ለማነፍነፍ የሰነፈችው ጥሩ ውሻ

ሉሉ Image copyright CIA

በአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲ አይ ኤ ፈንጂ ለማነፍነፍ ከተመለመሉት ውሾች አንዷ የነበረችው ሉሉ ቦምብ የማነፍነፍ ምንም አይነት ፍላጎት ስለሌላት ከስልጠናው እንድትወጣ ተደርጓል።

ሲ አይ ኤ ሉሉን ያባረራት በአንድ ጊዜ ሳይሆን ለሳምንት ያህል በስልጠናው እንድትቆይ ካደረገ በኋላ ነው።

ቦምብም ሆነ ሌላ አይነት ፈንጂ የማነፍነፍ ፍላጎት የሌላት ሉሉ እድሉን አግኝታው የነበረ ቢሆንም ለመቆየት ግን አላለላትም።

ስለዚህም እንደ አውሮፓውያኑ ከየሲ አይ ኤ የስልጠና ክፍል ልትሰናበት ግድ ሆኗል።

የሲ አይ ኤ ባለስልጣናትም ሉሉ ለምን እንደተባረረች በተደጋጋሚ በትዊተር ገጻቸው ላይ ሲፅፉ ነበር።

የዚህ አይነቱን ስልጠና የሚወስዱ ውሾች በ10 ሳምንታት 19 ሺህ የፈንጂ አካባቢዎችን ማነፍነፍ ይጠበቅባቸዋል።

በመጨረሻም ፈተና ይሰጣቸዋል።

ፈተናውን ማለፍ የቻሉት ደግሞ በፈንጂ አሰሳ ላይ እንዲሳተፉ ይደረጋል።

ድንገተኛ አደጋዎች ሲኖሩም እንደ ፖሊስ ያሉ የመንግስት ተቋማትን እንዲያግዙ ይደረጋል።

ወደ ሌሎች ሀገሮች እንዲሄዱና በፈንጂ አሰሳ ላይ እንዲሳተፉም የሚደረግበት አሰራር አለ።

Image copyright CIA

አዳዲሶቹ ምሩቅ አነፍናፊ ውሾች በሳምንት አስከ ስልሳ ሰዓት ይሰራሉ።

ስራ ላይ ባልሆኑበት ጊዜ እንኳን ልክ ስራ ላይ እንዳሉ ሁሉ የነቁ መሆናቸውን የሲአይ ኤ መረጃ ያሳያል።

አብዛኛውን ጊዜ በሲ አይ ኤ የሚመረጡት ውሾች እንደ ላብራዶርና ጀርመን ሸፐርድ ያሉ ናቸው።

ከእነዚህ ውሾች በተለየ መልኩ የሲ አይ ኤ ቆይታ ለሉሉ ፈታኝ ነበር።

የሚሰለጥኑት ውሾች ስራውን ሊወዱት ግድ መሆኑን ሲ አይ ኤ ይናገራል።

ሉሉ ግን ምንም እንኳን በምግብና በጨዋታ ሊያታልሏት ቢሞክሩ እንኳን ስራውን ልትወደው አልቻለችም።

የሉሉ ከሲ አይ ኤ ስልጠና መሰናበት ማህበራዊ ድረ ገፅ ላይአነጋጋሪ ሆኖ ነበር።

አንዳንዶች "ፋታ ስጧት ትጫወትበት"ሲሉ ሌሎች ደግሞ ምናልባትም የሉሉ ፍላጎት "አርቲስት መሆን ዓለምን መዞር ሊሆን ስለሚችል ተዋት ህልሟን ታሳካበት"ሲሉ ተደምጠዋል።