ማህበራዊ ድረ-ገፆች እየሰሩ አይደለም

ፌስቡክ Image copyright Justin Sullivan

ከዕለተ ማክሰኞ ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የማህበራዊ ድረ-ገፅ በተለይ ደግሞ ፌስቡክና ትዊተርን መጠቀም እንደተቸገሩ ያነጋገርናቸው ሰዎች ይገልፃሉ።

በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎች የተነሳውን ግጭት እና አለመረጋጋት ተክትሎ ነው የማሕበራዊ ሚድያው እንዲዘጋ የተደረገው ሲሉ ድምፃቸውወን ለቢቢሲ የሰጡ ሰዎች ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

በአዲስ አበባ በተንቃሳቃሽ ስልክ ፌስቡክና ትዊተር መጠቀም እጅግ አዳጋች እንደሆነ ነገር ግን ሌሎች መገናኛ መንገዶችና ድረ-ገፆች አገልግሎት እየሰጡ እንዳለ ነው ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል።

በተደጋጋሚ የማሕበራዊ ድረ-ገፆች እንደሚቋረጡና ደንበኞች ቪፒኤን (ቨርቹዋል ፕራይቬት ኔትወርክ) ለመጠቀም እንደተገደዱ ያናገርናቸው ሰዎች ገልፀውልናል።

"ከባለፈው ወር ጀምሮ በቋሚነት በቪፒኤን ነው የምጠቀመው" ያለን ጦማሪው በፍቃዱ ኃይሉ ነው።

በሌላ በኩል በባህር ዳርም መሰል የኢንተርኔት መቆራረጥ መከሰቱንና በተለይ በተንቀሳቃሽ ስልክ ኢንተርኔት (ዳታ ኔትወርክ) ፌስቡክን ለመጠቀም እጅግ ከባድ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል፤ 'ዋይፋይ' ኔትዎርክ በመጠቀም ግን አገልግሎቱን እያገኙ እንደሆነም ማጣራት ችለናል።

በመቀሌና በሐረርም እንዲሁ በተመሳሳይ በተንቀሳቃሽ ስልክ ኢንተርኔት (ዳታ ኔትወርክ) ፌስቡክ እንደማይሰራ ነገር ግን 'ዋይፋይ' በመጠቀም የማሕበራዊ መገናኛ መንገዱን አንዳንዶች መጠቀም እንደቻሉ ማወቅ ችለናል።

በአንዳንድ ከተሞች ችግሮቹ የባሰ ሲሆን በተለይም በአዳማ ከተማ ማህበራዊ ድረ-ገፆችንም ሆነ ማንኛውንም የኢንተርኔት አገልግሎት በዳታ ኔትወርክ መጠቀም አስቸጋሪ እንደሆነ አይናለም ወንድወሰን ለቢቢሲ ገልፃለች።

አሶሼትድ ፕሬስ ማክሰኞ ዕለት በኢትዮጵያ የኢንተርኔት መቆራረጥ መታየቱን ጠቅሶ በኦሮሚያ ክልል ጨለንቆ አካባቢ የተከሰተው ችግር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቁሞ እንደነበር አይዘነጋም።

ይህንን ጥያቄ ለኢትዮ-ቴሌኮም ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አብዱራሂም አህመድ ቢቢሲ በጠየቀበት ወቅት "ኢንተርኔት አልተቋረጠም፤ ማህበራዊ ድረ-ገፆችም እየሰሩ ነው" ብለዋል።

በተጨማሪም በቪፒኤን የሚጠቀሙ ሰዎች ከኢትዮ ቴሌኮም አቅርቦት ጋር የተያያዘ ሳይሆን ከሚሰሩበት ድርጅት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችልም አቶ አብዱራሂም ለቢቢሲ ገልፀዋል።