በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የፓርላማ አባሉና አጋሮቹ በመደፈር ወንጀል ተቀጡ

ሕፃናት የደፈሩ የኮንጎ ታጣቂዎች ተፈረደባቸው Image copyright AFP

ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ውስጥ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ 11 ሰዎች አንድ ጨቅላን ጨምሮ 40 ሕፃናትን በመድፈር ተከሰው ወንጀለኛ ሆነው በመገኘታቸው በእሥራት ተቀጥተዋል።

ወንጀሉን የፈፀሙት በአውሮፓውያኑ ከ2013 እስክ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን ወንጀሉ የተፈፀመባቸው ሕፃናት ዕድሜያቸው ከ8 ወር እስከ 12 ዓመት ያለ መሆኑንም ማወቅ ተችሏል።

የቡድኑ መሪ ፍሬድሪክ ባቱሚኬ የተባለ የፓርላማ አባል የሆነ ግለሰብ ሲሆን በእሥራት ወንጀል እንዲቀጣም ተወስኖበታል።

"የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል የፈፀሙ መሰል ግለሰቦች ላይ የተሰጠው ብይን ለሌሎች መስተማሪያ ይሆናል ብለን እናስባለን" ሲሉ የተከሳሾቹ ጠበቃ ቻርልስ ቹባካ ይናገራሉ።

'ጄሺ ያ የሱ' ወይንም 'የእየሱስ ወታደር' በማለት የሚጠሩት እኚህ ግለሰቦች ሕፃናት አስገድዶ ከመድፈር በተጨማሪ በግድያ ወንጀል በመከሰሳቸው እስከ ዕድሜ ልክ እሥራት የሚደርስ ቅጣት እንደተበየነባቸው ለማወቅ ተችሏል።

በጠቅላላው 18 ግለሰቦች የተከሰሱ ሲሆን ሁለቱ በአንድ ዓመት እሥራት እንዲቀጡ አምስት ደግሞ ነፃ ሆነው የተገኙ ሲሆን የተቀሩት 11 ሰዎች በከባድ ወንጅል ቅጣት ተበይኖባቸዋል።

አብዛኛው ወንጀል የተፈፀመው በምሽት እንደሆነ የታወቀ ሲሆን ግለሰቦቹ 'የልጃገረድ ደም መንፈሳዊ ኃይል እና ከለላ ያጎናፅፈናል' ብለው በማመን ወንጀሉን እንደፈፀሙም ታውቋል።

አንድ የመብት ጥሰት ተቋም እንዳሳወቀው ወንጀሉ ለተፈፀመባቸው ሕፃናት ለእያንዳንዳቸው 5 ሺህ ዶላር በካሳ መልክ የተከፈለ ሲሆን ለሟች ቤተሰቦች ደግሞ 15 ሺህ ዶላር ካሳ ተከፍሏል።

ጋርዲያን የተሰኘው ጋዜጣ በ2016 ባወጣው ዘገባ መሠረት አንድ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ባለስልጣን ኮንጎ ውስጥ እየተፈፀመ ያለውን ግፍ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማስቆም አልቻለም በሚል መንበራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል።

ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በሃገሪቱ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተጠቂ የሆኑ ሴቶች ድርጊቱን ካጋለጡ በገዛ ቤተሰቦቻቸው እና ዘመድ አዝማድ መገለል እንዳይደርስባቸው በመስጋት ሁኔታውን ለማንም አይናገሩም።

ከ20 ዓመታት በላይ በእርስ በርስ ግጭት ስታተመስ የቆየችው ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ በተለይ በምስራቁ ክፍል በሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ምክንያት ዜጎቿ ሰላምና መረጋጋት ማግኘት አልቻሉም።