"ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ መሆን ነው የምፈልገው"

ያዴሳ ዘውገ Image copyright Yadessa Zewge
አጭር የምስል መግለጫ የአፍሪካ ህብረት ሰንደቅ ዓለማን የሰራው ያዴሳ ዘውገ

ያዴሳ ዘውገ ሰዓሊ፣ የግራፊክስ ዲዛይን ባለሙያ እና አቀንቃኝም ነው።

ጥበብን የሰው ልጆችን ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበርም ይጠቀምባታል።

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመውባቸውል በሚላቸው ጉዳዮች ላይና በአሜሪካ የጥቁሮችን መብት ለማስከበር ይሠራል።

ወላጅ አባቱ በደርግ መንግሥት መገደላቸውን ተከትሎ በልጅነት ዕድሜው ከትውልድ ስፍራው ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ የሚናገገው ያዴሳ ገና በጨቅላ ዕድሜው የሰው ልጆችን መብት ለማስከበር ፍላጎት እንደነበረው ያስረዳል።

''ወላጅ አባቴ የሰው ልጆችን መብት ለማስከበር ባደረገው ጥረት ነው ሕይወቱን ያጣው። ከልጅነቴ ጀምሮ ስለ ሰብዓዊ መብቶች ጠንቅቄ አውቅ ነበር። በዚህም የሰውን ሰብዓዊ መብት የሚጥሱ ነገሮችን ስመለከት ዝም ማለት አያስችለኝም'' ሲል ይናገራል።

ያዴሳ የጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ጥረት ያደርጋል።

''ጥበብ ሰዎችን በማስደሰት እና በመማረክ በቀላሉ የምንፈልገውን መልዕክት ማስተላለፍ እንድንችል ይረዳናል። ለዚህም ነው የጥበብ ሥራዎችን በመጠቀም መልዕክቶችን የማስተላልፈው'' ሲል ይናገራል።

Image copyright Yaddi Bojia
አጭር የምስል መግለጫ ያዴሳ ከበቀለ ገርባ ጋር

''ብዙ ጊዜ መንግሥት ሰዎችን የሚያስረው ተረስተው እንዲቆዩ ነው 'ከዓይን የራቀ ከልብ ይርቃል' እንደሚባለው፤ እኔ ግን የሰው ልጅን ሰብዓዊ መብት ለማስከበር ሲሉ የሚታሰሩት እንዳይረሱ በጥበብ ሥራዎቼ ጥረት አደርጋለሁ'' ይላል።

ከዚህም በተጨማሪ አሜሪካ ውስጥ ሲካሄድ በነበረው ''ብላክ ላይቭስ ማተር'' በተሰኘው የጥቁሮች መብት አንቅስቃሴ ላይ ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው።

በቅርቡም በሲያትል በጥቁርነት ሀሳብ ላይ ያጠነጠነ "ትሩዝ ቢ ቶልድ" የሚል ዓውደ-ርዕይ አለው።

ያዴሳ ሰዓሊ ብቻ ሳይሆን ሙዚቀኛም ጭምር ነው።

በሙዚቃ ሥራዎቹ በርካት ሽልማቶችን ወስዷል።

''ከልጅነቴ ጀምሮ መዝፈን እወድ ነበር። የማዜመው ግን ሰዎችን ለማስደሰት ሳይሆን ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ ለመሆን ነው'' ሲል ያስረዳል።

የአፍሪካ ብረት ባንዲራ

ወደ ጥበብ እንድሳብ ካደረጉኝ ነገሮች እንዱ ወንድሜ ነው።

ታላቅ ወንድሜ ስዕሎችን ይስል ነበር።

ወደ አሜሪካ ከመጣሁ በኋላም ከሁለት ዩኒቨርሲቲዎች 'በቪዡዋል ኮሚዩኒኬሽን' እና 'ግራፊክስ ዲዛይን' ተመርቄያለሁ ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከሠራቸው የግራፊክስ ሥራዎች መካከል አንዱ የአፍሪካ ሕብረት ሰንደቅ ዓላማ ነው።

ከ116 ሃገራት የተወጣጡ የዲዛይን ሙያተኞች የሕብረቱን ሰንደቅ ዓላማ ለመሥራት ተወዳድረው ነው ያዴሳ አሸናፊ የሆነው።

''ሥራዬ ከሌሎች ተሽሎ የተገኘበት ዋነኛው ምክንያት የያዘው መልዕክት ነው። አረንጓዴው ቀለም አፍሪካ በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገች እንደሆነች ያሳያል፣ ኮኮቦቹ ሃገራትን የሚወክሉ ሲሆን ፀሐይዋ ደግሞ የአፍሪካ ሃገራት ከቅኝ አገዛዝ ወጥተው ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር መጀመራቸውን ያመላክታል" ሲል ይተነትናል።

በዚህ ሥራው 10ሺ ዶላር እንደተሸለመና በአህጉረ አፍሪካ የሚገኙ 54ቱንም ሃገራት የመጎብኝት ዕድል እንደተሰጠውም ተናግሯል።

ተያያዥ ርዕሶች