'ምስራቅ እየሩሳሌም የፍልስጤም መሆን አለባት'

'ምስራቅ እየሩሳሌም የፍልስጤም መሆን አለባት' Image copyright AFP

የአምሳ ሰባት የሙስሊም ሃገራት ስብስብ የሆነው ቡድን መሪዎች ዓለም 'ፍልስጤምን እንደ ራስ ገዝ አስተዳደር እንዲሁም ምስራቅ እየሩሳሌምን እንደ ዋና መዲና' እውቅና እንዲሰጥ አሳስበዋል።

የእስላማዊ ሃገራት ጥምረት ባወጣው መግለጫ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ እየሩሳሌም የእስራኤል መዲና ናት ማለታቸው እርባና ቢስ ትርጉም አልባ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

አልፎም የአሜሪካ ውሳኔ በፍልስጤምና እስራኤል መካከል ስትጫወት ከነበረው የዳኝነት ሚና ጋር የሚጣረስና ከዚህ በኋላም ሊሆን የማይችል ነው ይላል መግለጫው።

የፍልስጤሙ መሪ ማሕሙድ አባስ በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት በጉዳዩ ጣልቃ መግባት እንዳለበት ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።

ጥምረቱ በቱርክ መዲና ኢስታንቡል ባካሄደው ስብሰባ ላይ ድምፃቸውን ያሰሙት አባስ "አሜሪካ ከዚህ በኋላ እንደ ገላጋይ መቀበል አይቻልም፤ ለእስራኤል መወገኗን በግልፅ አሳይታለችና" ብለዋል።

"ፍልስጤም ለጉዳዩ ፍትሃዊ መፍትሄ ለማበጀት ከአሜሪካ ጋር ስትሰራ ብትቆይም ትራምፕ ግን የክፍለ ዘመኑን አስደናቂ ድርጊት ፈፅመዋል" ሲሉም ተሰምተዋል አባስ።

መግለጫው የትራምፕን ውሳኔ ውድቅ ከማድረጉም በላይ የአሜሪካ ውሳኔ ፍልስጤማውያን ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነው ሲል ያትታል።

"አሜሪካ ሆን ብላ የእስራኤል-ፍልስጤም የሰላም ሂደት ፉርሽ የሚያደርግ ድርጊት ከመፈፀሟም በላይ ለፅንፈኝነትና ሽብርተኝነት መንገድ እየከፈተችም ነው" ይላል የጥምረቱ መግለጫ።

ዋሽንግተን በወሰነችው ውሳኔ ምክንያት ለሚደርሱ ጥፋቶች ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ መሆኗ እንደማይቀርም ጥምረቱ ባወጣው የአቋም መግለጫ አስታውቋል።

Image copyright TR

የዓለም ሃገራት ፍልስጤም እንደ ሃገር መቀበል አለባቸው የሚለው የእስላማዊ ሃገራት ጥምረት የተባበሩት መንግሥታት ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣና ምስራቅ እየሩሳሌምን የፍልስጤም መዲና አድርጎ እንዲያውጅም ያሳስባል።

የቢቢሲው ማርክ ሎዌን የጥምረቱ እርምጃ የትራምፕን ውሳኔ ተቃውሞ ከመንገድ ላይ ሰልፎች ላቅ ያለ ቢያደርገውም አሁንም አንዳንድ ሙስሊም ሃገራት የአሜሪካ አጋር በመሆናቸው ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ ይህን ያህል ነው ይላል።

ምንም እንኳ የቱርኩ ጣይብ ኤርዶዋን ቢገኙም ሳዑዲ አረቢያና ግብፅ ሚኒስትሮቻቸውን ብቻ ነው ወደ ስብሰባው የላኩት ይህም በእስላማዊ ሃገራት ጥምረት መካከል መከፋፈል እንዳለ ማሳያ ነው ይላል ማርክ በትንታኔው።

ዋይት ሃውስ የማሕሙድ አባስ የመሰሉ ንግግሮች ናቸው ሁኔታዎችን እያባባሱ ያሉት እንጂ የአሜሪካ ውሳኔ የእስራኤልና የፍልስጤም ሕዝቦችን የሚጠቅም ነው ብሏል።

ቤንጃሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው የጥምረቱ ስብሰባ እንዳልማረካቸው በመግለፅ "ፍልስጤማውያን እውነታውን በመቀበል ለሰላም ተግተው ቢሰሩ እንደሚሻል" ተናግረዋል።