በደቡብ ሱዳን በተከሰተ ግጭት 170 ሰዎች ተገደሉ

Previous clashes in South Sudan have been over issues like cattle Image copyright AFP

በደቡብ ሱዳን ምዕራባዊ ክፍል በሁለት ጎሳዎች መካከል የተከሰተ ግጭት የ170 ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ ከ200 በላይ ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሃገሪቱ የፓርላማ አባል የሆኑት ደሩዋይ ማቦር ቴኒ አስታውቀዋል።

እርግጥ በአከባቢው ግጭት የተለመደ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት የተከሰተው ግጭት ግን እጅግ የከፋ ነው ሲል የቢቢሲው ፈርዲናንድ ኦሞንዲ ከናይሮቢ ይናገራል።

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በሃገሪቱ ለሶስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይፋ ማድረጋቸውም ይታወሳል።

አዋጁ በዋነኛነት ሶስት የሃገሪቱን ክልሎች የሚያካልል ሲሆን የሃገሪቱ ጦር በእነዚህ ቦታዎች ሙሉ ትጥቁን ታጥቆ እንዲንቀሳቀስ ታዟል።

የታጠቁ ሰዎች መሣሪያቸውን በሰላም የማያስረክቡ ከሆነ የሃገሪቱ ጦር አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ መብት እንዳለውም ነው ሳልቫ ኪር በአዋጁ ያስታወቁት።

በታህሳስ ወር መባቻ ላይ ተጋጭተው የነበሩት የዲንካ ማሕበረሰብ ጎሳዎች በርካታ መሣሪያ የታጠቁ ወጣቶች እንደሚገኙባቸው ይነገራል።

"ከ170 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። 342 አካባቢ ቤቶች ደግሞ ተቃጥለዋል፤ በዚህ ምክንያት 1800 የሚሆኑ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል" በማለት ቴኒ ሁኔታውን ያስረዳሉ።

የሳልቫ ኪር ቃል-አቀባይ የሆኑ ሰው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እየተፈጠረ ላለው የእርስ በርስ ግጭት መፍትሄ ሊያመጣ እንደሚችል ተስፋ እንዳላቸው ይናገራሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሃገሪቱ እየተከሰተ ያለውን የእርስ በርስ ግጭት የሚያጣራ ቡድን በላከ ሰሞን ነው መሰል ግጭት ተከስቶ የበርካታ ሰው ሕይወት ያጠፋው።

በደቡብ ሱዳን እየተከሰተ ያለውን ግጭት የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ ሌሎች ውጫዊ አካላት ለመፍታት እያደረጉ ያለው ግጭት እስካሁን ምንም ዓይነት መፍትሄ ማምጣት አልቻለም።