'የአውሮፓ ሕብረት የሊቢያ ስደተኞችን ስቃይ ችላ ብሏል'

Migrant boats are regularly intercepted by the Libyan coastguard Image copyright AFP

የአውሮፓ ሕብረት በሊቢያ እየተከናወነ ያለውን የስደተኞች ስቃይ እያወቀ ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቷል ሲል ነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ዘገባው ያተተው።

ሕብረቱ የሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ በሕገ-ወጥ የሰው ማዘዋዋር ሥራ ላይ ለተሰማሩ ሰዎች በተዘዋዋሪ መልኩ እየደረሰ ነወ ይላል ዘገባው።

የአውሮፓ ሕብረት መርከቦችን፣ ሥልጠና እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ በሊቢያ ለሚገኙ የውቅያኖስ ዳርቻ ጠባቂዎች ያበረክታል።

ሊቢያ የሜዲትራንያን ውቅያኖስን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመዝለቅ የሚሞክሩ በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች መዳረሻ ስትሆን ጣሊያን ደግሞ ስደተኞቹ አውሮፓ ሲደርሱ የሚያርፉባት ሃገር መሆኗ ይታወቃል።

ነገር ግን ውቅያኖሱን ለመጠበቅ የተቀጠሩ ግለሰቦች ከሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ጋር በጋራ እየሰሩ ስደተኞቹ ላይ ግፍ እያደረሱ ነው፤ የአውሮፓ ሕብረት ደግሞ ስለዚህ ጉዳይ እውቀቱ አለው ይላል ቡድኑ በዘገባው።

የሕብረቱ ችላ ባይነት ስደተኞቹ በአዘዋዋሪዎቹ እጅ ስቃይ እንዲደርስባቸውና የባርያ ንግድ እንዲስፋፋም አስተዋፅኦ አበርክቷል።

የአምነስቲ ዘገባ እንደሚያመለክተው 20 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞቹ ሊቢያ በሚገኙ የስደተኛ ማጎሪያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ።

በእነዚህ ጣቢያዎች ውስጥም ስደተኞቹ ለስቃይ፣ ለጉልበት ብዝበዛ እንዲሁም ለሞት አደጋ እየተጋለጡ እንደሆነም ነው ቡድኑ የሚያስረዳው።

"በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች በጣቢያዎቹ ውስጥ በጣም ተጨናንቀው ይገኛሉ። ለብዝበዛም የተጋለጡ ናቸው" ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአውሮፓ ኃላፊ ጆን ዳልሁይሴን ይናገራሉ።

በያዝነው የአውሮፓውያን ዓመት መባቻ የቢቢሲ ዘጋቢ ቡድን ወደ ጣቢያዎቹ ገብቶ ስደተኞችን አነጋግረው የነበረ ሲሆን ስደተኞቹ ሁኔታውን 'ልክ እንደ ገሃነም ነው' ሲሉ የገለፁ ሲሆን ከእሥር ቤት የባሰ እንደሆነም ተናግረው ነበር።

ለአምነስቲ ድምፁን የሰጠ አንድ ከጋምቢያ የመጣ ስደተኛ ለሶስት ወር ያህል ረሃብ ውስጥ ሆኖ ድብደባ እየደረሰበት እንደቆየ ተናግሯል።

የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ቡድኑ የአውሮፓ ሕብረትን ለመክሰስ የሚያበቃ ማስረጃ አለኝ ሲልም አስታውቋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