"በእንቅልፍ ልቤ መኪናም ሞተርም ነድቻለሁ"

Jackie in car

በእንቅልፍ ልብ የሚደረጉ ነገሮች በጣም አደገኛ ይሆናሉ። በተለይም ውሀ፣የተጨናነቁ መንገዶችና ከፍታዎች ካሉበት ከባድ ይሆናል።

በእንቅልፍ ልብ መንዳት ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ አደገኛ ነው።የነርቭ ሀኪም የሆኑት ጋይ ሌቺዝነር ጃኪ የተባሉ ታካሚያቸው በእንቅልፍ ልባቸው ይነዱ እንደነበር ይናገራሉ።

ጃኪ ከአሜሪካ ወደ ካናዳ እንደሄዱ የሚኖሩት ከአንዲት አዛውንት ጋር ነበር።አንድ ቀን አዛውንቷ ጃኪን 'የት ነው ሌሊት የሄድሽው?' ብለው ይጠይቃሉ። ጃኪም 'የትም አልሄድኩም' ሲሉ ይመልሳሉ።

አዛውንቷም 'እንግዲያውስ ሌሊት ሞተር ብስክሌትሽን ይዘሽ ወጥተሽ ነበር' አሏቸው ፤ጃኪ በጣም ደነገጡ።

ወዲያውም የራስ መከላከያቸውን አድርገው እንደነበር አዛውንቷን ጠየቁ።

አዛውንቷም "ወደ ታች ወረድሽና የራስ መከላከያሽን አደረግሽ።ከዚያም ወተሽ የቆየሽው ለሃያ ደቂቃ ነበር" ሲሉ መለሱ።

ሁሉንም ነገር በእንቅልፍ ልባቸው ያደረጉት ጃኪ ግን ምንም የሚያስታውሱት ነገር አልነበረም።

ወጥተው እንደነበር የሚያሳይም ምንም ፍንጭ አልነበረም።ሁሌም እንደሚሆነው ሞተሩ ፣የራስ መከላከያውም ሁሉም በትክክል ወደ ቦታቸው ተመልሰው ነበር።

ልጅ ሳሉ በትምህርት ቤት ክበባት ጉዞ ሲሄዱ ማንም ከጃኪ ጋር በአንድ ድንኳን ማደር አይፈልግም ነበር።ምክንያቱ ደግሞ ጃኪ ሲተኙ የሚያሰሙት የሚረብሽ ድምፅ ነበር።

"ስተኛ ድምፅ አወጣለው።እንዲሁ ቀላል ድምፅ አልነበረም።የድብ ድምፅ ይመስል ስለነበር ከኔ ጋር መተኛት በጣም ይፈሩ ነበር።"በማለት ጃኪ ያስታውሳሉ።

የያል ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ሚር ክሪገር ሌሊት እየተነሳ ብሄራዊ መዝሙር ዘምሮ ወደ አልጋው የሚመለስ አንድ ሰው እንደሚያውቁ ይናገራሉ።

የአዋቂዎች ጉዞ ላይም ጃኪ ተቆጣጣሪ ነበሩ። "በሌሊት ተነስቼ ወደ ወንዝ እወርድ ነበር።ወደ ጫካ ውስጥም እገባ ነበር ቢከተሉኝም አይደርሱብኝም ነበር።በመጨረሻ ሰዎች ተልከው ነበር ወደ ቤት የምመለሰው።"ይላሉ።

ጃኪ ካደጉ በኋላ ብቻም ሳይሆን ልጅ እያሉ በእንቅልፍ ልባቸው የተለያዩ ነገሮችን ያደርጉ ነበር።በተለይም በእንቅልፍ ልብ መብላት፣ ማውራትና ቅዠት በልጅነት ጊዜ የሚታዩ የተለመዱ ነገሮች ናቸው።

"ወደ ምግብ ቤት እወርድ ነበር።ወደ ወላጆቼ ክፍል በመሄድም በሩን ከፍቼ ዝም ብዬ እቆም ነበር።ይህ እናቴን በጣም ይረብሻት ነበር።አባቴ ግን እጄን ይዞ ወደ ክፍሌ በመውሰድ ያስተኛኝ ነበር።"በማለት ያስታውሳሉ።

ጃኪ ችግሩን ለመቅረፍ የመኪናቸውን ቁልፍ አብረዋቸው ለሚኖሩት አዛውንት በመስጠት የፈቱት መስሏቸው ነበር።

ነገር ግን መኖሪያ ከቀየሩ በኋላ እዚያም ጎረቤቶቻቸው ሌሊት ወዴት እንደሚሄዱ ሲጠይቋቸው ችግሩ ከብዙ ዓመታት በኋም እንዳለባቸው ተረዱ።

በእንቅልፍ ልባቸው መንዳታቸው ለጃኪ ፍፁም አዲስ ዜና አልነበረም።ነገር ግን በተለይም በእንቅልፍ ልባቸው ሞተር ከነዱ ረዥም ጊዜ ስለሆናቸው ነገሩ ትንሽ ገረማቸው።

የሰዎች የዚህ ዓይነት ባህሪ ማሳየት እንደሚያስጨንቅ የያል ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ክሪገር ይናገራሉ።

ጃኪም በእንቅልፍ ልባቸው ማሽከርከራቸው አደገኛ መሆኑን በመረዳት በመጨረሻ የዶክተር ምክር መጠየቅ ግድ ሆኖባቸዋል።

Image copyright Getty Images

ይህ የተወሳሰበ የአዕምሮ ነገር ለምንና እንዴት ሊከሰት ይችላል?

