አንጋፋው ኤርትራዊ ደራሲ የ2017 የሞርላንድ የሥነ-ጽሑፍ ተሸላሚ ሆኑ

አለምሰገድ ተስፋይ Image copyright MMF

አንጋፋው ኤርትራዊ ጸሐፊ አለምሰገድ ተስፋይ የሞርላንድ የሥነ-ጽሑፍ ስኮላርሺፕ አሸናፊ ከሆኑት አምስት አፍሪካውያን ጸሓፊዎች መካከል አንዱ ሆነዋል።

አቶ አለምሰገድ የኤርትራ ታሪክን በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንዲጽፉ ያስችላቸው ዘንድ £22,500 ፓውንድ አሸንፈዋል።

ሽልማቱ የሰጠዉን እንግሊዝ አገር ተቀማጭነቱን ያደረገው ማይልስ ሞርላንድ ፋውንዴሽን (ኤምኤምኤፍ) ተብሎ የሚጠራው ማህበር ሲሆን ከ550 ተወዳዳሪዎች አምስት አፍሪካውያን ጸሐፊዎች በልጠው በመገኘታቸው ለሽልማቱ መብቃታቸው ተገልጿል።

መመዘኛው በጣም የላቀ እንዲሁም ውድድሩ ከፍተኛ ስለነበር ሌላ ጊዜ እንደሚደረገው ለአራት አሸናፊዎች ሳይሆን ዳኞቹ አምስት ተወዳዳሪዎችን መሸለም እንደወሰኑም ማህበሩ አክሎ ገልጿል።

የተቀሩት አራት ጸሐፊዎች ድግሞ ብሪዮኒ ርሂም ከዚምባብዌ፣ ኤልናታን ጆንና ኢሎጎሳ ኦሱንደ ከናይጀርያ፣ እና ፋጢማ ኮላ ከደቡብ አፍሪካ ናቸው።

ለእነዚህም አሸናፊዎች የፈጠራ ሥራዎች የሚውል 18 000 ፓውንድ ለእያንዳንዱ አሸናፊ ተሰጥቷል።

አቶ አለምሰገድ በትግርኛና በእንግሊዝኛ የሚጽፉ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪ ናቸው።

የተለያዩ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎችን አበርክተዋል።

ለሕትመት ከበቁ ዋነኛ ሥራዎቻቸው 'አይንፈላለ (አንለያይም) 1941-1950'፤ ፌደረሽን ኤርትራ ምስ ኢትዮጵያ ካብ ማትዮንሶ ክሳብ ተድላ ባይሩ 1951-1955' (የኤርትራ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር ከማትዮንሶ እስከ ተድላ ባይሩ 1951-1955)፤ 'ኤርትራ ድሕሪ-ቃልሲ (ኤርትራ ከትግል በኋላ) የሚሉት ይገኙባቸዋል።

ከታሪካዊ ሥራዎቻቸው በተጨማሪ በኤርትራ አንባብያን የሚታወቁ በርካታ የልብወለድ ሥራዎችን አፍርተዋል ከእነዚህም ውስጥ በእውነተኛ የሕይወት ታሪክ የተመረኮዘው 'ወዲ ሓደራ' (የአደራ ልጅ) አንዱ ነው።

አሸናፊዎቹ ለዚህ ሽልማት የበቁት ባቀረቡት የመጽሐፍ ንድፍ መሠረት መሆኑ ቢነገርም አቶ አለምሰገድ ተስፋይ የሚጽፉበት ርዕስ ምን እንደሆነ የተገለጸ ነገር የለም።

ለሽልማቱ ከተጠቀሙባቸው መመዘኛዎች መካከል የቀረበው የመጽሐፉ ንድፍ ያለውን የሕትመት ብቃት፣ በዓለም ዙርያ ያለውን የንባብ ተቀባይነት፣ የአቀራረብ ዘዴና እንዲሁም የደራሲውን የፈጠራ ችሎታ ያካተተ ነው።

ከማህበሩ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ሽልማቱ ለ5ኛ ጊዜ የተሰጠ ነው።

ማይልስ ሞርላንድ ፋውንዴሽን (ኤምኤምኤፍ) መንግሥታዊ ያልሆነ ማህበር ሲሆን በተለያዩ ዘርፎች እርዳታ የሚያደርግ መሆኑ ድረ ገጹን ይጠቁማል።