የኒው ዮርክ ቦምብ ጥቃት ተጠርጣሪ ትራምፕን አስጠንቅቆ ነበር

Akayed Ullah emigrated to the US with his family in 2011 Image copyright CBS

"ትራምፕ ሃገርህን መጠበቅ አልቻልክም" ሲል በፌስቡክ ገፁ ያሠፈረው አካየድ ኡላህ ሰኞ ዕለት ኒው ዮርክ ውስጥ በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት ተጠርጥሮ የሽብር ክስ ተመስርቶበታል።

የ27 ዓመቱ ኡላህ በ2011 ነበር ከቤተሰቦቹ ጋር ከባንግላዲሽ ወደ አሜሪካ ያቀናው። ግለሰቡ ጥቃት እንዲፈፅም ያነሳሳው ኢስላሚክ ስቴት የተሰኘው ቡድን እንደሆነም የአሜሪካ ባለሥልጣናት በመናገር ላይ ይገኛሉ።

ዕለተ ሰኞ በደረሰው የቦምብ ጥቃት ተጠርጣሪውን ጨምሮ አራት ሰዎች መቁሰላቸው ሲታወቅ በጥቃቱ ምንም ዓይነት ሕይወት አልጠፋም።

ኡላህ ራሱ ላይ የሚፈነዳ ቁስ በመጠምጠም በኒው ዮርክ ማንሃተን በሚገኝ የአውቶቡስ ማቆሚያ ሥፍራ ሊያፈነዳ ሞክሯል በሚል ነው የተከሰሰው።

የኒው ዮርክ ከተማ ፖሊስ በትዊተር ገፁ እንዳሠፈረው ግለሰቡ የሰው ነብስ የማጥፋት ሙከራ ወንጀልን ጨምሮ የሽብር ተልዕኮ ያለው ተግባር በመፈፀም ይከሰሳል።

Image copyright Getty Images

ክሱን የመሠረተው የአሜሪካ ፌዴራል አቃቤ ሕግ እንደገለፀው ኡላህ ከተያዘ በኋላ "ድርጊቱን የፈፀምኩት ለአይ ኤስ ስል ነው" ብሏል።

ክሱ የተመሠረተበት ፋይል እንደሚያትተው ተጠርጣሪው ይህንን ድርጊት ለመፈፀም የተነሳሳው በቅርቡ አሜሪካ አይ ኤስ ላይ በፈፀመችው የአየር ድብደባ ምክንያት ነው።

የተጠርጣሪውን ቤት የፈተሸው የከተማዋ ፖሊስ ኡላህ ቦምቡን ለመሥራት የተጠቀመባቸውን ብዙ ዓይነት ቁሳቁሶች አግኝቻለሁ ሲል ማሳወቁን አቃቤ ሕግ ጁም ኪም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የባንግላዲሽ መንግሥት ኡላህ ሃገሩ በነበረበት ወቅት ምንም ዓይነት የወንጀል ሬከርድ እንደሌለበት ያሳወቀ ሲሆን ባለፈው ወርሃ መስከረም ወደ ባንግላዲሽ ተመልሶ አጎቱን ጎብኝቶ እንደተመለሰ ሊታወቅም ችሏል።

ከአደጋው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ "ጥቃቱ አሜሪካውያንን ለመጠበቅ ሂደቶች ጠበቅ ማለት እንዳለባቸው አመላካች ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።