በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ድንበር ግጭት የገዳ ስርዓት መፍትሔ ለምን አላመጣም?

አባ ገዳ ኩራ ጃርሶ

የገዳ ስርዓት የኦሮሞ ሕዝብ ማንኛውንም ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ሲፈታበት የኖረ ሥርዓት እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ይጠቅሳሉ።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ተከስቶ መጠነ-ሰፊ ቀውሶችን እያስከተለ ያለውን ግጭት በገዳ ስርዓት መፍታት ያልተቻለው በቁጥር ብዛት ያላቸው የታጠቁ ሃይሎችና ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ስላሉበት አስቸጋሪ እንዳደረገው አባገዳዎች ይናገራሉ።

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል በተከሰተው ግጭት የብዙ ዜጎች ሕይወት ማለፉንና ከ 600 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው።

ግጭቱ ከሐረርጌ ጀምሮ እስከ ቦረና የዘለቀና ድንበር አካባቢ ያሉ ሰዎችንም ለከፋ ችግር የዳረገ ነው።

በቦረናና በሞያሌ የድንበር ግጭት እየከፋና በፀጥታ ኃይሎች በንፁሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ችግር እያሳሰባቸውም እንደሆነ የቦረናው አባ ገዳ ኩራ ጃርሶ ገልፀዋል።

ባለፈው ሐሙስ በቦረና ኦሮሞና በገሪ ሶማሌ መካከል በተፈጠረው ግጭት የሰው ሕይወት እንዳለፈና አሁንም ችግሩ አሳሳቢ እንደሆነ አባ ገዳ ኩራ ጃርሶ ጨምረው ይናገራሉ።

"የገዳ ስርዓትን ተጠቅመን ህዝቡን እንዳናስታርቅ ያለው የፀጥታ ኃይል እክል ፈጥሮብናል። የገዳ ስርዓት በኦሮሞ ባለው በእርስ በርስ ግጭት ብቻ ሳይወሰን ከሌሎች ክልሎችም ጋር የሚከሰቱ ግጭቶችን መፍታት ይችላል። እሱን ግን ተግባራዊ ማድረግ አልቻልንም"ብለዋል።

የገዳ ስርዓት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለምን መፍት ማምጣት አልቻለም?

አባ ገዳው ስለድንበር ችግሩ ሲናገሩ ከፍተኛ ግጭቶች ለውይይት እንዳይቀመጡ እንዳደረጋቸውና የችግሩ መጠን ከአቅማቸው በላይ መለጠጡን ነው።

''ለብዙ ዘመናት ሕዝቦችን በገዳ ስርዓት እያስታረቅን እንደቤተሰብ እንዲኖሩ በማድረግ ዛሬ ደርሰናል። በግጭቱ ያለው የፀጥታ ኃይል በዘመናዊ መሳሪያ የተደገፈ ስለሆነ ከአቅማችን በላይ ሆኗል" በማለት ይናገራሉ።

የገዳ ስርዓት ዘመንን ተሻግሮ ለዓለም ባበረከተው ሥርዓት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣የሳይንስ እና የባህል ተቋም በማይዳሰሱ ቅርስነት ተመዝግቧል።

የኦሮሞ ሕዝብ ለገዳ ስርዓት ትልቅ ክብር እንዳለው የሚናገሩት አባ ገዳ ኦሮሞዎችም የገዳ ውሳኔዎችንም እንደሚያከብሩ ይናገራሉ።

ይህም ቢሆን ግን ከኦሮሚያ ክልል አልፎ የገዳ ውሳኔ በሀገሪቷ የፖለቲካ ውሳኔ ምን አይነት ተፅፅኖ ሊያሳርፍ ይችላል ወይም ተቀባይነቱ ምን ድረስ ነው የሚለው ጥያቄ አሳሳቢም እንደሆነ አባ ገዳው ያስረዳሉ።

በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም በኦሮሚያ ውስጥ ለሚፈጠሩት ችግሮች ግን ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ለማድረግ እየሰሩ እንዳሉ አባ ኩራ ጃርሶ ይናገራሉ።

"በገዳ ስርዓት የሚተዳደረውን የኦሮሞን ሕዝብና በሀገሪቷ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ማስታረቅ እንደምንችል፤ ይህ ስርዓት ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወት ለማድረግ ስራችን ይቀጥላል" ብለዋል።

የኦሮሞን ታሪክና የገዳ ስርዓት ታሪክ ተማራማሪ የሆኑት ዶር ቦኩ የኦሮሞ ሕዝብ ግጭቶችን የሚፈታበት ሁለት መንገዶች ሲኖሩ እነዚህም መከላከል (ፕሪ ኤምፕቲቭ ሜዠር ) እና ማቋቋም (ሚቲጌሺን ሜዠር) እንደሚባሉ ይገልፃሉ።

በዚህም መሰረት ቂም በመያዝ አብሮ አይኖርም በሚልም እሳቤ በማስታረቅ ለግጭቶች ዘለቄታዊ መፍትሄ ማግኘት ይቻላል ብሎ የሚያምን ስርአት እንዳለው ዶ/ር ቦኩ ይናገራሉ።

ገዳ በብቃት የማስተዳደር አቅሙን ማግኘት አለበት ብለው የሚያምኑት ዶ/ር ቦኩ ከተለያዩ የመንግስትም ሆነ ከፖለቲካ ጫና የገዳ ስርዓት ነፃ ሊሆን እንደሚገባ ይናገራሉ።

"ሕዝብን ማወያየትም የገዳ ሚና ነው። ሰላምን ለማምጣት ሕዝቡ ገዳን መስማት አለበት''ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች