ ዓመት ከሠራሁ በኋላ በአካባቢው ችግር በመከሰቱ ዲማን ለመልቀቅ ተገደድኩኝ።

ልጅ ነህ

ዲማ በነበርኩበት ሰዓት በሱርማና በአኝዋክ ሕዝቦች መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ጓደኞቼን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ተገደሉ። ስለዚህ በቡሌ ሆራ፣ ቦረና ከዚያም በጉጂ አቆራርጬ ወርቅ ወደሚቆፈርበት ሌላ ቦታ ወደ ሻኪሶ አቀናሁ።

ነገር ግን እዚያ አብሬያቸው እቆፍር የነበሩ ሰዎች 'አንተ ልጅ ነህ፥ አካፋ እንኳን ማንሳት አትችልም' በማለት አባረሩኝ። ስለዚህ ሌላ መላ ማግኘት ነበረብኝ።

ቁፋሮው በሚካሄድበት ቦታ ምግብ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ስለነበረ እነሱ ለምግብ የሚያስፈልገውን ካቀረቡልኝ እኔ እያበሰልኩ 30 ሰዎችን መግቤ በጋራ የሚገኘውን ገቢ እኩል ለመካፈል ሃሳብ አቀረብኩኝ፤ እነሱም ተስማሙ።

በዚህ አይነት በቀን 3 ጊዜ ለ30 ሰዎች ምግብ በማብሰል ከእነርሱ እኩል የተገኘውን በመካፈል ሠራሁኝ። ከ6ወራት በኋላ ግን በአካባቢው ከነበረው አለመመቻቸት የተነሳ ወደሌላ ሃገር በመሄድ የተሻለ ሕይወት ለምን አንኖርም በማለት ከጓደኞቼ ጋር መነጋገር ጀመርን።

መነጋገር ብቻ ሳይሆን በጅቡቲ በኩል አቆራርጠን ወደ ዐረብ ሃገር ለመግባት መንገድ ጀመርን። ከ5 ወራት ውጣ ውረድ በኋላም በየመን በኩል ሳዑዲ ገባን። ይሁን እንጂ ከረዥሙ ጉዞ በኋላ የሳዑዲ ድንበር ላይ እንደደረስን የሳዑዲ ፖሊሶች ይዘውን ወደ ኢትዮጵያ መለሱን።

ወደ ሰው ሀገር ሄዶ የመስራት እቅዴ ሳይሳካ ቀረ። ነገር ግን ተስፋ አልቆረጥኩም። ጊዜዬን ሳላባክንም ወደ ኬንያ አቀናሁ።

እዚያም ስደርስ የሰው እጅ ላለመጠበቅ ስል የተለያዩ ሥራዎችን ሠርቼአለሁ።

ለ5 ዓመታትም የወንዶች የፀጉር ማስተካከያ ቤት በመክፈትና ከተጣሉ ቁሳቁሶች የጠረጴዛ ቴኒስ መጫወቻ በመሥራት ገቢ ለማገኘት ታትሬያለሁ።

ከ5 አድካሚ የጥረት ዓመታት በኋላ እኤአ በ2004 በተባበሩት መንግሥታት ጥገኝነት ለሚጠይቁ ሰዎች በሚዘጋጀው የቤተሰብ ማገናኛ መርሃ ግብር አማካይነት ወደ አሜሪካ ኒው ዮርክ ከተማ መምጣት ቻልኩ።

Image copyright ABDULSELAM ABAJEBEL
አጭር የምስል መግለጫ የአብዱልሰላም ምግብ አፍቃሪዎች

ከራስ አልፎ ለሌሎች መትረፍ

አሜሪካ ስገባ የልቤ ሃሳብ በሙሉ የተፈጸመ መስሎኝ ነበር፤ ነገር ግን እውነታው የተለየ ነበረ። እንዲያውም ለተወሰኑት የመጀመሪያ ወራት አየሩ፣ ሃገሩና ቋንቋው አዲስ ከመሆኑ የተነሳ ግራ እጋባ ነበር። በኋላ ግን ቀስ በቀስ ተላመድኩት።

ሥራ ለመጀመር ግን ሃገሩንና ቋንቋ በመልመድ ጊዜ ማባከን አልፈለኩም።

ሠርቼ ራሴን ለመለወጥ ባለኝ ከፍተኛ ፍላጎት አሜሪካ በገባሁ በ2ኛው ቀን በልብስ ንፅህና መስጫ ቤት ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩኝ። ከዚያም በኒው ዮርክ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለያዩ የሥራ መደቦች ላይ ሠርችያለሁ።

በመጨረሻም ለአየር መንገድ የአውሮፕላን ነዳጅ ቀጂ ሆኜ እሠራ ነበር። ከዚያ በኋላ እንዴት ራሴን ችዬ ሌሎችን ልርዳ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሰዎችን ማማከር ጀመርኩኝ።

ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች 'አንተ አልተማርክም እንዲሁም ገንዘብ የለህም' እያሉ ቅስሜን ሊሰብሩ ይሞክሩ ነበር።

