በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ተማሪዎች ሞቱ

ወለጋ ዪኒቨርሲቲ Image copyright Wollega University

ትናንት በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሻምቡ ካምፓስ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ትምህርት የተቋረጠ ሲሆን አመሻሽ ላይ ሁለት ተማሪዎች በግጭቱ መሞታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እንደገለጹት"በዓዲግራት ወንድሞቻችን እያለቁ ነው" በሚል ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩ ተማሪዎች በሌሎች ተማሪዎች ላይ ጥቃት የፈፀሙ ሲሆን፤ የሁለት ተማሪዎች አስከሬን ጫካ ውስጥ ተገኝቷል።

በዚሁ ካምፓስ ከትናንት ምሽት ሦስት ሰዓት ጀምሮ የተወሰኑ ብሔር ተወላጆች ከማደሪያ ክፍላቸው እየተፈለጉ ጥቃት እንደደረሰባቸው ምንጮቹ ይገልፃሉ።

በፍራቻም በፖሊስ ጣቢያ ተጠልለው እንደሚገኙም ተማሪዎቹ ይናገራሉ።

የትግራይና የኦሮሚያ ክልል የኮምኒኬሽን ጉዳይ ኃላፊዎች አቶ ገ/ሚካኤል መለስ እና አቶ አዲሱ አረጋ በዩኒቨርሲቲው የተፈጠረውን ነገር ዛሬ በፌስቡክ ገፃቸው አረጋግጠዋል።

ትናንት ታህሳስ 2 ቀን 2010 ዓ.ም እኩለ ሌሊት አካባቢ በወለጋ ዩኒቨርስቲ ሻምቡ ካምፓስ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሁለት ተማሪዎች ሕይወት እንዳለፈም ኃላፊዎቹ ጽፈዋል።

በዚህ ግጭት የተሳተፉ እና የሰው ሕይወት በማጥፋት የተጠረጠሩ በርካታ ሰዎች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልጸዋል።

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎችን ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ባለፈው አርብ በተነሳው ግጭት የአንድ ተማሪ ሕይወት ያለፈ ሲሆን፤ ትናንት በተለይ በጎንደር፣በወለጋ፣ በደሴና በአምቦ ዩኒቨርሲቲዎች ተቃውሞና ግጭት እንደተከሰተ ቢቢሲ ከዩኒቨርሲቲዎቹ ያገኘው መረጃ ያመላክታል።