ሞሐመድ ሳላህ የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ተጫዋች ሆኖ ተመረጠ

ሞሐመድ ሳላህ Image copyright BBC Sport
አጭር የምስል መግለጫ የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ተጫዋች አሸናፊ ሞሐመድ ሳላህ

በቢቢሲ ምርጥ አፍሪካዊ ተጫዋች ታሪክ ከፍተኛ የሆነ ድምፅ በማምጣት ግብፃዊው የሊቨርፑል ተጫዋች የ2017 አሸናፊ መሆን ችሏል።

ሳላህ ጋቦናዊውን ኦባሜያንግ፣ የጊኒው ኬይታን፣ ሴኔጋላዊው ሳዲዮ ማኔንና ናይጄሪያው ሞሰስን በማስከተል ነው ውድድሩን ማሸነፍ የቻለው።

"ይሄንን ውድድር በአሸናፊነት በመቋጨቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ" ሲል የ25 ዓመቱ ሳላህ የተሰማውን ስሜት ለቢቢሲ ስፖርት ተናግሯል።

"አንድ ነገር በአሸናፊነት ስትወጣ ሁሌም ደስ ይልሃል። በጣም ውጤታማ ዓመት እንዳሳለፍክም ይሰማሃል፤ እኔም ያ ስሜት ነው እየተሰማኝ ያለው። በሚቀጥለው ዓመትም እንደማሸንፍ ተስፋ አለኝ።"

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጎል አስቆጣሪ ደረጃን በ13 ጎሎች እየመራ የሚገኘው ሳላህ ሃገሩ ግብፅን ወደ ዓለም ዋንጫ ማሳለፍ ከመቻሉም በላይ በክለቡ ሊቨርፑልም ውጤታማ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል።

በ2017 በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ሃገሩ ግብፅ ለዋንጫ ደርሳ ብትሸነፍም ሳላህ ግን በውድድሩ ምርጥ ብቃቱን ማሳየት ችሏል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ሳላህ፡ የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ተጫዋች

ግብፅ የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ባደረገችው ጉዞ በተቆጠሩ ሰባት ጎሎች ውስጥ እግሩ ያለበት ሳላህ ከኮንጎ ጋር በነበረው የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታ ባለቀ ሰዓት ባስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ሳቢያ ሃገሩ የሩስያ ትኬቷን መቁረጥ ችላለች።

የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ተጫዋች በማሸነፍ ሶስተኛው ግብፃዊ መሆን የቻለው ሳላህ "ምርጡ ግብፃዊ ተጫዋች መባል ስለምፈልግ ሁሌም ጠንክሬ እሠራለሁ" ይላል።

በጣሊያን ለሮማ በሚጫወትበት ጊዜም 15 ጎሎችን በማስቆጠር እንዲሁም 11 አመቻችቶ በማቀበል ክለቡ 2ተኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ አግዟል።

"ሮማ ሳለሁ የነበሩ ጓደኞቼን፣ የሊቨርፑል አጋሮቼን እንዲሁም የብሔራዊ ቡድን ጓደኞቼን ላገኘሁት ስኬት እጅግ አድርጌ ማመስገን እፈልጋለሁ" ባይ ነው ሳላህ።

Image copyright BBC Sport

"ፕሪሚዬር ሊጉን ለቅቄ ከሄድኩበት ሰዓት ጀምሮ ተመልሼ መጥቼ ብቃቴን ማሳየት ፈልጌ ነበር። ይህንንም ማድረግ በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ" ሲል ይናገራል።

በ2014/15 በቼልሲ ካሳየው ብቃት በተለየ ሊቨርፑልን ከተቀላቀለ ወዲህ እጅግ ጥሩ አቋም ማሳየት የቻለው ሳላህ ስሙን ከአቤዲ ፔሌ፣ ዊሃ፣ ኦኮቻ፣ እንዲሁም ድሮግባ ተርታ ማሥፈር ችሏል።

በ2015 የቢቢሲ የዓምቱ ምርጥ ተጫዋች ምርጫን የማንቸስተር ሲቲው ያያ ቱሬ በ2016 ደግሞ የሌይስተሩ ሪያድ ማህሬዝ ማሸነፋቸው አይዘነጋም።