እኔ ግን በውስጤ የነበረውን ሃሳብ ለማሳካት ጠንክሬ መሥራቱን ቀጠልኩኝ። ባገኘሁት ሰዓት ሁሉ አጫጭር ስልጠናዎችን መውሰድ እና መፅሃፍ ማንበብ ቀጠልኩ።

ከዛ በኋላ ነው እንግዲህ በ2012 'ኦሲስ ጅማ ጁስ ባር' የተሰኘውን ጭማቂ ቤት መክፈት የቻልኩት።

በቀጣዩም ዓመት ኒው ዮርክ ውስጥ የሚገኝ ምርጥ ጭማቂ ቤት በመባል የሶስተኝነት ደረጃ በማግኘት የምስክር ወረቀት አግኝቻለሁ።

ከዛም ወዲህ ድርጅቴ በየዓመቱ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን እየያዘ መጣ። አሁን ታዲያ ዓለም አቀፍ ስምና ዝና ያለው ድርጅት መሆን በምችልበት ሁኔታ ላይ እየሰራሁ ነው።

የስራዬ ዋና አላማ ገንዘብ ማግኘት ብቻ አይደለም። ሰዎች ጤናማ ምግብ ማግኘት እንዳለባቸው አስባለሁ።

እኔም ራሴ ከአመጋገብ የተነሳ ለስኳር በሽታ የተጋለጥኩበት አጋጣሚ ነበር።

ጤናማ ምግቦች ደግሞ እንዲህ አይነት የጤና እክሎችን ለመቆጣጠር ወይም ለመቀነስ ትልቅ ሚና አላቸው።

Image copyright ABDULSELAM ABAJEBEL
አጭር የምስል መግለጫ በአብዱልሰላም ጭማቂ ቤት የሚቀርቡት ምግቦች በከፊል

ወደ ትምህርት ቤቶች፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ የህብረተሰብ ማእከላት በመግባት የራሴን ተሞክሮ እና ሰዎች እንዴት ጤናማ የሆነ ምግብ መመገብ እንደሚችሉ የተለያዩ የልምድ ልውውጦችን አደርጋለሁ።

በአሁኑ ሰዓት ለአስር ሰዎች የአጭር እና የረዥም ጊዜ የስራ ዕድል መፍጠር ችያለሁ። እዛው ኒው ዮርክ ውስጥ ሁለተኛ ጭማቂ ቤት ከፍቻለሁ፤ በካናዳም እንደዚሁ።

በተለያዩ ግዛቶች እና እዚህ ክፈት የሚል ጥያቄ እየቀረበልኝ ስለሆነ የመጪው አመት እቅዴ የእኛ ሰዎች ወደሚገኙበት እየሄድኩ ቅርንጫፎቼን አስፋፍቼ ለበርካቶች የስራ እድል መፍጠር ነው። ሀገር ቤት ሄዶ መክፈትም ምኞቴ ነው።

በተጨማሪ ደግሞ ኦሲስ ፓወር ሐውስ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅቴ መስከረም 29 2017 ተመርቆ አገልግሎት ጀምሯል።

የዚህ ድርጅት ዓላማ የተለያዩ ሙያ ያላቸው ሰዎች ልምድ እና እውቀታቸውን መመር ለሚፈልጉ ሰዎች ያለክፍያ እንዲያሰለጥኑ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው።

በዚህ ማዕከል ከኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ እና ከሲቲ ኮሌጅ ጋር በጋራ በመሆን ነው የምንሰራው፤ ከተቋማቱ የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች እየመጡ ልምዳቸውን ያካፍላሉ።

ሁሉም ሰው በተፈጥሮው ሙሉ ሆኖ የተፈጠረ ቢሆንም ካሰብነው ቦታ እንዳንደርስ ማህበረሰቡ ተፅእኖ ያደርግብናል።

የምንሰራውን ነገር ከግብ ለማድረስ የሚያስፈልገው ዋናው ነገር በራስ መተማመን እንዲሁም ሌሎችን አለማውቀስ፣ እና ከሰዎች አለመጠበቅ ናቸው።

አሁን የምወደውን ስራ እየሰራሁ ነው። ለዛም ነው የተሳካልኝ። ለኔ ስኬት ማለት ገንዘብ ማግኘት ብቻ አይደለም። የሚወዱትን እየሠሩ ሌሎችን ማገዝ ነው ለኔ ስኬት ማለት።

ገንዘብ በየትኛውም መንገድ ሊገኝ ይችላል፤ እውነተኛ ሕይወትን መኖር ግን ከገንዘብ ይበልጣል።

ለበለጡ ቡልቡላ እንደነገራት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦

ካለሁበት 14፡ "ብርዱ ሲከፋ፣ ቀኑም ሲያጥር የሀገሬ አየር በስንት ጣዕሙ እላለሁ።"

ካለሁበት 15፡ "ራሴንና ልጆቼን የሰሜን ተራሮች ላይ ባገኝ በጣም ደስ ይለኝ ነበር"

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