የታንዛንያው ፕሬዝዳንት ለሕፃናት ደፋሪዎች ይቅርታ አደረጉ

John Magufuli Image copyright AFP

የሕፃናት መብት አቀንቃኞች የታንዛንያው ፕሬዚዳንት ለሁለት ሕፃናትን የደፈሩ ወንጀለኞች ይቅርታ ማድረጋቸውን አውግዘውታል።

አሩሻ የሚገኘው ኮሙዩኒቲ ፎር ችልድረን ራይትስ ድርጅት ዳይሬክተር ኬት ማክአልፓይን "አስደንጋጭ ግን አስደናቂ ያልሆነ" ብለውታል።

ጆን ማግፉሊ ይህንን ይቅርታ ያደረጉት ቅዳሜ የነፃነት ቀን ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

10 የአንደኛ ደረጃ ሴት ተማሪዎችን የደፈሩት ዘፋኙ እንጉዛ ቫይኪንግ ወይም በቅጽል ስሙ ባቡ ሴያ እንዲሁም ልጁ ጆንሰን እንጉዛ ናቸው።

ፕሬዝዳንቱ ከእስረኞቹ መሀል የባህርይ ለውጥ አምጥተዋል ያሉዋቸውን እስረኞች እንዲለቀቁ ወስነዋል።

ኬት ማክአልፓይን ይህ ይቅርታ ፕሬዝዳንቱ በሕፃናት ላይ የሚደረግ ጭካኔን ወይም ሰብዓዊ መብት ጥሰትን መረዳት እንዳቃታቸው ማሳያ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ይህ ንግግራቸውን ባለፈው ሰኔ እርጉዝ የሆኑ ተማሪዎች ትምህርት ቤት እንዳይመለሱ ካሉት አዋጅ ጋር አያይዘውታል።

"ሕፃናትን ተጠቂ አድርገው ማየት የማይችሉ እውር ናቸው። ህፃናት ተማሪዎች እርጉዝ የሆኑት ጥቃት ስለደረሰባቸው ነው" ብለዋል።

የሕፃናት መብት አቀንቃኟ ሄለን ኪጆ ቢሲምባ ለቢቢሲዋ ሙኒራ ሁሴይን እንደተናገሩት "እነዚህን ወንጀለኞች ይቅር ማለት ለቤተሰቡና ለወላጆች ህመምን መጨመር ነው" ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ተመሳሳይ ነገርም እንዳይፈፅሙ ሕገ-መንግሥቱ ሊያግዳቸው እንዲገባ ዘመቻ እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በታንዛንያ ሕፃናት ሲደፈሩ በቤተሰብ ስምምነት እንዲፈታ ከመደረጉም በላይ በብዙ አጋጣሚዎች ደፋሪዎች ፖሊስን ወይም የፍርድ ቤት ሠራተኞችን እንደሚከፍሉ ማክአልፓይን ይናገራሉ።

"የሕፃናት መደፈር ጉዳይን ወደ ፍርድ ቤት ማምራት ማለት እንደ መስቀል ወፍ ነው" ያሉት ማክአልፓይን ወንጀለኞችም የዕድሜ ልክ ፍርድ ሲፈረድባቸውም አይታይም ብለዋል።

ይህም ሆኖ ቫይኪንግ እና እንጉዛ በአውሮፓውያኑ 2003 ዕድሜያቸው ከ6-8 ዓመት የሚገመቱ በዳሬሰላም የሚገኙ 10 ሕፃናትን በመድፈራቸው የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶባቸው ነበር።

እሰከተለቀቁባት ቅዳሜ ድረስም ለ13 ዓመታትም በእስር ቆይተዋል።

የሀገሪቱ ሚዲያ እንደዘገቡትም ከእስር ቤት ሲወጡ ደጋፊዎቻቸው በጭብጨባ ተቀብለዋቸዋል።