እንደ ዶልፊንና ወፍ ያሉ እንስሳት በግማሽ አዕምሯቸው ሊተኙ ይችላሉ።ምክንያቱም በግማሽ አዕምሯቸው መዋኘትና መብረር ይችላሉና።በሰዎች ግን የዚህ ዓይነት ነገር የለም።

ቢሆንም ግን እንቅልፍምንቃትም በሰው አዕምሮ በአንድ ጊዜ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ማወቃቸውን የነርቭ ሀኪዎቹ ይናገራሉ።

በእንቅልፍ ልብ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በእንቅልፍ ልብ ዕይታን፣እንቅስቃሴንና ስሜትን የሚቆጣጠረው የአዕምሮ ክፍል ሲነቃ ትውስታን፣ ውሳኔንና ምክንያታዊነትን የሚመለከተው ክፍል ደግሞ ጥልቅ ዕንቅልፍ ውስጥ ይሆናል።

እንቅልፍ ልብ ከዘር ጋርም የሚገናኝ ነገር አለው።

ወደ ጋይ ሆስፒታል ከሄዱ በርካታ ታካሚዎች ብዙዎቹ በዘራቸው በእንቅልፍ ልብ የተለያዩ ነገሮችን የሚያደርጉ የቤተሰብ አባላት እንዳሏቸው ተናግረዋል።በዚህ መሰረትም የተደረጉ ጥናቶች አሉ።

ጃኪ በመጨረሻ በፍቃዳቸው ጋይ ሆስፒታል ቢገቡም መጀመሪያ የራሳቸውን ሁኔታ ለማሻሻል የተለያዩ ነገሮችን ሞክረዋል።

ለምሳሌ መጀመሪያ ያደረጉት በር ላይ ደወል በማስቀመጥ ሌሊት በር ከፍተው ሲወጡ አብሯቸው ያለ ሰው እንዲሰማ ማድረግን ነበር።

ከጃኪ ጋር ይኖሩ የነበሩት ኢድ ከባድ እንቅልፍ ይይዛቸው ስለነበር ደውሉን አይሰሙም ነበር።የደውሉን ድምፅ መጨመር ደግሞ ጎረቤት ይረብሽ ነበር።

ስለዚህ ጃኪ በዚህ ፈንታ የበሩን ቁልፍ በሰዓት የሚሞላና በምስጢር ቁጥር የሚከፈት ሳጥን ውስጥ ያስቀምጡ ጀመር። ሳጥኑ ደግሞ ያለ ንጋት አስራ ሁለት ሰዓት አይከፈትም ነበር።

ይህ ዘዴ ጃኪን በሌሊት በእንቅልፍ ልብ ከመንዳት አቅቧቸዋል።

በእንቅልፍ ልብ የሚደረጉ ነገሮች ለአድራጊውም ለሌላውም አስቸጋሪ የሚሆኑበት ጊዜ አለ።በእኩለ ሌሊት በእንቅልፍ ልብ ስልክ መደወል፣መልዕክት መላክ ወይም ምግብ ማብሰል ብዙዎች የሚያደርጉት ነው።

ነገር ግን ለብዙዎች በእንቅልፍ ልብ የሚደረግ ነገር ብዙ ድራማ አይበዛውም።

በእንቅልፍ ልብ የተለያዩ ነገሮችን የሚያደርጉ ሰዎች በተለይም ከቤት ሲወጡ፣መኪና ሲነዱና እንደ ቢላ ያለ ነገር ሲይዙ ነገሮች አደገኛ እንደሚሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

እንቅልፍን በተደጋጋሚ ሊያቋርጡ የሚችሉ ነገሮችን በማስወገድ በእንቅልፍ ልብ የሚደረግን ነገር በተወሰነ መልኩ መቆጣጠር ይቻላል።ነገር ግን ነገሩ የከፋ ከሆነ መድኃኒት የተሻለ ይሆናል።

ትንንሽ የሚመስሉ እርምጃዎችም ትልቅ መፍትሄ ሊያስገኙ ይችላሉ።

ወደ አልጋ መሄጃንና ከእንቅልፍ መነሻ ሰዓትን የተወሰነ ማድረግ፣አልኮልና ውጥረትን ማስወገድ፣ካፌን መቀነስና የመሳለሉትን ነገሮች በማድረግ ጥሩ እንቅልፍ ማግኘት ይቻላል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ንቃትና እንቅልፍ ሁለት የተለያዩ ሂደቶች ተደርገው የታዩ ነበር።አሁን ግን ነገሩ እንደዚያ ሳይሆን ሁለቱም በአንድ ጊዜ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ታውቋል።

በርግጥ እንቅልፍና ንቃት የአዕምሮ አንድ ሂደት ሁለት ጫፎች ናቸው።በእነዚህ ሁለት ጫፎች መሀከል አዕምሯችን ያለበት ቦታ የምናስታውሰውንና የምናደርገውን እንቅስቃሴ ይወስናል።

እንቅልፍ በምናጣበት ወቅት የአዕምሯችን የተወሰነ ክፍል ይተኛል።

ስለዚህ እንቅልፍ ስናጣ ነቅተንም ቢሆን የሆነው የአዕምሯችን ክፍል እንደ መተኛት ሊያደርገው ይችላል። አንዳንዴ ትኩረት የምናጣውና ነገሮችን ልብ ማለት የሚያቅተን ለዚህ ሊሆን ይችላል።

በሌላ በኩል ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ሆነን የአዕምሯችን ክፍል ግን ንቃት ላይ መሆን ሰዎች እንዴት በእንቅልፍ ልባቸው ይሄንን ያንን አደረጉ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሆናል።