ኔታንያሁ፡ ፍልስጤማውያን የእየሩሳሌምን እውነታ መቀበል አለባቸው

ቤንጃሚን ናታንያሁ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ፍልስጤማውያን እየሩሳሌም የእስራኤል መዲና መሆኗን አምነው ወደ ሰላም ሂደቱ ቢመጡ ይሻላል ብለዋል።

ቤንጃሚን ኔታንያሁ እንዳሉት እየሩሳሌም ለ3000 ዓመታት የእስራኤል መዲናነቷ የቀጠለች ሲሆን የሌላ የማንም ዋና ከተማ ሆና አታውቅም ብለዋል።

ይህንን የተናገሩት አሜሪካ እየሩሳሌምን በእስራኤል ዋና ከተማነት ዕውቅና ከሰጠች በኋላ የሙስሊሙና የአረቡ አለም በተቃውሞ እያናወጡ ባለበት ወቅት ነው።

ግጭቶችም ሊባኖስ በሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ተቀስቅሰዋል።

በእየሩሳሌምም አንድ ፍልስጤማዊ አንድ ወታደርን የአውቶብስ ማረፊያ አካባቢ በስለት ከወጋ በኋላ በቁጥጥር ስር ውሏል።

በፓሪስ ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ኔታንያሁ እንዳሉት "አይሁዳውያንን ከእየሩሳሌም ጋር ያላቸውን ግንኙነት መካድ አስቂኝ ነው" ብለውታል።

በተጨማሪም " በያንዳንዱ ምርጥ መፅሀፍ ላይ ታሪኩን ማንበብ ይቻላል። ይሄም መፅሀፍ መፅሀፍ ቅዱስ ነው። ከሀገር ውጭ ባሉም የአይሁዳዉያን ማህበረሰብ ታሪኩን መስማት ይቻላል። የእስራኤል መዲና ታዲያ የት ነው? እየሩሳሌም እንጂ"

"ፍልስጤማውያንን ይህንን እውነታ ቢረዱት ወደ ሰላም የምናደርገው ጉዞ በቅርቡ ይሆናል" ብለዋል።

በተያያዘም ዜና የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ቃል አቀባይ ማይክ ፔንስ የፍልስጤም ባለስልጣናትን በከፍተኛው ተችተዋል።

ይህንን ትችትም ያቀረቡት የፍልስጤሙ ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ ማይክ ፔንስ ወደ አካባቢው በሚመጡበት ወቅት ሊያደርጉት የነበረውን ስብሰባ በመሰረዛቸው ነው።

በግብፅም ከፍተኛ የሚባሉ የሙስሊምና የክርስትና መሪዎች የአሜሪካን ውሳኔ ተከትሎ ከማይክ ፔንስ ጋር ተይዞ የነበረውን ውይይት ሰርዘዋል።